የመምህርነት ሙያን ማህበረሰባዊ እይታዎችን ለማሻሻል...

 

የመምህራንን የቀድሞ ሙያና ክብር ለመመለስ መስራት እንደሚገባ ተነገረ!!

የመምህርነት ሙያን ማህበረሰባዊ እይታዎችን ለማሻሻል ሃገራዊ ንቅናቄ ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ተካሄደ፡፡

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ  በሀገራችን መምህርነት እንደ ሙያ ጥያቄ ውስጥ እንደገባ የሚያሳዩ ጠቋሚዎች እንዳሉ ተናግረው እየተዳከመ ለመጣው የሙያዎች ሁሉ መሰረት ለሆነው መምህርነት ማህበረሰቡ፣ የመንግስት  ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች  አጋር አካላት ቀደም ሲል የነበረውን ክብርና ተቀባይነት ለመመለስ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡ አሁን በሀገር ደረጃ  ያጋጠመው ችግር በአህጉርና በአለምአቀፍ ደረጃ የሚያጋጥም መሆኑን ገልፀው በንቅናቄ ብቻ ሳይሆን በችግሮች ላይ ተመርኩዞ የመፍትሄ ሀሳቦችን በመለየትና ተግባራዊነታቸውን በማረጋገጥ ችግሩን መቀነስ ብሎም ማጥፋት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡  

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ይሀን የተከበረ ሙያ በጥንካሬ እንዲወጣ ከመምህራን ምልመላ ጀምሮ ስልጠናዎችን በበቂ መልኩ መስጠትና መምህራንን ለሚያሰለጥኑ ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ ሙያውን በመሸሽ ጥሩ ደመወዝ የሚያስገኙ የትምህርት መስኮችን የመቀላቀል ዝንባሌዎች እየበዙና እየጠነከሩ  መምጣታቸው የመምህርነት ሙያ አደጋ እንዲጋረጥበት አድርጓል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ተማሪው፣ ህብረተሰቡ፣ ፖለቲከኛው እና መንግስት ስለመምህራን ምን ይላሉ ከማለት ባለፈ መምህራን ስለራሳቸው ምን ይላሉ የሚለውን በአንክሮ መመልከት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ መምህራን የሙያው ፍቅር ሳይሆን የገንዘብ ክብርን እንደሚያስቀድሙ ይታወቃል ስለዚህ መጀመሪያ ለሙያው ተገዥ መሆን እንዳለባቸው ገልፀው ደመወዝ በመጨመር ብቻ ሙያው ጠንክሮ እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡና በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው የመምህርነት ተሞክሮዎቻቸውን ያቀረቡ መምህራንና የተማሪ ወላጅ ማህበር ተወካዮች ንግግር አድርገዋል፡፡ በዳንግላ ወረዳ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩትና በሀገራችን የበጎ ሰው እጩ ሽልማት ባለቤት የሆኑት መምህር ስዩም ቦጋለ የተሰብሳቢዎችን ቀልብ የያዘ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም መምህር ማለት ለራሱ የሚኖር ሳይሆን እራሱ እንደሻማ ቀልጦ ለተማሪዎቹ ብርሃን የሚሆንና ለተቸገሩ ተማሪዎች ከፈጣሪ በታች በበጎ ተግባር የሚደርስ መሆኑ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው ከደመዎዛቸው 75% በመቀነስ ለተቸገሩ ተማሪዎች እንደሚረዱና በተለያዩ ምክንያቶች ተማሪዎች ችግር ሲደርስባቸው ከጎናቸው በመሆን ሳይሰለቹ እንደሚረዷቸውና በዚህ መልኩ ያስተማሯቸው ተማሪዎች ጥሩ ውጤት በማምጣት ለሀገርና ለወገን ኩራት ሆነው ማየታቸውና በዚህ ስራቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶችን ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተማሪ ወላጅ ማህበርን ወክለው ንግግር ያደረጉት ኢ/ር ጌታቸው ሰጠኝ እንዳሉት የመምህርነት ሙያ አሁንም ቢሆን እንዳልወደቀ ገልፀው ነገር ግን በማህበረሰቡ ዘንድ መሰራት ያለበትን ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ይበልጥ መሰራትና ተማሪዎችም ጥሩ ስነምግባርና ግብረገብነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ሀገር ወዳድ ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ የመምህራን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ላይ ትልቅ ስራ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የመምህርነት ሙያ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዴት ይታያል እና መምህራን በሙያቸው ተጠቃሚ ባለመሆናቸውና ኑሮአቸውን ለመደጎም ስራቸውን በመልቀቅ ሙያው አደጋ ላይ በመውደቁ የቀደመ ክብሩን ለመመለስ ምን መደረግ አለበት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዩች ላይ ጥናታዊ ፁሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይትና ክርክር ተደርጓል፡፡

የምክክር መድረኩ አዘጋጅ እንዲሁም ጥናታዊ ፁኁፍ አቅራቢ የሆኑትና  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመምህራን  ትምህርት እና የአመራር ልማት የልህቀት ማዕከል ዲን የሆኑት ዶ/ር አስናቀ ታረቀኝ እንዳሉት የአውደ ጥናቱ ዋና አላማ የመምህርነትን ክብርና ሞገስ እንደገና መመለስና ማኅበረሰቡ ስለመምህራን ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ብሎም መምህራን ማግኘት ያለባቸውን የሙያ ክብር እንዲያገኙ መስራት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በሀገሪቱ  ውስጥ መምህራንን ከሚያስለጥኑ ተቋማት ጋር በመሆን በትምህርት ጥራት ላይ የጋራ ስራ እየተሰራ  መሆኑን ጠቁመው ይህ ደግሞ መምህርነት ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያ የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በትምህርት ሚኒስቴር የመምህር እና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ አሰፋሽ ተካልኝ በሀገራችን ውስጥ ያሉ አምስቱ የልህቀት ማዕከላት ባልተመቻቸና ዘርፈ ብዙ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ እየሰሩ ያለውን ስራ አድንቀው ቀጣይ ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን በማውጣት መሬት  ላይ የወረደ ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን ስራ ለመስራት በመተሳሰርና አንድ በመሆን መምህርነት እንደ ሙያ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚሰጠው ቦታ ከፍ ይል ዘንድ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የግንዛቤ ፈጠራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡  

በመድረኩ የሁለተኛ ቀን ውሎ የመምህርን የሰው ኃይል አስተዳደር ማዕቀፍን አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር ያስጠናው ጥናት የጥናቱ ተሳታፊ በሆኑ ምሁራን ቀርቧል፡፡ በጥናቱ አንደተመለከተው መምህራን ለሃገር ዋልታ ለሌሎች ሙያዎች ደግሞ መሰረት በመሆናቸው ከመምህራን ምልመላ ጀምሮ፣ የመምህራን የሙያ ስልጠና ብሎም መምህራንን በስራ ገበታቸው ላይ እንዲቆዩ የማድረግ እና ከጦረታ በኋላ በሚኖራቸው ህይወት አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ከሙያው ሀገሪቷ ማግኘት የሚገባትን ትልቅ ግልጋሎት ማግኘት እንደሚቻል ተነግሯል፡፡ ለዚህም መምህሩን ያቀፈ ስራ እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል፡፡

በአውደ ጥናቱ ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጡ ምሁራን፣ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የመምህራን ማኅበር አመራሮች፣ በተለያየ ደረጃ የሚያስተምሩ መምህራን፣ በመምህርነት ሙያቸው አርአያነት ያለው ስራን ያበረከቱ መምህራን፣ የወላጅ ማህበር ተወካዮች እና ሌሎች ተገኝተዋል፡፡