130ኛው የአድዋ ድል በዓል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በድምቀት ተከበረ

ትላንት የተገኘ ድል፤ ለዛሬ ስንቅ!”፦ 130ኛው የአድዋ ድል በዓል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በድምቀት ተከበረ

BDU

03 Mar, 2026

ትላንት የተገኘ ድል፤ ለዛሬ ስንቅ!”፦ 130ኛው የአድዋ ድል በዓል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በድምቀት ተከበረ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት እና የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን 130ኛውን የአድዋ ድል በዓል፣ የአባት አርበኞች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የአስተዳድር ሰራተኞችና ተማሪዎች በተገኙበት በታላቁ የጥበብ አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ አክብሯል።

የዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ሲያስተላልፉ፤ አድዋ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀን መሆኑን ገልጸዋል። "አባቶቻችን በዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን ወራሪ ኃይል በጀግንነትና በአንድነት ድል በማድረግ የነፃነትን ችቦ አቀብለውናል፤ ይህ ታሪክ ለትውልድ የሚተላለፍ የማይደበዝዝ አኩሪ አሻራችን ነው" ብለዋል።


የጥንታዊት ኢትዮጵያ አባት አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዳኝነት አያሌው፣ ዩኒቨርሲቲው ለአርበኞች ለሚሰጠው ክብርና እንክብካቤ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። አክለውም ታሪክን ለትውልድ ለማጋራት "የታሪክ ክበባት" እንዲጠናከሩና ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ የታሪክ ትምህርት ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። አዳራሹም በአርበኞች ፉከራ እና ሽለላ ደምቆ ውሏል።

የበዓሉን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ፋይዳ የሚያትት ሰፊ የፓናል ውይይት በዶ/ር ገረመው እስከዚያ፦ የታሪክ ድርሳናትን ዋቢ በማድረግ የአድዋን ድል አመጣጥ፤በአቶ ወርቅነህ ገነት፦ ድሉ በፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ ረገድ የፈጠረውን ተፅዕኖና በዶ/ር ሞገስ ሚካኤል፦ አድዋ በቋንቋ እና በባህል ግንባታ ላይ ያለውን ሚና በተመለከተ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሲኒማና ቴአትር ጥበባት ተማሪዎች በአድዋ ጦርነት ዙሪያ የሚያጠነጥን አጭር ድራማ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተማሪዎች የቀረቡ ግጥሞችና የባህል ማዕከል የሙዚቃ ቡድን ዝግጅቶች ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአባቶቻችን ታሪክ በመዘከርና ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የበኩሉን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል።