Latest News

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት /ISSD/ ክልላዊ አውደጥናት አካሄደ!!

=======================================================
 

በሙሉጌታ፡ዘለቀ
የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማትፕሮጀክት /ISSD/ እስካሁን የመጣበትን የስራ ዘመን ለመገምገምና በቀጣይነቱ ላይም ለመምከር በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋራ ውይይቱን በባህር ዳር ከተማ አካሄደ፡፡

ዶ/ር ደረጀ አያሌው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት /ISSD/ ዋና ዳይሬክተር (ISSD Project Coordinator) በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት የአውደ ጥናቱ ዋና አላማ እስካሁን የተሰሩ ስራዎችን ለመገምገምና ፕሮጀክቱ ከስድስት ወር በኋላ የስራ ጊዜውን የሚያበቃበት ወቅት በመሆኑ ይህ ፕሮጀክት ሲሰራቸው የነበሩትን ስራዎች በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት እና የፕሮጀክቱ የቅርብ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንዳሉት የሀገራችንን የግብርና ምርትን ውጤታማ ለማድረግ ከበሽታ የነፃና በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት ሊሰጥ የሚችል ምርጥ ዘር ወሳኝ መሆኑን ተናግረው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በየጊዜው በዚህ ዘርፍ ከሚሰሩ ፕሮጀክቶች ጋር ከሚያደርገው ግንኙነቶች ውስጥ አንዱ የISSD ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ፕሮጅክት የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ግንዛቤን ከፍ ያደረገና ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎችን ያመጣ ብሎም የተገበረ እንዲሁም በቀጣይነቱ ዙሪያ እየሰራ ያለ እንደሆነ  ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግዙፍ ተቋም እንደመሆኑ ISSD Project እስካሁን የሰራቸውን ስራዎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የግንዛቤ ፈጠራና ምርጥ ዘርን የማዳረስ ስራን በስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ይህ ጉባኤ ለወደፊቱ በምርጥ ዘር ላይ ቋሚ ስራ ለመስራት በምን መልኩ መሄድ እንደሚገባ መክሮ የተጀመሩ ስራዎችን ከግብ ማድረስ እንደሚገባ በአፅኖት ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የስራ ጊዜው ቢጠናቀቅ እንኳን የአማራ ክልል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ዩኒቨርሲቲዎቸ /እና አጋር ተቋማት ይህንን በጎ ስራ ማስቀጠል እና አርሶ አደሩን የተለያዮ ስልጠናዎችን በመስጠትም ሆነ ምርጥ ዘር በማቅረብ መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የISSD ፕሮጀክት የእሴት ሰንሰለት ባለሙያ የሆኑት አቶ መስፍን አስታጥቄ  ለጉባኤው ተሳታፊ እንዳሉት ባሳለፍነው አስር ዓመት በዋናነት የተመረጠና በምርምር የተገኘ ጥራት ያለው  ዘርን ወቅቱን ጠብቆ በተፈለገው መጠን ለአርሶ አደሩ እንዲደርስና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘዬ ለመቀየር እንዲሁም ኢኮኖሚን ለማሳደግ አልሞ መስራቱን ተናግረዋል። የፕሮጀክቱን የአስር አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርትም አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም በፕሮጀክቱ  የተገኙ ጠንካራና ደካማ ጐኖችን በማንሳት ውይይት የተደረገ ሲሆን ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም ተሳታፊዎቸ አስቀምጠዋል፡፡  ይህንን ፕሮጀክት የማስቀጠል ስራ የዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን የሌሎች ባለ ድርሻ አካላትም እንደሆነ ተገልጿል፡፡  በውይይቱ ላይ  የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በተለያ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ ቢሮዎች የተጋበዙ እንግዶች እንዲሁም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዚደንትን ጨምሮ ዳይሬክተሮች እና ሌሎች ምሁራን ተገኝተዋል፡:

በሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች መማር ማስተማር ላይ ያተኮረ አለማቀፍ አውደ ጥናት ተካሄደ !!
====================================================
በሙሉጌታ ዘለቀ
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ስነ-ባህሪ ኮሌጅ ከNORHED PROJECT ጋር በመተባበር በሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች መማር ማስተማር ላይ ያተኮረና የተለያዩ የምርምር ፁሁፎች የቀረቡበት ለሁለት ቀናት የቆየ አለማቀፍዊ አውደጥናት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የNORHED PROJECT ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዳዊት አስራት በአውደጥናቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች ተማሪዎች ያላቸው ፍላጎትና ዝንባሌ መቀነሱን ጠቅሰዋል፡፡ ዶ/ር ዳዊት ቀጥለውም በአውደ ጥናቱም በችግሩ ዙሪያ በታዋቂ ሙሁራን የተሰሩ ጥናታዊ ፁሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ጠቅሰው ይህም በሀገራችን የሳይንስና ሒሳብ ትምህርት ላይ የራሱ የሆነ አውንታዊ ተፅእኖ እንደሚያሳድር እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
 
አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እንዳሉት የሀገራችንን መማር ማስተማርን ለማዘመንና በትምህርቱ ዘርፍ የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ በሙያው ውስጥ ያለን ሙሁራን እንደዚህ ያለ አለማቀፍ አውደጥናቶችን በማዘጋጀት አለማቀፍ የሆኑ የተለያዩ የምርምር ፁሁፎች እንዲቀርቡና ክርክር እና ውይይት እንዲደረግባቸው ማድረግ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
በመድረኩ ላይ ከቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች መካከል የእንግሊዝ ሀገሩ የሒሳብ ተመራማሪና ሙሁር የሆኑት ፐሮፌሰር ፓውል ኢርነስት “Mistakes in Mathematics and Learning” በሚል ርእስ እና ኢትዮጵያዊው ሙሁር ዶ/ር ተመቸኝ እንግዳ «Science education: issues and trends” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፁሁፎች ቀርበው በአውደጥናቱ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች በጥናት አቅራቢዎች ግብረ-መልስ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በሀገራችን የሳይንስና ሒሳብ መማር ማስተማር ስልጠና የሚሰጠው በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ብቻ በመሆኑ ተማሪዎች ትምህርቱን ከመውደድ ይልቅ ትምህርቱን መጥላትና መሸሻቸው በውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተፅኖ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ይህንን ቸግር ለመከላከል በሙያው የሰለጠኑ መምህራን ተጨማሪ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ተማሪዎች የሳይንስና የሒሳብ ትምህርቶችን በሚያዝናና እና በጨዋታ መልክ እንዲከታተሉ ቢደረግ በሂደት በመማር ማስተማሩ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ በአውደጥናቱ ላይ ተጠዉሟል፡፡ በአውደጥናቱ ላይ ከሃያ ሰባት በላይ ጥናታዊ ፁሁፍች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
 
በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብይ መንክር ለአውደጥናቱ ተሳታፊዎች የመዝጊያ ንግግርና ለጥናታዊ ፁሁፍ አቅራቢዎች የእውቅና የምስክር ወረቀት በሰጡበት ወቅት እንዳሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ይህ አለማቀፍ አውደጥናት ከተለያዩ የአለማትን ክፍሎች ያሉና በሙያው ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ሙሁራን የተሳተፉበት በመሆኑ ለራዕያችን መሳካት መድረኩ ጠቋሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ መድረኮች ችግሮቻችን የሚጠቁሙና መፍትሄም የሚያፈልቁ በመሆኑና ዩኒቨርሲቲያችንም ከፍተኛ ልምዶችን የሚያገኝበት በመሆኑ የሚበረታታ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
 
