Latest News

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለክቡር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ኦመር ያዘጋጀውን የሜዳሊያና የዕውቅና ሽልማት  አበረከተ፡፡ 

----------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት በ2011ዓ.ም. ባካሔድው የተማሪዎች የምረቃ ስነ-ስርዓት  ላይ  በእንግድነት የተገኙትን የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር  ክቡር  አቶ  ሙስጠፌ  ሙሐመድ  ኦመር የዓመቱ ‘ተስፋ የተጣለበት መሪ’ በሚል ዘርፍ የክብር ሜዳሊያ እንዲሰጣቸው በአንድ ድምፅ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተፈጠሩ አለመመቻቸቶች ምክንያት በወቅቱ ዩኒቨርሲቲው ለክቡር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ኦመር ሊያበረክት ያዘጋጀውን የሜዳሊያና የዕውቅና ሽልማት ማድረስ ያልተቻለ ሲሆን በዛሬው ዕለት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራር በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ ስነ-ስርዓት  ላይ  በመገኘት  በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ አማካይነት የሜዳሊያና የዕውቅና ሽልማቱን አበርክቷል፡፡ በምረቃ 

ስነ-ስርዓቱ  ላይ በመገኘት  ሽልማቱን  የተረከቡት  ክቡር  አቶ  ሙስጠፌ ሙሐመድ ኦመር  የተሰማቸውን ደስታ  የገለፁ ሲሆን ዶ/ር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው የሽልማት መርሐ-ግብሩ ዘግይቶ የተካሄደበትን ምክንያት አብራርተው  ክቡር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ኦመር ከክልላቸው ባለፈ ለአገራችን ኢትዮጵያ በምሳሌነት እያከናወኗቸው ላሉት ተግባራት ምስጋናቸውንና አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ፍሬው አክለውም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን እና አደጋ መከላከልና ዝግጁነትን ጨምሮ በጋራ እየሰሯቸው ስላሉ የትብብር ስራዎች አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም በአገር-አቀፍ ደረጃ ከፀደቀው  የትምሕርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ጋር በሚጣጣም መልኩ የሶማልኛ ቋንቋ በባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ ውስጥ  ቢሰጥ ስለሚኖረው ፋይዳና ይህንንም ለማስጀመር ስለሚቻልበት አግባብ አውስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት በተማሳሳይ የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርትን ያስጀመረ ሲሆን እንደሶማልኛ ቋንቋ ሁሉ ሌሎች አገር-በቀል  ቋንቋዎችን  በቀጣይ የማስከፈት ግቡ አንድ አካል ይሆናል፡፡  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት  ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ትምሕርታቸውን አጠቀናው ለምረቃ ለበቁ የ2012ዓ.ም.  ተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ አላችሁ (Hambalyo) ይላል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ  ለማጥፋት የተጀመረውን ሀገራዊ ዘመቻ ተቀላቀለ

 

በሙሉጌታ ዘለቀ

 

የእንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ለማስወገድ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ የቆየው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ዘመቻ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሩ ቦታው ድረስ በመሄድ አስጀመረ፡፡ 

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እንዳሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሐይቁ ላይ የእንቦጭ አረም  መከሰቱን ለባለድርሻ አካላት ከማሳወቅ ጀምሮ አረሙን ከሐይቁ ለማጥፋት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጠንካራ ስራዎችን መስራቱን ጠቅሰው ለዚህም የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት  የመካኒካል ምህንድስና መምህራን ዲዛይን በመስራትና የሙላት ኢንጂኒየሪንግ የእንቦጭ መሰብሰቢያ ማሽን ማምረቱን አስታውሰው ላደረጉት መልካም አስተዋፃ  ምስጋና አቅርበዋል፡፡  ዶ/ር ፍሬው አክለውም ከዘመቻው ባሻገር ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የእምቦጭ አረም በዘላቂነት እንዲወገድ ከተፈለገ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ከዘመቻ ባለፈ በቋሚነት በመናበብ መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው  የእንቦጭ አረምን ከሀይቁ ለማስወገድ በዘመቻ የሚሰሩ ስራዎች ውጤት እንደማያመጡ በመገንዘብ በቋሚነት በርካታ የሰው ሀይልን እና  ማሽኖችን በመጠቀም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሰው ሃይል አረሙን በማስወገድ ሂደት ለሚያጋጥሙ ማንኛውም ጉዳቶች  በቦታው ሀኪሞችን በመመደብና  ቋሚ የማረፊያ ቤቶች እንዲሰሩ  ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ቦታው ድረስ በመገኘት በጉዳዩ ላይ  መምከሩን ተናግረዋል፡፡

