የ"Turnitin" ሶፍትዌር አጠቃቀም ስልጠና

የምርምር ስራዎችን ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችል የ"Turnitin" ሶፍትዌር አጠቃቀም ስልጠና መሰጠት ጀመረ

Campus Name

10 Feb, 2026

የምርምር ስራዎችን ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችል የ"Turnitin" ሶፍትዌር አጠቃቀም ስልጠና መሰጠት ጀመረ
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፤ ጥር 02/2018 ዓ.ም
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ጽ/ቤት አስተባባሪነት ለዲኖች፥ ዳይሬክተሮችና ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች የTurnitin ሶፍትዌር አጠቃቀም ስልጠና እየተሰጠ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የምርምር ጉዳዮች ኮርፖሬት ዳይሬክተር  የሆኑት ፕሮፌሰር ነፃነት ፈንታሁን በዩኒቨርሲቲው የሚካሄዱ የምርምር ስራዎችን ጥራት ለመጠበቅ እና ከስርቆት (Plagiarism) የፀዱ እንዲሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝና ሶፍትዌሩ በከፍተኛ ወጪ በግዢ የቀረበ መሆኑን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት እስከ 1,500 ለሚደርሱ ተመራማሪዎችና መምህራን አካውንት የመክፈት አቅም እንዳለው ገልጸዋል። ፕሮፌሰሩ አክለውም "ይህንን ሶፍትዌር ስንጠቀም በተፈቀደልን ልክ እና እጅግ በአግባቡ ሊሆን ይገባል" በማለት አሳስበዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህትመት፥ዶክመንቴሽንና ስርጭት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አባባይ ከተማ፣ ስለ ሶፍትዌሩ ምንነት እና አጠቃቀም ሰፊ ገለፃ አቅርበዋል። በገለጻቸውም፦አዲስ አካውንት እንዴት መክፈት እንደሚቻል፤የምርምር ሰነዶችን እንዴት መመርመር (Check) ማድረግ እንደሚቻል፤እና ውጤቱን እንዴት መተንተን እንደሚቻል በዝርዝር አሳይተዋል።
ዶ/ር አባባይ ከተማ አክለውም፣ ሶፍትዌሩ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውጭ መጠቀም እንደማይቻልና ሰልጣኞች በአጠቃቀም ሂደት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው የአብያተ መጸሃፍት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ይበልጣል ታፈረ  ሶፍትዌሩን እንዴት ማስተዳደር (Manage) ማድረግ እንደሚቻል እና ተቋሙ የከፈለውን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ እያንዳንዱ ተጠቃሚ በራሱ ትክክለኛ መረጃ አካውንት መክፈት እንዳለበት በተግባር አስረድተዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ከሰልጣኞች ለተነሱ ጥያቄዎች በዶ/ር አባባይ ከተማ አማካኝነት ዝርዝር ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። ይህ ስልጠና ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዘርፍ የጀመረውን የጥራት ማረጋገጫ ጉዞ አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚያስኬደው ይታመናል።