የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ አመታዊ አውደ ጥናት አካሄደ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ አመታዊ አውደ ጥናት አካሄደ
-------------------------------------------------------------------
በትዕግስት ዳዊት
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት አካዳሚ ለሁለት ቀናት የሚቆየውን 4ኛውን ሀገራዊ አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።

የአውደ ጥናቱ ዋና ጭብጥ “sport as a tool for sustainable social development and peace: realizing the potential” የሚል ነው። በአውደ ጥናቱ ተገኝተው ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ አካዳሚ ዲን ዶ/ር ተስፋዬ ደሳለኝ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት አሰጣጥ እና ጥናት እና ምርምሮች አለም አቀፍ ደረጃዎችን ጠብቀው እየተካሄዱ መሆናቸውን ማረጋገጥ የአካዳሚው ተቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር እሰይ ከበደ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳክ ጉዳዮች ም/ፕ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ተገኝተው ዩኒቨርሲቲው በፕሮግራም ስብጥር፣ በሰው ሀይል እንዲሁም በምርምር እያደገ መሆኑን ተናግረው ዩኒቨርሲቲው የዛሬ 10 አመት የምርምር ተቋም የመሆን ራዕዩን ሰንቆ እየሰራ ሲሆን ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከድህረ ምረቃ መርሃ ግብሮች በተጨማሪ 13 የምርምር ተቋማትን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው የምርምር ተቋም እንዲሆንም እነኝህን የመሳሰሉ አውደ ጥናቶች ጉልህ ደርሻ አለቸው ብለዋል።

ዶ/ር እሰይ በማከልም የስፖርት አካዳሚው ምሁራን ስፖርቱ ላይ ያሉ ችግሮችን ወርደው በማጥናት የሀገራችን ስፖርት በሁሉም ዘርፎች የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የበለጠ እንዲሰሩና የስፖርት መሰረት የሆኑት ልጆችና ወጣቶች ላይ ፕሮጀክት በመቅረፅ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተወካይ ወ/ሮ ሄሮዳይት ዘለቀ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ስፖርትን ለስራ፣ ለሀብት ፈጠራና ገቢ ማመንጫ እንዲሆን ለማድረግ በጥናትና ምርምር የታገዘ ስራ መስራት እንደሚገባ ጽ/ቤታቸው አምኖ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለውጤታማነቱም በሀገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጋራ እቅድ በማውጣትና ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመነጋገር እየሰራ መሆኑን ተናግረው ወደፊትም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አቅም በፈቀደው አግባብ መሰል አውደ ጥናቶችን እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

ሎሬት ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ የአ.አ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል መምህር ፣ተመራማሪ ፣ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሪ እና የአለም አቀፍ volley ball instructor አለማየሁ ሸዋታጠቅ የአውደ ጥናቱን ቁልፍ ማስታወሻ ያቀረቡ ሲሆን በንግግራቸውም የረጅም ጊዜ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል። ከተሳታፊዎች ጋርም ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ተሳታፊወችም ልምድ እንደቀሰሙበት ተናግረዋል፡፡

መርሀ ግብሩ ነገም የሚቀጥል ሲሆን ከሚቀርቡት 25 ጥናታዊ ጽሁፎች መካከል 14 የሚሆኑት በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሚቀርቡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 5 የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲው የPhD ተማሪዎች፣ 9 ያክሉ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሚቀርቡ ናቸው። 11 የሚሆኑት ጥናታዊ ጽሁፎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ ምሁራን የሚቀርቡ ሲሆን በአጠቃላይ ከሚቀርቡት ጥናታዊ ጽሁፎች 56 % በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደሚቀርቡ ተጠቅሷል።