“Social Ecological System Dynamics: Characteristics, Trends, and Integration in the Lake Tana Basin, Ethiopia” በሚል ርዕስ የታተመ መጽሀፍ ለንባብ በቅቷል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በመጽሃፍ ምረቃው ላይ እንደተናገሩት

መጽሀፉ ከምርምር የመነጨ እውቀት የተካተተበት በመሆኑ መታተሙ  በተለይም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን በዝግጅቱ መሳተፋቸው የሚያስደስት መሆኑን ገልፀው ወደፊትም ዩኒቨርሲቲው ይህን መሰሉን ስኬት የሚደግፈው ተግባር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

 

ዶ/ር ፍሬው አክለውም በዩኒቨርሲቲው የ55 ዓመት የትምህርት ጉዞ ውስጥ የተሰሩት የምርምር ውጤቶች ተሰንደው መቀመጥ ይኖርባቸዋል ብለዋለወ፡፡ ፕረዚደንቱ ቀጥለውም በእለቱ ለንባብ የበቃው መጽሀፍም የመጀመሪያው በመሆን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመረጃ ቋት ዝግጀት መጀመር ማብሰር እንዳለበት አሳስበዋል። ዩኒቨርሲቲውም  የምርምር ተቋም ለመሆን ያቀደውን ራዕይ ለማሳካት እንዲሁም ለዩኒቨርስቲው ተቋማዊ እውቅና ጉልህ ሚና ስለሚኖረው ከዚህ በኋላም መፅሀፍና የምርምር ውጤቶቻቸውን የሚያሳትሙ ተመራማሪዎችን መደገፍ እና ማበረታታት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

 

ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ የመሆን ራዕይውን ለማሳካትና ተወዳዳሪ ለመሆን የህትመት ባህላችንን በማሻሻል፣ በመነቃቃት ብሎም በማሳተም እንዲሁም ጥናቶችን  ወደ ማህበረሰቡ በመውሰድ ችግር ፈች የሚሆኑበት መንገድ ላይ መሰራት የሙሁራን ዋና ተግባር መሆን አለበት ሲሉ  ዶ/ር ፍሬው ተገኘ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ብሉ ናይል ተቋም ዳይሬክተር አቶ ጎራዉ ጎሹ መጽሃፉ 35 ምእራፎች እንዲሁም አምስት  ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን ይዘቶቹም  ስለአባይ ተፋሰስ ፣ስለስነ-ምህዳሩ ፣ እንዲሁም ወደፊት ምን መደረግ እንዳለበት የሚጠቁም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መጽሃፉ 49 ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን ተመራማሪዎቹም ከተለያዩ የምርምር ተቋማት እና፣ የክልል ቢሮዎች የተገኙ ሲሆን 57% የሚሆነውን የሸፈኑት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተመራማሪዎች  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመጽሀፉ አላማ በክልሉ እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተሰሩ የምርምር ስራዎችን በማዘጋጀት እውቀትን ተደራሽ ለማድረግ እና ማህበራዊ ስነ-ምህዳራዊ ትስስር ለመፍጠር የማገዝ ነው። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ሆነ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ውጭ ላሉ ተመራማሪዎች የመረጃ ምንጭ በመሆን መፅሀፉ እንደሚያገለግልም ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም መጽሃፉ ለልማት ጣቢያ ሰራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ ውሀ እና ግብርና ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች ሊረዱት  በሚችሉት መንገድ ይዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ  በቅርቡ ወደ አማርኛ እንደሚተረጎም ተገልጧል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት አኳቲክ ኢኮሎጂስት የሆኑት  ፕ/ር ስዩም መንግስቱ የመጽሀፉን ግምገማ  ያደረጉ ሲሆን አብዛኛው መጽሀፉ ላይ አስተዋጽኦ ያደረጉት ተመራማሪዎች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ጠቅሰው መበረታታት አለበት ብለዋል። ወደ ትርጉም በሚሄድበት ጊዜ በተቻለ አቅም ሙያዊና ሳይንሳዊ ቃላትን አቻ በሆኑ ቃላት ለግብርና ባለሙያዎችም ሆነ ለአርሶ አደሮች በሚገባቸውና ሊረዱት በሚችሉት ቋንቋ መጻፍ አለበት ብለዋል።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን እና ስት/ኮም/ም/ፕ ዶ/ር ዘውዱ እምሩ በመርሃ ግብሩ መዝጊያ ላይ ተገኝተው ይህን ተግባር ለሰሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ተገቢነት ያለው፣ ወቅታዊና ጠቃሚ የሆነ ስኬታማ እና እጅግ የሚያኮራ ስራ መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡ መፅሀፉ የ 49 ምሁራንን የምርምር ውጤቶች በአንድ መያዙ ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ለንባብ ምቹ ከመሆኑ ባሻገር በየመፅሀፍ መደርደሪያው ተበትነው የሚገኙትን ጠቃሚ እውቀቶች እንዲህ በአንድ ላይ መሰነዱ አስተዋጾውን የጎላ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የጥናቶቹ ትኩረት የህይዎታችን መሰረት ከሆነው አባይ ላይ መሆኑ የመጽሀፉን ዋጋ ከፍ የሚያደርገው ነው ብለዋል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ተቋም የመሆን እቅዱን ለማሳካት  የቀሩት አመታት ትቂት በመሆናቸው ለዚሁ እቅድ መሳካት የሚረዳውን የምርምር ስራዎችን እና  መጽሀፍትን የማሳተም እንዲሁም ተመራማሪዎችን የመደገፍ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው ተመራማሪዎችም  ዩኒቨርሲቲውን መግፋት እና መጠየቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ሳይንሳዊ አስተያየት ለሰጡ እንዲሁም  በመጽሀፉ ውስጥ  ለተሳተፉ ተመራማሪዎች የምስጋና የምስክር ወረቀት በማበርከት ጉባኤው ተጠናቋል።