Latest News

“የሀገራችን ችግር የሚፈታው የችግሮችን ስፋትና ጥልቀት በሚረዱ ምሁራን በመሆኑ የምንግዜም ጠላታችን የሆነውን ድህነት ለማስወገድ ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት መስክ ትኩረት ሰጥተው የመስራት ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው”

(የኢ.ፍ.ድ.ሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ2012 ተመራቂዎችን ሲያስመርቁ ከተናገሩት)

 

በሙሉጌታ ዘለቀ

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 7520 ተማሪዎች በበይነ - መረብ አስመረቀ፡፡

 

በድኅረ ምርቃ መርሀ ግብር በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛውና በተከታታይ መርሀ-ግብር  2254 ተማሪዎች፣ በሦስተኛ ዲግሪ መርሀ-ግብር 40 ተማሪዎች፣ እንዲሁም በስፔሻሊቲ መርሀ-ግብር 41 ተማሪዎች፣ በምስክር ወረቀት መርሀ-ግብር 642 ተማሪዎች በድምሩ 7520 ተማሪዎችን በበይነ-መረብ በመታገዝ በዛሬው እለት አስመርቋል፡፡ ከተመራቂ ተማሪዎቸ መካከል  2345 ሴቶች ሲሆኑ፤ ከነዚህ ሴት ተመራቂ ተማሪዎች መካከል አምስቱ የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡  

 

በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ የኢ.ፍ.ድ.ሪ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስቴር ድኤታና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል ወ/ሮ ሰሀረላ አብዱላሂ፣ ፕ/ር ማስረሻ ፈጠነ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል እንዲሁም ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ የአማራ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል፣ የዬኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት፣ ዲኖችና ዳይሬክተሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

 

በስነ-ስርዓቱ የባህር ዳር ዪኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተመራቂ ተማሪዎችና ለተመራቂ ቤተሰቦች እንኳን ደስ ያላችሁ መልክዕት አስተላልፈዋል፡፡ በመልዕክታቸውም አለምን ባስጨነቀው የኮሮና ወረርሽኝ ተግዳሮት ሳይደናቀፋ የሚጠበቅባቸውን አሟልተው ለተመረቁ ተማሪዎች አድናቆታቸውን ገልፀው ወደ ቀደምት ትልቅነታችን እና ጥበብ ለመመለስ እና አሁን የጀመርናቸውን የአባይ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማሳካት የጋራ መድሃኒት ስለሚያስፈልገን ሁላችንም ለሀገራችን ሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባን አሳስበዋል፡፡

 

የኮረና ቫይረስን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዩኒቨርስቲዎች ሕይወትን ለመታደግ የእውቀት እና የህዝብ ተቋምነታቸውን ማስመስከራቸውን ጠቅሰው ለዚህም ባሕር ዳር ዪኒቨርሲቲ የኮረና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በማምረት እና በርካታ የፈጠራ ስራዎችን በማበርከት ህብረተሰቡን ከወረርሽኙ እየታደገ መሆኑን ዶ/ር ፍሬው ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች በኮቪድ 19 ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከትምህርት እንዳይለዩ በዩኒቨርሲቲው የICT ባለሙያዎች የበለፀገ የትምህርት አስተዳደር ስርዓት (Learning management System) ለአማራ ክልለዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ማበርከቱን አውስተዋል፡፡

 

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፍ.ድ.ሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ እንዳሉት መማር ትርጉም የሚኖረው የህብረሰተቡን ኑሮ ማሻሻልና ለችግሮቹ መፍቻ የሚሆን አዳዲስ አሰራሮችንና ሀሳቦችን መፍጠር ሲቻል መሆኑን ጠቁመው የሀገራችን ችግር የሚፈታው የችግሮችን ስፋትና ጥልቀት በሚረዱ ምሁራን በመሆኑ የምንግዜም ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማስወገድ ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት መስክ ትኩረት ሰጥተው ለመስራት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

 

በአክለውም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የልሕቀት ማዕከል ለመሆን የሚያደርገውን ትጋት አድንቀው በእምቦጭ ዙሪያ ብዙ ሥራ መሥራት የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ በስፋት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል። ከአባይ ፏፏቴ ጀምሮ እስከ ሰሜን ብሄራዊ ፓርክ ድረስ ትኩረት በመስጠት የቱሪዝም ኮሪደር ለማድረግ የሚቻልበትን ምርምር በመስራት መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች ማሳየትም ከዩኒቨርሲቲው እንደሚጠበቅ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ ተናግረዋል፡፡

 