በምክክር መድረኩ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የውጭ ሀገር ሙሁራን፣ የትምህርት ቢሮ ሀላፊዎችና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከ26 ሺ በላይ መፅሀፎች በዕርዳታ አገኘ
==================================
በሙሉጌታ ዘለቀ
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር ካደረገው ቡክስ ፎር አፍሪካ ከተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር ባደረገው ግንኙነት የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ፣ የስነ-ፁሁፍ እና የማህበራዊ ሳይንስ ይዘት ያለቸው መፅሀፎችን በዕርዳታ ተረክቧል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብይ መንክር በመፅሀፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት መፅሀፎቹ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት በሆኑት ዶ/ር እሰይ ከበደ ከቡክስ ፎር አፍሪካ ጋር በመፃፃፍ የመጡ መሆናቸውን ገልፀው፤ መፅሀፎችን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያስመጣቸው እንጂ ከምርምሩ በተጨማሪ ህብረተሰቡን ከሚያገለግልበት ሂደቶች ውስጥ አንዱ የማህበረሰብ አገልግሎት በመሆኑ በባሕር ዳርና አካባቢዋ ለሚገኙ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና ከፍተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፋፈሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ አብይ አክለውም እነዚህን መፅሀፎች በማጓጓዝና የትራንዚት ክፍያዎችን በመክፈል ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ድረስ እንዲመጣ ያደረጉ ካፒቴን አንተሁነኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አቶ አብይ ካፒቴን አንተሁነኝን አመስግነው ሌሎች ሀገር ወዳድ ባለሀብቶችም የሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ መክረዋል፡፡
 
ቡክስ ፎር አፍሪካ የተሰኘው ድርጅት የተለያዩ መፅሀፎችን አሜሪካን ሀገር ካሉ ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት እያሰባሰበ ለተለያዩ አፍሪካ ሀገራት በእርዳታ የሚያበረክት ግብረ-ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ መፅሀፎች ከ1ኛ - 4ኛ ክፍል፣ከ5ኛ- 8ኛ፣ ከ9ኛ-12ኛ እና ለጎልማሶች ትምህርት የሚያገለግሉ ከ26ሺህ በላይ የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ፣ የስነ-ፁሁፍ እና የማህበራዊ ሳይንስ ይዘት ያለቸው መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

ፕሮግራሙ የአርሶ አደሮችን የመስክ ቀን በደመቀ ሁኔታ አከበረ

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ደብረ መድሀኒት ቀበሌ የአርሶ አደሮችን የመስክ ቀን የተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት አከበረ::

መርሃ-ግብሩ በይፋ መከፈቱን ያበሰሩት የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አዳሙ ሲሆኑ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች አማካኝነት ለወረዳው ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም የወረዳው አርሶ አደሮች በመጡት አዳዲስ ዘሮች ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

የፕሮግራሙ ማናጀር ዶ/ር አልማዝ ጊዜው ቤነፊት ሪያላይዝ ምን ምን ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ በሰፊው አብራርተዋል፡፡በተጨማሪም የበዓሉ ዋና ዓላማ የተሰሩትን ስራዎች በመገምገም ጠንካራና ደካማ ጎኖችን አውጥቶ የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ ለመለየትና ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ታልሞ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ማናጀሯ በማስከተልም ፕሮግራሙ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸው ወረዳዎች የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡት ላይ ስለሆነ በበዓሉ ከታደሙት አርሶ አደሮችም ሆነ የግብርና ባለሙያዎች በርካታ ግብዓት ማግኘት እንደሚቻል ሙሉ እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ሰፊ የመስክ ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን በተለያዩ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ የተሞከሩትን ሶስት አይነት አዳዲስ የስንዴ ዝርያ ቴክኖሎጂ ሙከራዎችን ማለትም አሳታፊ የተሻሻሉ የስንዴ ዘር መረጣ፣ የስንዴ ሰርቶ ማሳያ እና የ1000 ብር የስንዴ ፓኬጅ ቴክኖሎጂ ሙከራ በጉብኝቱ ተዳሰዋል፡፡ የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች በታየው ለውጥ መደሰታቸውንና ለወደፊት ምርትና ምርታማነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ሰፊ የመስክ ጉብኝት ከተካሄደ በኋላ በአብክመ ግብርና ምርምር ተቋም ም/ዳይሬክተር ዶ/ር ኤርሚያስ አባተ፣በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሽመልስ አይናለም እና በአቶ መለሰ አዳሙ በመሩት ድረክ  የጉብኝቱ ውሎ በሰፊው ተዳሶ  ከአርሶ አደሮችና ከባለሙያዎችም ገንቢ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡

የማጠቃለያውን ንግግር ያደረጉት የአብክመ ምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አማረ ክንዴ ሲሆኑ የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ ወረዳዎች ላይ የሚሰራው ስራ ይበል የሚያሰኝና የሚበረታታ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ለተመደቡ አዲስ ተማሪዎች የሞቀ አቀባበል ተደረገላቸው!!