 

ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም የእንቦጭ አረም የሀይቁን 4300 ሄክታር የሽፈነ ሲሆን አረሙን የማስወገድ ዘመቻው ሽሃ ጎመንጌ ቀበሌ መጀመሩን ጠቅሰው አፈፃፀሙ እየታዬ ስራው በአስሩም ቀበሌዎች እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡

 

አረሙን የማስወገጃ ቦታዎችን በመምረጥ በማከማቸት አድርቆ ለገበሬው ማሳ ኦርጋኒክ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ምርምር እየተደረገበት መሆኑን በዘመቻው ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

 

ለመምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ዳይሬክቶሬት ለዩኒቨርሲቲው መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች በ Leadership and Change Management ፣ Statistical Package for Social Science ( SPSS )፣ Payton Programming  እና በግዢና ንብረት አስተዳደር የሙያ ዘርፎች  ስልጠና ሰጠ ::

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አበበ እንደተናገሩት በአስተዳደር ሰራተኞች በኩል የዝቅተኛና የመካከለኛ አመራሮችን በራስ የመወሰን አቅማቸዉን ለማጎልበት ያመች ዘንድ በማዕከላዊና በተለያዩ ግቢዎች ለሚገኙ አመራሮች በ Leadership and Change Management ዙርያ ለ4 ቀናት ፣በግዢና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በኩል ደግሞ በሁሉም ግቢ ለሚገኙ የንብረት አስተዳደር ሰራተኞች ንብረትን በሲስተም እንዴት ማስተዳደርና መጠቀም እንደሚቻል በተግባር የታገዘ ለ2 ቀናት ስልጠና መሰጠቱን ገልፀውልናል፡፡

አያይዘውም የስልጠና ዳይሬክቶሬቱ በዘንዘልማ ግቢ ለሚገኙ መምህራን የምርምር ስራቸዉን በተገቢዉ ለመስራት ያመቻቸዉ ዘንድ ከስታትስቲክስ ትምህርት ክፍል አሰልጣኞችን በማስመጣት Statistical Package for Social Science ( SPSS ) ለ 5 ተከታታይ ቀናት ስልጠና የተሰጣቸዉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በሂሳብ ትምህርት ክፍል Payton Programming ስልጠና ለተከታታይ አምስት ቀናት ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል ፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ሰዓት በሁሉም ዘርፍ ከ 03-09/02/2013 ዓ/ም ድረስ 154 የሚሆኑ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ስልጠናዉን በተገቢዉ መንገድ ተከታትለዉ ማጠናቀቃቸዉን የዩኒቨርሲቲዉ የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ወርቁ አበበ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን፣ የሐኪሞች ሙሉ ልብስ ማምረቻን ጎበኙ።

........................ ........................ ................................................

 

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሔራን ገርባ ከሌሎች የመስሪያ ቤቱ ባለስልጣናት ጋር በመሆን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፣ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፍሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ስር የሚገኘውን የሐኪሞች ሙሉ ልብስ (Coverall) ማምረቻና ማስተማሪያ ፍብሪካ ጎብኝተዋል። በጉብኝቱም  በተሰጠው የጥራት ዕውቅና መሰረት እያመረተ መሆኑንና በቀን እስከ 400 የሐኪሞች ሙሉ ልብስ የማምረት አቅም እንዳለው መረዳት ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የመንግስት እና የግል ሆስፒታሎች ምርቱን ወስደው እየተጠቀሙ ሲሆን፣ እንዲመረትላቸው ጥያቄ ያቀረቡ እንዳሉም ማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሔራን ገርባ በተቋሙ እየተሰሩ ያሉ  ስራዎች አበረታችና ለሌሎች ተምሳሌት መሆናቸውን ገልፀው፣ወደፊትም መስሪያ ቤቱ ማንኛውም ሙያዊ እገዛ እንደሚደረግላቸውና፤ ሌሎች በላብራቶሪ ደረጃ ላይ ያሉ ምርቶችም ለሀገር ጠቃሚና የውጭ ግዥ የሚያስቀር መሆኑን ገልፀው፣ መስፈርቶችን ሲያሟሉ ለመስሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፍሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የእውቅና ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችል ገልፀዋል።

 

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የግምገማና ክትትል ቡድን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመቀበል እየሰራ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ስራ ገመገመ