የምረቃ ሥነ-ስርዓቱን ጥቂት ተማሪዎች አዳራሽ ውስጥ በአካል በመገኘት አብዛኛዎቹ ተመራቂ ተማሪዎች ደግሞ በየቤታቸው ሆነው በአማራ ቴሌቪዥን ከጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢ አዳራሽ በቀጥታ ስርጭት፣ በፌስቡክ እና ዩቲዩብ  የተላለፈውን ታድመዋል፡፡

አገር-በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ህክምና ጋር በማቀናጀት የአዕምሮ ሕክምናን ማሳደግ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡

(ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ/ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፌስቡክ ገፅ የተወሰደ)

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና በአንዳሳ ደብረ መንክራት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም መካከል የአዕምሮ ሕክምናን በተቀናጀ መልኩ ለማሳደግ “አገር-በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ሕክምና ጋር በማጣመር የአዕምሮ ጤና እንክብካቤን ማሳደግ” በሚል መሪ ቃል ነሐሴ 15፣2012 ዓ.ም በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥበበ ግዮን ግቢ በስነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት ውይይት ተደርጓል።

የውይይቱ ዓላማ

የውይይቱ ዓላማ በአገራችን በተለይም በክልላችን በአዕምሮ ህመም ምክንያት የሚደርሰውን መጠነ-ብዙ ተጽዕኖ መቀነስና የአዕምሮ ህመም ታማሚዎችን የተቀናጀ የመንፈሳዊ ወይም የፀበልና የዘመናዊ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የታማሚዎችን የአዕምሮ ጤና በማሻሻል፣ ቤተሰቦቻቸውና አገር ላይ የሚደረሰውን ጫና በመቀነስ ለህብረተሰባቸው ብሎም ለአገራቸው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማስቻል ነው። ኮሌጁ ከተሰማራባቸው አራት አብይ ዓላማዎች ማለትም መማር-ማስተማር፣ ማህበረሰብ አገልግሎት፣ ምርምር እና የሕክምና ስራ አንፃር የሚኖረው ቀጥተኛ ጥቅም ከፍተኛ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ አገር በቀል ጥበብንና ዕውቀትን በዘመናዊ መንገድ በምርምር በመደገፍ ዩኒቨርሲቲው ላስቀመጠው በቅርቡ በአፍሪካ ከምርጥ የምርምር ተቋማት አንዱ የመሆን ራዕይ እውን መሆን የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በውይይቱም የሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት የተጋበዙ ሲሆን በዋናነት ግን የአንዳሳ ደብረ መንክራት ገዳም አስተዳዳሪና ካህናት አባቶች፣ አጥማቂያን፣ ሰባኪያን፣ የአንዳሳና አካባቢው ታዋቂ ሰዎችና የሃገር ሽማግሌዎች፣ ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ፣ ገዳሙ የሚገኝበት ወረዳ ማለትም ከባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት፣ የአንዳሳ ጤና ጣቢያ ሃላፊና ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ቢሮ ማለትም የአስተዳደርና ቢዝነስ ም/ፕሬዝዳንትና ከሕ/ጤ/ሳ/ኮ ዋና ስራ አስፈጻሚ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የውይይቱ ይዘት

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ቢዝነስ ም/ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ መድረኩን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስከፈቱ በኋላ የኮሌጁ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የሺጌታ ገላው የውይይቱን ዓላማ በማስተዋወቅ ውይይቱን አስጀምረዋል፡፡ በስነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል በኩል ስለ አዕምሮ ጤና እና አዕምሮ ህመም ለተወያዮች የመነሻ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን ለሚታቀዱ ስራዎች ክንውን ሲባል በተቀናጀ መልኩ የአዕምሮ ታማሚዎችን በመንከባከብ ከሚሰሩት ተቋማት ማለትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ከዕንጦጦ ኪዳነ-ምህረትና ከሽንቁሩ ሚካኤል ገዳማት ጋር እየሰሩበት ያለው ተሞክሮ (ልምድ ልውውጥ) ለታዳሚዎች ቀርቧል።

ከዚህ በመቀጠል መድረኩ ‘እኛስ እንዴት በቅንጅት መስራት እንችላልን?’ በሚል የውይይት መነሻነት፣ እንግዶች ሃሳብ እንዲያንሸራሽሩ ተደርጓል፡፡ ከአንዳሳ ደብረ-መንክራት የመጡ አባቶች ገዳሙ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የነበረው ግንኙነት የቆየ እንደሆነና በተለይም የተለያዩ ወረርሽኞች ሲከስቱ (ለምሳሌ ወባ፣ አተት) ኮሌጁ የጤና ባለሙያዎችን በመላክ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ከገለፁ በኋላ አሁንም የአዕምሮ ህመም ያለባቸው ምዕመናን በገዳሙ በጣም በከፍተኛ ቁጥር ስለሚገኙና ከፀበል ውጭ ዘመናዊ ሕክምና ስለማይከታተሉ የቅንጅት ስራውን መጀመር አድንቀው ከዩኒቨርሲቲው ጋር አብረው መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች በተወያዮች ተነስተዋል፡-

