በስፔን ባርሴሎና ከፍተኛ የስፖርት ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከACCeDE Spain Barcelona እና ከETHIO-GAVA(Sport Education and Women Development Enterprise) ጋር በመተበባር የተዘጋጀዉና Youth Sport Development and Professional Training በሚል ርዕስ ሲሰጥ የቆየው ዓለምአቀፍ ይዘት ያለዉ ስልጠና ሐምሌ 17/2013 ዓ.ም ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

የETHIO-GAVA ድርጅት ኃላፊ የሆኑት አቶ ይመር ሃይሌ እንደተናገሩት ግንቦት ወር 2013ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት በእግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ እና በዘመናዊ ስፖርት እድገት ዙሪያ ACCeDE ከተባለው የባርሴሎና ድርጅት ጋር ከሐምሌ 12-17/2013ዓ.ም ድረስ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ በተለይም ቅርጫት ኳስ እና እግር ኳስ ከስፔን ካታሎን አንደኛ ደረጃ ፕሮፌሽናል አሰልጣኞችን በማምጣት የአካዳሚ መምህራንን ጨምሮ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመረጣቸው በአማራ ክልል ለሚገኙ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች፤ የፌዴራልና የአማራ ክልል ፌዴሬሽን አመራሮች እና ከባሕር ዳር ከተማ አስተደደር ለመጡ ስፖርተኞች ስልጠናው ተሰጧል፡፡ የስልጠናው ዋና ትኩረት በአለም ላይ የታወቁት ስፔን ባርሴሎና ካታሎናዊያን በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ያረጉበትን የአሰለጣጠን ዘዴ ልምድ ለመቅሰም ነው ብለዋል፡፡

ኃላፊው አያይዘውም በታዳጊ ፕሮጀክት ላይ እግር ኳስ፣ ቮሊቮል፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ባድሜንተንና አትሌትክስ ሠልጣኝ ወጣቶች ለስፖርት ማዘውተሪያ የሚውል አልባሳትን ከማበርከት ባሻገር ለስፖርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ማለትም የእግር፣ የቅርጫት፣ የእጅ እና የቫሊቮል ኳሶችንና ለልምምድ የሚያገለግሉ እቃዎችን ድጋፍ አድርገናል ብለዋል፡፡ እነዚህ ድጋፎች በተደረሰው ስምምነት መሰረት ለ2 ዓመት የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡

የስፖርት አካዳሚ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ዲን የሆኑት ዶ/ር ተከተል አብርሃም ለተሳታፊ ሰልጣኞችና የፌዴሬሽን አመራሮች ወደፊት ስፖርቱን በጋራ ለማሳደግና ዘመናዊ ስፖርትን ለማሳደግ በሳይንስና በምርምር የተደገፈ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራትና በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ የስፖርት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና ፌዴሬሽኖች ከዚህ ልምድ በመዉሰድ ለሀገራችን ስፖርት እድገት የበኩላቸዉን ድርሻ እንዲወጡ ም/ዲኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ዲን ዶ/ር ዳኛቸዉ ንግሩ በመርሃ-ግብሩ መጠናቀቂያ ላይ ለአሴዴና ኢትዮ-ጋቫ አመራሮችና አሳልጠኞች ላደረጉት ድጋፍና ስልጠና አመስግነዋል፡፡ ከስፔን የመጡት ልዑካን በባሕር ዳር ከተማ ዉስጥ የሚገኘዉን የተስፋ ልማት ማህበር የህጻናትና አረጋዊያን ማዕከል የጎበኙት ልዑካኑ በቀጣይ አብሮ ለመስራት ቃል መግባታቸዉን ዶ/ር ዳኛቸዉ ጠቁመው ስለተደረገዉ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በዩኒቨርሲቲዉና በአካዳሚዉ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በእለቱ ተሳታፊዎች፤ የአሴዴ ልዑክ እና ከፌዴሬሽን የመጡ አመራሮች በስፖርት አካዳሚው በተዘጋጀው ቦታ ላይ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሂደዋል፡፡
በመዝጊያ መርሃ-ግብሩም ለተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት በመስጠት ተጠናቋል፡፡

Image: 
Date: 
Wednesday, July 28, 2021