-----------------------------------------------------------------------------------------------------

በሙሉጌታ ዘለቀ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ኮቪድ-19ን በመከላከል ትምህርት ለመጀመር  ዩኒቨርሲቲዎች ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ  የኮቪድ 19 ኘሮቶኮልን ተከትሎ የተማሪዎች መኝታ ቤት፣ የመመገቢያ አዳራሾች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራዎች እና የተማሪዎች መዝናኛዎች በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የተሰሩ ስራዎችን ገምግሟል፡፡

 

እንደሚታወቀው በሀገር አቀፍ ደረጃ ባሳለፍነው የትምህርት ዘመን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተማሪዎቻችን ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው ቆይተዋል፡፡ በያዝነው ዓመት ወረርሽኙን በመከላከል ዩኒቨርሲቲዎች  ትምህርት ለማስቀጠል የሚያሰችል ደረጃ ላይ መሆናቸውን  ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስተር የተላከ የሱፐርቪዥን ቡድን እያረጋገጠ ይገኛል፡፡

 

 በመሆኑም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች የኮረና ቫይረስ ቅድመ መከላከል ስልጠናና ምርመራ ማድረጋቸውን፣ ተማሪዎች ሲገቡ የሚኖራቸው መስተጋብር ምን መምሰል እንዳለበት ዩኒቨርሲቲው በስምንቱም ግቢዎች ያደረገውን ቅድመ ዝግጅትና የተሰሩ ስራዎችን  የግምገማና ክትትል ቡድኑ ተመልክቷል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሰራውን የመንጃ ፍቃድ መረጃ  አያያዝ ዘዴ( Driving License Information Management System) አስመረቀ

በወንዳለ ድረስ

በኢንስቲትዩቱ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ  ትስስር እና ማህበረሰብ  አገልግሎት  ጽ/ቤት ድጋፍ  የማህበረሰቡን  ችግር

ለመፍታት የተሰራውን Driving License Information Management System ቴክኖሎጂ ባለድርሻ

አካላት በተገኙበት መስከረም 30/2013 ዓ.ም አስመርቋል፡፡

 

በምረቃ ስነ ስርዓቱ  አቶ ቴዎድሮስ ጌራ በኤሌክትሪካል  እና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ  ፋኩልቲ  ዲን  በመክፈቻ

ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና ምርምር ተልኮዎች ባሻገር በተለያየ

ወቅት ዘርፈ ብዙ ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ ለተለያዩ ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ  ማስረከቡን  አስታውሰዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴከኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኤሌክትሪካል እና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ፋኩልቲ የሚሰሩት አቶ አማረ ካሳው ቴክኖሎጂውን ሲያስተዋውቁ እንደተናገሩት የመረጃ አያያዝ ዘዴው  የመንግስት  ገቢን  ለማሻሻል፣  የትራፊክ  አደጋን  ለመቀነስ ፣ የተቋሙን አፈፃፀም  ለማሻሻል፣  የሥራ  አፈፃፀሙን  ለማስተዳደር  እና  ለመቆጣጠር የራሱን እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀው ቴክኖሎጂው የሥልጠና  ተቋማቱን የሚደግፍና ለአሽከርካሪዎች አገልግሎቱን ቀላል በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፆ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

 

በመጨረሻም የአብክመ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ውቤ አጥናፉ እና የባህር ዳር ከተማ መንገድ

ትራንስፖርት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ  የመንጃ ፍቃድ ስርዓቱ በሚሻሻልበት መንገድ ዙሪያ በክልሉ ከሚገኙ

የዞን መንገድ ትራንስፖርት ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

 

                    ተማሪዎችን ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ስልጠናው እንደቀጠለ ነው

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ዳይሬክቶሬት በ2013 ዓ/ም የተማሪዎችን ቅበላ ምክንያት በማድረግ በተላያዩ ክፍሎች ለሚሰሩ የተማሪዎች አገልግሎት ሰጭ የአስተዳደር ሰራተኞች የጀመረውን ስልጠና አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ወርቁ አበበ በስልጠናው ዙሪያ በሰጡት ገለፃ በሁሉም ግቢ ለሚገኙ የምግብ ቤት አስተናጋጆች ስለደንበኞች አገልግሎት፣ በዋናዉ ግቢና ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ለሚገኙ ለጸጥታና ደህንነት ሰራተኞች በደንበኞች አገልግሎትና ጥበቃ፣ በሁሉም ግቢ ለሚገኙ ፕሮክተሮችና የጽዳት ሰራተኞች በወቅታዊው  የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ዓለምአቀፋዊ እና ሀገራዊ ሁኔታ፣ ስለ መተላለፊያ መንገዶችና መወሰድ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ተገቢ የሆኑ ባለሙያዎችን በማስመጣት ስልጠና እየሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አቶ ወርቁ እንዳሉትም ሰራተኞቹ በስልጠናው የሚያገኙትን እውቀት ካላቸው ሰፊ ልምድ ጋር በማስተጋበር ተማሪዎች በሚመጡበት ወቅት እንደ ልጆቻቸው ወይም እንደ ቤተሰብ አባላቸው እንዲያስተናግዷቸው አደራ ብለዋል፡፡