1. በቅንጅት ከገዳሙ ጋር ሊሰሩ የታቀዱ ስራዎች በግልጽ መቀመጥ እንደሚኖርባቸውና ጥናት ላይ የተደገፉ እንዲሆኑ ቢደረግ፣

2. ከገዳሙ ጋር ሊሰሩ የታሰቡ ስራዎች በፍጹም የቤተክርስቲያኗን ዶግማ የማይነኩና የአካባቢውን ማሕበረሰብ ወግና ባህል ያከበረ መሆን እንደሚገባው፣

3. ከገዳም አባቶችና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ኮሜቴ ተዋቅሮ የሚሰሩ ስራዎች ክትትል ቢደረግባቸው ቶሎ ለማረምና ለማስተካከል እንደሚያግዝ፣

4. ዩኒቨርሲቲው ወይንም ኮሌጁ ለገዳሙ የሚያስፈልጉ ስልጠናዎችን ቢሰጥና አቅጣጫ ቢያስይዝ፤

5. የምዕመናን የአዕምሮ መድኃኒት መከታተልም (ዘመናዊ ሕክምና መከታተል) ከገዳሟ አሰራር ውጭ እንዳልሆነና ለዚህም ገዳሟ በቀጥታ እንደምታግዝ፤

6. ወደ ገዳሙ የሚመጡ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ መሆን አንደሚገባቸውና ከዩኒቨርሲቲው በደብዳቤ ህጋዊነታቸውን በማረጋገጥ እንዲላኩ፣ ወደ ገዳሙ ለዚህ ስራ ተብሎ ከመጡ በኋላ የሚሰሩት ስራም በስምምነታችን ላይ የተፈቀዱትን ብቻ መሆን እንደሚኖርበት ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የታደሙ የአካባቢው ታዋቂ ሰዎችና ሽማግሌዎችም በበኩላቸው የቅንጅት ስራው ለአዕምሮ ታማሚዎች የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑንና ለአካባቢው ማህበረሰብም መልካም እድል መሆኑን ገልጸው የሚከተሉትን አንኳር ነጥቦች አንስተዋል፡፡

1. የአካባቢው ማሕበረሰብ የገዳሙ ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን ከገዳሙ ጋር የሚሰሩ የቅንጅት ስራዎች ለማሕበረሰቡ በተለያየ መንገድ በማስተዋወቅ ጠቀሜታውን ማስተማር አንደሚገባ ፣

2. ምንም እንኳን ሕብረተሰቡ አማኝ እንደሆነና ለማንኛውም የአዕምሮ ህመም ጸበል ቦታ እንደሚያዘወትር ቢታውቅም በእርኩስ መንፈስ የሚመጣውን የአዕምሮ ህመም በፀበል መከላከልና ማዳን ቢቻልም በተለያዩ ችግሮች ለሚከሰት ጭንቀት ግን ዘመናዊ ህክምና እንደሚያስፈልግ ለማህበረሰቡ ትምህርት ቢሰጥ መልካም እንደሆነ፤ለምሳሌ፣ አንድ ገበሬ ቀንጃው በሬ (ብቸኛ በሬው) ቢሞትበትና በአዕምሮ ጭንቀት ቢታመም ይህ በምክር አገልግሎትና በዘመናዊ ህክምና ሊድን ይችላል እንጂ በፀበል ስለማይድን የተቀናጀ የአዕምሮ ጤና እንክብካቤ ለዚህ ዓይነቱ የአዕምሮ ጭንቀት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

3. ምንም እንኳን አንዳንድ የአካባቢው የአዕምሮ ታማሚዎች አልፎ አልፎ ወደ ዘመናዊ ሕክምና ሂደው መድኃኒት ቢሰጣቸውም በቤተሰቦቻቸው ጫና ወደ ፀበል ቦታ ሲወሰዱ አንዳንድ የእምነት አባቶች መድኃኒት መውሰድ እምነትን ማጓደል እንደሆነ በመገሰጽ መድኃኒት መውሰዳቸው እንዲቋረጥ ምክንያት ስለሚሆኑ የቅንጅት ስራው ይህን መሰል ችግር ያስቀርልናልና መልካም ነው ሲሉ የአካባቢው ሽማግሌዎች ጠቀሜታውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የአንዳሳ ጤና ጣቢያ ኃላፊም የቅንጅት ስራው በጣም አስፈላጊና ለማህበረሰቡ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው ጤና ጣቢያውም የሚጠበቅበትን ለማገዝ ፍቃደኛ መሆኑንና ከገዳሙና ዩኒቨርሲቲው ጎን ሆኖ ህብረተሰቡን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አስረድተው ስራው ውጤታማ እንዲሆን ከሦስቱ አካላት ማለትም ከዩኒቨርሲቲው፣ ከገዳሙ አባቶች እና ከአንዳሳ ጤና ጣቢያ ኮሚቴ ተዋቅሮ ቢሰራ መልካም እንደሆነ ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ቢዝነስ ም/ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ የገዳሙ አባቶች የዩኒቨርሲቲውን ጥሪ አክብረው ለውይይት ስለመጡ አመስግነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት አለመገኘታቸውን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲውን በመወከል ከገዳሙ ተወያዮችና ከአገር ሽማግሌዎች ለተነሱት ሐሳቦች ማብራሪያ በመስጠት ለቅንጅት ስራው ውጤታማነት የሚያግዙ መሰረታዊ ስራዎችን እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ አክለውም የሚከተሉትን ነጥቦችና የውሳኔ አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል፤