በስልጠናው ያገኘናቸው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከስልጠናዉ ከፍተኛ የሆነ ዕዉቀትና ግንዛቤ በማግኘታቸዉ መደሰታቸዉን በመግለጽ በሰለጠኑበት አግባብ ደንበኞቻቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ከ1087 የማያንሱ በተለያየ ዘርፍ የሚሰሩ የአስተዳደር ሰራተኞች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋኩሊቲ ለፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የመታሰቢያ መርሀ ግብር አካሄደ፡፡

በትዕግስት ዳዊት

በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በተለይም በጂኦግራፊ የትምህርት መስክ፣ በሀገራችን ፖለቲካ እና በርከት ያሉ ተግባራትን በመከወን ዘመን የማይሽረው አስተዋጽ አበርክተው እና አሻራ ትተው ያለፉትን ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን በጥቂቱ ለመዘከር የተደረገ መርሀ ግብር መሆኑን መርሀ ግብሩን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የፋኩልቲው ዲን ዶ/ር ቃለወንጌል ምናለ  ተናግረዋል፡፡

 

ደ/ር ቃለወንጌል አክለውም ወደፊት የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን ጨምሮ የሌሎችንም በተለያየ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ለሆኑ የአንጋፋ ምሁራን ስራዎች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ መርሀ ግብሮች፣ እንዲሁም ውይይቶችን በሰፊው እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

በማስከተል የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም አጭር የህይወት ታሪክ በዶ/ር አረጋ ባዘዘው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ቀርቧል፡፡

የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የቀድሞ ተማሪ የነበሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ፈረደ ዘውዱ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የአስተማሪነት ዘመን ትዝታቸውን ያካፈሉ ሲሆን ፕሮፌሰሩን ሀገር ወዳድ፣ ለወገን ተቆርቋሪና ጀግና ምሁር ሲሉ አውስተዋቸዋል፡፡

በተጨማሪም ዶ/ር ጥጋብ በዜ እና ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም በህይወት ዘመናቸው ስላበረከቷቸው ታሪክዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበረሰባዊ ይዘት ስላላቸው መጽሀፍት፣ ስላዘጋጇቸው የማስተማሪያ መጻህፍት እንዲሁም ስለ ማህበራዊ ህይወታቸው የሚዳስስ ወረቀት አቅርበዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ዘመን ተሸጋሪው የአደባባይ ምሁርና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች መሆናቸውም ተወስቷል፡፡

በመርሀ ግብሩ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የቀድሞ ተማሪዎች፣ የስራ ባልደረቦች፣ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ታድመዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ መክፈቻ የሻማ ማብራት ስነ-ስርአት እንዲሁም የሁለት ደቂቃ የህሊና ጸሎት በሊቀ-ህሩያን በላይ መኮኘን የተደረገ ሲሆን በመጨረሻም የደራሲያን ማህበር ባህር ዳር ቅርንጫፍ ፕሬዚዳት የሆኑት ሊቀ-ህሩያን በላይ መኮንን የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን ህልፈት አስመልክተው አጠር ያለ ግጥም አቅርበዋል፡፡

 

 

 

የማስክ/ጭንብል/ የቤት ውስጥ አዘገጃጀት እና አጠቃቀም የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሠጠ ነው

ትዕግስት ዳዊት

 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ መምህራን እና FGCF ከተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት በመጡ አሰልጣኞች የተዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና ባሕር ዳር ዙሪያ ከሚገኙ 63 ት/ቤቶች ለተወጣጡ ፍላጎቱ ያላቸው 126 መምህራን እየተሰጠ ሲሆን ከጥቅምት 25 ጀምሮ እስከ 28 እንደሚቀጥል ተነግሯል፡፡