1. የቅንጅት ስራው በሚሰራበት ወቅት ሊፈጠር የሚችልን ስጋት ለመከላከል በገዳሙ አባቶች በኩል የገዳሟን ዶግማ ከማስጠበቅ አንፃር ለተነሱት የጥንቃቄ ሐሳቦች፣ ዩኒቨርሲቲው በኮሌጁ በኩል የዕቅድ ትውውቅ ፕሮግራም እንደሚያዘጋጅና የሚሰሩ ስራዎች በግልጽ ለውይይት እንደሚቀርቡ፤

2. ዘላቂነቱን ለማስጠበቅና ለገዳሙ ስራ አመችነት ሲባል ዩኒቨርሲቲው ከገዳሙ ጋር የጋራ ስምምነት እንደሚያዘጋጅና በቅርቡ እንዲያስፈጽም፤

3. የሚያስፈልጉ የሙያ ስልጠናዎች ለገዳሙ አባቶችና አባላት በኮሌጁ በኩል እንደሚዘጋጅና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የሺጌታ ገላው በበኩላቸው ኮሌጁ ገዳሙ ድረስ ሄዶ መወያየት ሲገባው ካለው የመሰብሰቢያ ቦታ አመችነት አንፃር አባቶችን ወደ ኮሌጁ እንዲመጡ መደረጉ የማንገላታት ባህሪ ቢኖረውም አባቶች ግን በተያዘው ቀጠሮ መሠረት በመገኘታቸው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ፕሮፌሰር የሺጌታ የእምነት አባቶች ለሕክምና ሙያና አገልግሎት እጅግ እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው ካሁን በፊትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስትሰራበት እንደቆየች ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የቅንጅት ስራ የዘገየና የኮሌጁ ድክመት መሆኑን ገልጸው የእለቱ ውይይት ጥሩና መልካም አጋጣሚ እንደሆነና ኮሌጁ በስነ-አዕምሮ ህክምና ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሙያዎች ከገዳሙ ጋር በጋር መስራቱ የሚኖረውን የላቀ ጠቀሜታ አብራርተዋል። ፕሮፌሰር የሺጌታ ከዚህም ጋር አያይዘው የእምነት አባቶች በየእምነታቸው ሆስፒታል ድረስ እየመጡ ታማሚዎችን እንዲጠይቁና ለታማሚዎች የመንፈስ ጥንካሬ እንዲሰጡ ለወደፊቱ ይመቻቻልም ብለዋል።

ቀጣይ ስራዎች

በመጨረሻም ከገዳም አባቶች፣ ከዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብና ከአካባቢው ሽማግሌዎች የተውጣጣ ኮሜቴ ተዋቅሮ ቀጣይ የቅንጅት ስራዎች እንዲሰሩ በመወሰን ውይይቱ በጥሩ ሁኔታ ተጠናቋል።

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሰራውን የትምህርት ማስተግበሪያ ስርዓት ለአብክመ ትምህርት ቢሮ አስረከበ
-----------------------------------------------------------------------------------
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ መካከል በተደረገ ስምምነት መሰረት በዩኒቨርሲቲው አይ.ሲ.ቲ ዳይሬክቶሬት ክፍል የተሰራው የትምህርት ማስተዳደሪያ ስርዓት ርክክብ ተፈፅሟል፡፡