ከዚህ ስልጠና በኋላ ኋሰልጣኞች በሚያስተምሩባቸው ት/ቤቶች ለሚገኙ ስልጠናውን ላልወሰዱ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ለተማሪ ወላጆች እንደሚሰጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

FGCF ከተባለው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ስልጠናውን ለመስጠት የመጡት ሲ/ር ማርናት አዱኛ እንዳሉት በኮሮና ምክንያት ተዘግተው የነበሩት ትምህርት ቤቶች በቅርቡ የሚከፈቱ በመሆናቸው የኮሮናን አደጋ ለመቀነስ እንዲቻል መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ሲ/ር ማርናት  አክለውም ተማሪዎችና መምህራን ወጭ ሳያወጡ ቤት ውስጥ በሚገኙ ባገለገሉ ልብሶች ጭንብል ማዘጋጀት እንዲችሉ የሚያስችል ውጤታማ ስልጠና እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ከማስክ/ጭንብል/ አሰራር በተጨማሪ ሲ/ር ማርናት ስለኮሮና ቫይረስ (COVID _19) መተላለፊያ እና መከላከያ መንገዶች ለሰልጣኞች አስረድተዋል፡፡

ሜጫ ወረዳ በወተት አባይ ት/ቤት መምህር የሆኑት መምህር ሽባባው አስማረ የስልጠናውን ጠቃሚነት አብራርተው ወጭ ቆጣቢና ማንም ሰው አገልግሎት ከሰጡ ጨርቆች ማዘጋጀት የሚችለው መሆኑን እና ያገኙትን እውቀትም ለሌሎች እንደሚያጋሩት አያይዘው ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ ከፍርን የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ት/ቤት የመጡት መምህርት ማለፊያ ልየው ከስልጠናው ስለኮሮና ቫይረስ (COVID _19) ምንነት፣ መተላለፊያ መንገዶች፣ በቁሶች ላይ ለምን ያክል ጊዜ እንደሚቆይ እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል/ማስክ/ በቤት ውስጥ እንዴት እንደሚዘጋጅና አጠቃቀሙን በተመለከተ ሰፊ እውቀት ማግኘታቸውን አጋርተውናል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ውይይት ተካሄደ ፡፡

የአገሪቱን የአሳ ግብርና ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ለማስጀመር Advancing Climate Smart Aquaculture Technologies (ACliSAT) በሚል ርዕስ ከመስከረም 22-23 አውደ ጥናት ተካሄደ፡፡ በአውደ ጥናቱ  በዋነኛነት የፕሮጀክቱን ትግበራ ማስጀመር በሚቻልባቸው፣ በትብብር መስራት በሚያስፈልግባቸው ጉዳዮችና በአጠቃላይ የአገሪቱን የአሳ ግብርና ማሳድግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የሚያተኩሩ ጥናታዊ ፁሁፎች ቀርበው፣ ሰፊና ገንቢ ውይይት ተደርጓል፡፡  

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋየ ሽፈራው  ዩኒቨርሲቲው ዘንዘልማ በሚገኝው ካምፓሱ ከቅድመ ምረቃ እስከ ፒኤችዲ ደረጃዎች በአሳ ልማት ዘርፍ ትምህርት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋየ አክለውም ጣና ሀይቅ አካባቢ የአሳ ሀብታችንን በተሻለ መንገድ ለመጠበቅ የሞዴል ፋርም ተገንብቶ ለስልጠና እና የአሳ እርባታን ለማዘመን እየተሰራ ቢሆንም በሃገሪቱ ፈጣን የህዝብ ብዛት፣ ከፍተኛ የወጣት ሥራ አጥነት መጨመር እና ከተጋረጠብን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ሲነፃፀር ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በላይ መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዋሴ አንተነህ በበኩላቸው የእለቱ አውደ ጥናት ዋና አላማ የአሳ ግብርናን በኢትዮጰያ ማስፋፋት በሚቻልበት ዙሪያ በIFAD እና WorldFish ድጋፍ የሚተገበረውን ፕሮጀክት በማስጀመር ከአጋር አካላት ጋር ውይይት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ 

ዶ/ር ዋሴ ፕሮጀክቱ ኤርትራና ግብፅን እንደሚያካት ጠቁመው፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም በኢትዮጵያ ያለውን የውሃ ልማት በተመለከተ ማንኛውም እንቅስቃሴ እንዲያስፈፅም ተወከሎ እያስተባበረ ይገኛል ብለዋል፡፡

 

Pages