በመርሃ ግብሩ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የኮረና ቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ስርጭቱን ለመግታት ከሚደረጉ ከፍተኛ ጥረቶች ውስጥ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት ህብረተሰቡን ከወረርሽኙ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን ሲያበረክት ቆይቷል ፡፡ የወረርሽኙ መከሰት ካስቀራቸው ነገሮች አንዱና ለትምህርቱ መስክ አዲስ መንገድ ያሳየው የገፅ ለገፅ ትምህርት መቅረቱ ነው፡፡ እንደ ዶ/ር ዘውዱ ገለፃ ለዚህም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ከሚያደርጋቸው ያላሳለሰ ጥረቶች አንዱ በሆነውና ተማሪዎች በያሉበት ቦታ የማስተማሪያና የምዘና መሳሪያዎች እንዲደርሷቸው እና በትምህርቱ እየተሳተፉ እንዲቆዩ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በጣም አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለይ ባሁኑ ስዓት በዩኒቨርሲቲው አገልግሎት እየሰጠ ያለው የቪዲዮ ኮንፈረሲንግ ሲስተም በሙሉ ተግባር ላይ እንዲውል በማድረግ ዛሬ ላይ የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎቻችን የመመረቂያ የጥናት ፅሁፎቻቸውን በያሉበት ቦታ ሆነው ርቀት ሳይገድባቸው ስራዎቻቸውን በማቅረብ ተፈትነው ነሀሴ 23 ቀን በሚከናወነው ምረቃ ለመታደም በዝግጀት ላይ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ የትምህርት ማስተዳደሪያ ስርዓትን በዩኒቨርሲቲያችን ደረጃ በመስራት ተማሪዎች እና መምህራን የፊት ለፊት መስተጋብሩ በተቋረጠበት ስዓት ስራዎቹ ሳይቋረጡ በሁሉም የትምህርት ክፍሎች ስልጠናዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል ፡፡

አያይዘውም ዛሬ ለትምህርት ቢሮ በይፋ የሚረከበው የትምህርት ማስተዳደሪያ ስርዓት በተለይ ዩኒቨርሲቲው በስትራቴጅክ ዘመኑ የe- university ወይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ትምህርት መማርና ማስተማርን ምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራቶችን ለማዘመን በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ዩኒቨርሲቲውን ከፍ ለማድረግ ያስቻለ ስራ ነው ብለዋል ፡፡

በመርሃ ግብሩ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ባስተላለፉት መልእክት ዩኒቨርሲቲው አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ማፍራት፣ ችግር ፈች ምርምር መስራት እና የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት መሆኑን አስታውሰው፤ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ዩኒቨርሲቲዎች በተልኮ እንዲደራጁ በተደረገው ጥናት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሁለት የዕቅድ ዘመናትን (ከአስር ዓመት በላይ) የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሁኖ ሲሰራ በመቆየቱ ባለፈው አመት በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረገ ጥናት የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በመጀመሪያ ደረጃ የተቀመጠ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ የዩኒቨርሲቲው አይ.ሲ.ቲ ክፍል በራሳቸው ፍላጎት ተነስተው ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ችግር ፈች ምርምር በመስራት ሀምሌ 23 ለምናስመርቃቸው ተማሪዎች ጉልህ ድርሻ ከማበርከት ባሻገር ህዝብንና ሀገርን ለመጥቀም ሰርተው በማቅረባቸው አመስግነዋል ፡፡

በትምህርት ማስተዳደሪያ ስርዓቱ ዙሪያም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አይ.ሲ.ቲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ማሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲያችን ለሀገር የሚጠቅሙ በጣም ትልልቅ ሲስተሞችን በማዳበር እውቅና ያለው መሆኑና ይህም የሆነው በማኔጅመንቱ ጥሩ የሆነ ድጋፍ ስላለ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም የኮቪድ ወረርሺኝን ተከትሎ የተለያዩ ስራዎችን በማበርከት እንደቆዩ አስታውሰው አሁንም ለክልላችን መማር ማስተማር ይውል ዘንድ ትምህርት ቦታ እና ጊዜ እንዳይወስነው የሚያስችል ቴክኖሎጂ አበርክተናል ብለዋል ፡፡

በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲው የተሰራውን የትምህርት ማስተዳደሪያ ስርዓት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እና በቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ገዳም ማንደፍሮ Official Handover of Amahara National Regional State Educational Bureau learning Management System የተሰኘውን ማስተግበሪያ ቁልፍ በአብክመ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ለዶ/ር ይልቃል ከፋለ አስረክበዋል ፡፡

በርክክቡም ከትምህርት ቢሮ ጀምሮ እስከ ተማሪ ወላጅ ሁሉም የትምህርት መዋቀር ተወካዮች ተገኝተውበታል ፡፡

 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ2012 ዓ.ም የተሰሩ ማህበረሰብ ተኮር የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አስመረቀ፡፡ ለዝርዝሩ ቀጣዩን ሊንክ ይከተሉ፡- https://www.facebook.com/bitpoly/posts/1115642688836900

የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ ርክክብ ተካሄደ
********************************************
በሙሉጐጃም አንዱዓለም
ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ለባህር ዳር ከተማ ትምህርትና ጤና መምሪያ “Frances G. Cosco Foundation (FGCF)” /ኤፍ. ጂ. ሲ. ኤፍ./ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ በጐ አድራጐት ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁስ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ርክክብ ተካሄደ።

የመርሐ-ግብሩን መጀመር ይፋ ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፕ/ር የሺጌታ ገላው ለታዳሚዎች የእንኴን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡አክለውም ወቅቱ ሀገራችንን ጨምሮ ሁሉም የዓለም ህዝብ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ፍልሚያ የሚደረግበት መሆኑን ጠቁመው ለተደረገው ድጋፍ በኮሌጁ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ድርጅቱ ከአሁን በፊት ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ሆነ ለሌሎች ተቋማት በርካታ ድጋፍ እንዳደረገና ድጋፉ ወረርሽኙ ከሚጠበቀው በላይ በጨመረበት ወቅት መሆኑ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ አውስተው በሆስፒታሉ ስም ቢሰጥም ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ አገልግሎት እንዳለው በመግለፅ ለወደፊት ቀጣይነት እንዲኖረው አሳስበዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋና አቅርበው ድርጅቱ ከአሁን በፊት “ትምህርት ለለውጥ” በሚል መሪ ቃል ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር አራት ትምህርት ቤቶችን ከተለመደው ወጣ ባለ እና በተሻለ መንገድ እንዲገነባ በማድረግ በርካቶ ከአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በተጨማሪም ሆስፒታሉ መማር ማስተማርን ምርምርን እና የማህበረሰብ አገልግሎትን ሶስቱንም የዩኒቨርስቲውን አምዶች አሳልጦ እየሰራ መሆኑን ም/ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የበጐ አድራጐት ድርጅቱ የአማራ ክልል አስተባባሪ የሆኑት አቶ አብዮት አሸናፊ ድርጅቱ በአማራ ክልል በተመረጡ 5 ዞኖች እንደሚሰራና ለወደፊትም ተደራሽነቱን እንደሚያስፋፋ ገልፀው ከዩኒቨርሲቲው ጋርም በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል።

አስተባባሪው በማከልም የቀረቡት ቁሳቁሶች 11 አይነት እንደሆኑና ለዩኒቨርሲቲው፣ ለባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ እና ጤና መምሪያ ጭምር በገንዘብ ቢተመን ከ6 መቶ ሺህ ብር በላይ ድጋፍ እንዳደረጉ ተናግረው በክልሉ ለሚገኙ ለ14 ትምህርት ቤቶችም 4 ሰዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስታጥብ ከንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ከቁሳቁሶች መካከል ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ባለሙያዎች አልባሳትና ከንክኪ ነፃ የሆነ የሙቀት መለኪያ እንደሚገኙበት አስገንዝበው ለወደፊት ት/ት ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ት/ቤቶች ቢከፈቱ ተማሪዎችን በምን ዓይነት መልኩ ከወረርሽኙ መታደግ እንደሚገባ እንዲሁም የዓይን ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ለማገዝ በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ አስተባባሪው ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሻገር አዳሙ ድርጅቱ በተለይ ትምህርት ላይ መሬት የነካ ስራ በስፋት እየሰራ መሆኑንና 5 ትምህርት ቤቶችን በፍጥነትና በጥራት አስገንብቶ ምቹ ክፍሎችን በመፍጠር አኩሪ ተግባር እንዳከናወነ ተናግረው አሁን ለተደረገው ድጋፍም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ ተወካይ አቶ ተስፋ ሞላ በአሁኑ ወቅት በሃገራችንም ሆነ በከተማችን ወረርሽኙ እየተስፋፋ ባለበትና የመከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት በተከሰተበት ወቅት እርዳታው መድረሱ አስፈላጊ ጊዜ ላይ እንደሆነ አስገንዝበው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ርክክቡ የተካሄደው በድርጅቱ አስተባባሪ አቶ አብዮት እና በዶ/ር ተስፋዬ አማካኝነት ሲሆን የጥበበ ጊዮንን ፕ/ር የሺጌታ፣ የባህር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያን አቶ ተሻገር እና የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያን አቶ ተስፋ ተረክበዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አምስት የትምህርት ተቋማት የችግኝ ተከላ አካሄዱ

በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪነት በሶሻል ሳይንስ እና ሂውማኒቲስ ፋኩልቲዎች እንዲሁም ፣ በትምህርትና ስነ ባህሪ ፣ ሳይንስ እና በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጆች  የሚገኙ መምህራንና ሰራተኞች በቤዛዊት ተራራ የችግኝ ተከላ አካሄዱ፡፡

በመርሃ ግብሩ የሶሳይቲ ፎር ኢኮ ቱሪዝም እና ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን በጎ አድራጎት ሲቪል ማህበር ስራ አስኪሂያጅ ትዝታ የኔአለም እንዳሉት እየለማ ያለው እና በእለቱ ችግኝ የተተከለበት ቦታ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በ225 ሄክታር  መሬት የላንታና  ካማራ አረምን ማስወገድ እና መልሶ ማልማት የ5 ዓመት ፕሮጀክት እየተካሄደበት የሚገኝበት አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ችግኞቹ አገር በቀል የሆኑ እና ሌሎችም የተካተቱበት ሲሆን በየእለቱ ችግኞችን የሚንከባከቡ ጊዚያዊ ሰራተኞች እንዳሉ ገልፀዋል ፡፡ 

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀገራችን የያዘችውን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ የመትከል ሰፊ እቅድ ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎችና ቀናት በ2012 ዓ.ም. ከፍተኛ አመራሮችንና መላውን የዩኒቨርሲቲውን እና በአማራ ክልል የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችንም ያሳተፈ ችግኝ የመትከል  መርሃ ግብር እንዳካሄደ ይታወቃል፡፡

በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በባሕር ዳር ቤዛዊት ተራራ ላይ ችግኝ ተከላ አካሄዱ
======================================================
በሙሉጌታዘለቀ
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ "የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከደለል፣ የአባይን ወንዝ እና የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ እንታደግ” በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና የባህር ዳር ከተማ ም/ከንቲባን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በቤዛዊት ተራራ የችግኝ ተከላ ተካሄደ፡፡

በመርሀ ግብሩ የባሕር ዳር ከተማ ም/ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለከተማዋ እስትንፋሷ መሆኑን አውስተው፣ የጣናንና አባይን ህልውና ለማስቀጠልና ከደለል ለመታደግ ተቋማት በያሉበት ችግኞችን በመትከል የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በተካታታይ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢ ዶ/ር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው ችግኞች ፀድቀው ለተፈጥሮ ሐብት ጥበቃና ለህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያለሙዋቸው ቦታዎች ህብረተሰቡን በባለቤትነት ያሳተፈ መሆን እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ሲናገሩም በጉና ተራራ የተጀመረው የዩኒቨርሲቲዎች የአካባቢ ጥበቃ ስራ በጮቄ ተራራ ቀጥሎ ባህር ዳር በቤዛዊት ተራራ ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ ጉዞውን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ችግኞች መፅደቃቸውን መከታተልና የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲሆኑ ማድረግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚጠበቅ ጠቁመው የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ አንፃር ተከታታይ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

አክለውም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የላንታና ካማራ /የረኛ ቆሎ/ አረምን ከማስወገድ ጀምሮ በርካታ የልማት ስራዎችን ከሶሳይቲ ፎር ኢኮቱሪዝም እና ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን በጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን አውስተዋል፡፡ በቀጣይም በተራራው የኬብል ካር ቴክኖሎጂን በመዘርጋት ለተማሪዎች አገልግሎት የማዋል እቅድ እንዳለው ጠቅሰው በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና የአማራ ክልል አመራሮች ባሉበት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአባይ ወንዝ ላይ ያወጣውን የአቋም መግለጫ አቅርበዋል፡፡

አመራሮች ከችግኝ ተከላው በፊት ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል /STEM Center/ አጫጭር ስልጠና የሚሰጥበትን ተቋም እና የደንገል ልማት ፕሮጀክት ስራዎችን መጎብኘታቸው ታውቋል ፡፡

 

 “የተባበረ ክንድ ጣናን ለመታደግ”

ሰኔ 19/2012 ዓ.ም

በሙሉጌታ ዘለቀ

------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

"ጣናን ለመታደግ የጋራ፣ የትብብርና የፍቅር አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ወደ ጉና" በሚል መሪ መልዕክት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የደብረታቦር፣ የደባርቅ፣ የጎንደር፣ የእንጅባራ እና የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች የጉና-ጣና ተፋሰስ ቦታዎች ላይ ችግኝ ተክለዋል፡፡

 

የችግኝ ተከላውን ሲያከውኑ ዩኒቨርሲቲዎቹ ከጉና ተራራ የሚነሱ ወንዞችና መጋቢ ጅረቶች ተከዜንና ጣናን የሚሞሉ መሆናቸው እና ጉና ተራራን በደን መሸፈን የተፈጥሮ ሃብቶችን ለመጠበቅ ዋስትና መሆኑን መነሻ ያደረጉ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በእለቱም የጉና ተራራ ጣና ተፋሰስ አካባቢን ለማልማት የተደረገ የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓትም ተካሂዷል፡፡

 

በዚህ ታሪካዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ አባይና ጣናን ለማዳን በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዳለ ጠቅሰው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም በከፍተኛ የተፋሰስ ቦታዎች ላይ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንና የጉና ተራራ አካባቢ ተኮር የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ ምርምሮች እየተሰሩ መሆኑን ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

 

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ፣ ከመጤ አረሞች እንዲሁም ከደለል ለመታደግ ዩኒቨርሲቲዎች በተናጠል ከመሆን ይልቅ በጋራ ሁነው የምርምር ስራዎችን መስራታቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ አክለውም የጉና አካባቢ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን መስራት ብሎም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት አካባቢውን የጋራ የምርምር ማዕከል ማድረግ ጊዜው የሚፈልገው መሆኑን ተናግረው የዕለቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የእንቅስቃሴው መነሻ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

 

 

በተጨማሪም በክምር ድንጋይ ከተማ በሚገኘውና በመከላከያ በተገነባው የደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ ምዕራብ እዝ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግኝ ተከላ ተከናውኗል፡፡ 

 

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የተጀመረው የስድስቱ ዩኒቨርስቲዎች የጉና ተራራ አከባቢን የማልማት የችግኝ ተከላ መረሀ ግብር የመጨረሻ መዳረሻውን ጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር በማድረግ ጉብኝት አካሂዷል፡፡

በዚህ ታሪካዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የስድስቱም ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የዞን አስተዳዳሪዎች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

 

 

 

የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዓመታዊ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ
**************************************************************
የዘንዘልማ ግቢ የአስተዳደር ዘርፍ፡- የጠቅላላ አገልግሎት ፣ የተማሪ አገልግሎት፣ የሰው ሃብት አስተዳደር ፣ የግዥና ፋይናንስ አገልግሎት፣ የንብረት አስተዳደር፣ የፀጥታና ደህንነት ክፍሎች ስራቸውን በማቅረብ ዓመታዊ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄዱ፡፡
በመርሃ ግብሩ የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ታደሰ መኳንንት የዕለቱን ዝርዝር ፕሮግራም ያቀረቡ ሲሆን ግምገማው ለቀጣይ በጀት ዓመት የተሻለ ለመንቀሳቀስ እንደመነሻ የሚሆኑ ሀሳቦችን ለማግኘት እና የነገ እቅድን በተሻለ ለመፈፀም ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ኤክስኪዩቲቨ ዳይሬክተር አቶ ገደፋው ሽፈራው በበኩላቸው ሁሉም የስራ ክፍሎች በያዙት ዕቅድ መሰረት ምን ያህል ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን መገምገማቸው ለቀጣይ በጀት ዓመት ጠቃሚ ግብዓቶችን ከማግኘት ባሻገር በሌሎች ግቢዎች ባልተለመደ መልኩ መቅረቡ ይበል የሚያስብል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዋናነት ከተሳታፊዎች ለተነሱ የግቢው የውሃ እና የመብራት ችግርም ዩኒቨርሲቲው ሰባት አሚት ላይ በከፍተኛ ወጭ 5 ጉድጓዶች አስቆፍሮ በሶስቱ ጉድጓድ ላይ ውጤት እያመጣ ስለሆነ በቅርቡ ይፈታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አሳምነው ጣሰው በተገኙበት የተሻለ ስራ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የኮሌጁ ሰራተኞች የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከሶካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በአንድነት በጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ተቋም ድጋፍ የተዘጋጀውን ፐሮጀክት አሸንፈዋል።
****************************************************************************

የፕሮጀክቱ ርዕስ “Eco-engineering for Agricultural Revitalization Towards improvement of Human nutrition (EARTH): Water hyacinth to energy and agricultural crops” የሚል ሲሆን ፕሮጀክቱ ከእንቦጭ ስጋት መጨመር ጋር የተገኘ መሆኑ ወቅቱን የጠበቀ ያደርገዋል፡፡ በሶስቱ ዩኒቨርሲቲዎች ቅንጂት የሚሰራው ይህ ፕሮጀክት በተዘጋጀው አንድ የጥናት ጭብጥ ዙሪያ ለውድድር ከተላኩ ሰላሳ ትልመ ጥናቶች አሸናፊ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ይህ አለም አቀፍ ምርምር በሶካ ዩኒቨርሲቲ (Soka University) መሪነት የሚካሄድ ሲሆን ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር በሚገባበት ጊዜ የተመራማሪዎችን አቅም ከፍ ከማድረግ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዉ በእንቦጭ አረም ላይ እያካሄደ ያለዉን ፈርጀ ብዙ ምርምር ወደላቀ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገዉ ይታመናል። ፕሮጀክቱ ወደ ትግበራ ለመግባት የሁለቱን ሃገራት ስምምነት የሚያሰፈልግ ይሆናል።

Pages