በሙሉጌታ ዘለቀ

በ2012 ዓ.ም ለተመደቡ አዲስ  ተማሪዎች የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በዋናው ግቢ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ትምህርት ለመቅሰም የተሰባሰቡ አዲስ ተማሪዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ እነዚህን አዲስ ተማሪዎች ለመቀበል ደፋቀና ያሉ የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶችን እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላትን አመስግነዋል፡፡ ተማሪዎች ከወላጅ ቤተሰቦቻቸው ርቀው ይምጡ እንጂ በተጨባጭ ግን ወደሌላኛው ቤታቸው ወይም ወደ ወገናቸው፣ ወንድም እህታቸው የመጡ መሆናቸውን መገንዘብ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡  

ዶ/ር ዘውዱ አክለውም ዛሬ ዓለም የኋላቀርነት ምልክት አድርጎ የተጠየፈውን የመለያየት በሽታ እኛ ኢትዮጵያዊያንን በማይመጥነን ደረጃ ወርደን ከመቀራረብና በትግሮቻችን ላይ ከመነጋገር  ይልቅ ስለሰፈር ማሰብ ጀምረናል፡፡ ያም ሆነ ይህ የሁሉም ችግሮቻችን መፍቻ እውቀትና ክህሎት ማመንጫ የሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን የነዚህ የወረዱ አመለካከቶች ማራመጃ መሆን እንደሌለባቸው በአፅኖት ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ዘውዱ በንግግራቸው መቋጫም እኛ ተማሪዎች ነን እንማር እንወቅ ፣ያልገባንን እንጠይቅ፣ የሚጠቅመንን ለይተን እንያዝ፣ እኔ የተሻልኩ ነኝ የሚል ቢኖር ነውር ነገር ባለማድረግ መሻሉን ያሳይ እሳት በውሃ እንጂ በእሳት አይጠፋም ክፉውን ነገር በክፉ ከመፍታት ይልቅ በበጎ መፍታት ባህላችን እናድርግ በማለት ተማሪዎች በጋራ ለመማማር ብቻ እዲሰለፉ መክረው  ዓመቱ መልካም የትምህርት ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን  አስተላልፈዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በ2012 ዓ.ም. ለተመደቡ አዲስ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ደረጃ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ያለ ትልቅ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም እንደማሳያ በሀገራችን ካሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያልተካተተ/የማይሰጥ የማሪታይም አካዳሚ ከፍቶ ከ1500 በላይ ተማሪዎችን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ ስምና ዝና ያገኘ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ዶ/ር ፍሬው አክለውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እሴቶች ፡- ዕውቀትን እና ጥበብን ፍለጋ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን የልዕቀት ማዕከል ማድረግ፣ ብዝሀነትን ማክበር፣ አለማቀፋዊነት እና ህብረተሰብን ማገዝና መደገፍ ለተማሪዎች አብራርተዋል፡፡ በንግግራቸው ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸው ጥላቻን ከሚፈጥሩ ማንኛውም ነገር ተቆጥበው የዩኒቨርሲቲውን ህግና ደንብ አክብረው ትምህረታቸውን እንዲማሩ አሳስበዋል፡፡

 የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ መምህርና የወልደያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ ለአዲስ ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ እኪገቡ ያለውን የሂዎት ውጣውረድና ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ያጋጠማቸውን የሂዎት ተሞክሮዎቻቸውን ለተማሪዎች አካፍለዋል፡፡ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ውጤት ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ብቻ የሚያገለግል መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ያለው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተማሪዎች ብዙ ውጣውረድና ፈተናውችን በማለፍ ስኬት ላይ መድረስ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ አለም ወደ አንድ መንደር እየመጣች ባለችበት ሰዓት  በዘርና በቋንቋ ከሚከፋፍሉ እኩይ ባህሪ ካላቸው ግለሰቦች እራሳቸውን በመጠበቅ ለቤተሰብ እንዲሁም ለሀገር የሚበጅ እውቀት ይዘው እንዲወጡ መክረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዩች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብረሀኑ ገድፍ ለተማሪዎች በግቢ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ በሚያገኟቸው የምግብ፣ የመኝታ፣የውሃ፣ የመብራት፣ የመዝናኛ እና ሌሎችም አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ አሟልቶ ለተማሪዎች ለማቅረብ ደፋ ቀና ሲል መቆየቱን ጠቅሰው ማንኛውም ተማሪ በምንሰጣቸው አገልግሎቶት የጥራት ማነስ ቢኖር እንኳን በመነጋገር ችግሮችን እንደሚፈቱ አቶ ብርሀኑ ተናግረዋል፡፡ የአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስርዓተ ፆታ ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ብርሃኔ መንግቴ ለአዲስ ተማሪዎች ማንኛውንም ችግር ሲገጥቸው በሁሉም ግቢዎች በተቋቋሙት የስርዓተ-ፆታ ቢሮዎች መገልገል እንደሚችሉ ተናግረው በተለይ አዲስ ለተለመደቡ ተማሪዎች በሚቀጥሉት ሦስት ቀናት የህይወት ክህሎት ስልጠና እደሚሰጥና ስልጠናውንም ሁሉም አዲስ ተማሪዎች እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የሆነው ተማሪ አደባባይ ጋሻው እንዳለው  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት የተማሪዎችን መብት በማስጠበቅ በአገልግሎት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ይፈታል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ተማሪ ሰላምን ከማይወዱና የተለዬ አላማ አንግበው ለሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች መጠቀሚያ እንዳይሆኑና ትምህርታቸው ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡      

ዩኒቨርሲቲው በመሬት አጠቃቀም የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በምርምር ታግዞ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ::
የዜናውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ቀጣዩን ሊንክ ይጫኑ፡ https://www.ena.et/?p=61010

A delegation of the University of Applied Sciences from Germany and of GIZ from Addis Ababa visit BDU.

During their visit and the discussion held therewith, several possible partnership areas have been assessed. Among many strategic partnership programs, a Joint Masters in Agricultural Management which will involve staff and student exchange has particularly been highlighted as one of the feasible areas of cooperation and partnership. It is presumed that MoU shall be signed in the near future.

                     የተሻሻለ ሰብል ዝርያ በሰርቶ ማሳያ የመስክ ምልከታ ተደረገ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት በታች ጋይንት ወረዳ ቆጥ መንደር የተሻሻለ የስንዴና ገብስ ዝርያ ሰርቶ ማሳያ ላይ የመስክ ላይ ጉብኝትና ምክክር መስከረም 26 አደረገ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት ማኔጀር የሆኑት ዶ/ር አልማዝ ጊዜው በመድረኩ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ እየሰራ ያለው CASCAPE እና ISSD ከተሰኙ ፕሮግራሞች የተገኙ ምርጥ የግብርና ተሞክሮዎችን የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ 10 የፕሮግራሙ ወረዳዎች ላይ ማስፋት ነው፡፡ ለዚህም ውጤታማነት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ክላስተር የሶስት ዓመት ፕሮግራም ምርጥ ተሞክሮዎችን በማላመድ፣ በማረጋገጥ እና በማስፋት የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ የድርጅቶችንና የተቋማትን አቅም ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት በደቡብ ጎንደር ጋይንት ወረዳ ቆጥ መንደር ቀበሌ ታይ የተሰኘ የስንዴ እና ትራቪለር የሚባል የቢራ ገብስ ዝርያ የማሳ ላይ ሰርቶ ማሳያ እና የቅድመ ማስፋፋት ስራዎች እንደተሰራ ተናግረዋል፡፡

የፕሮግራሙ ተግባር ተቀብለው እየሰሩ ያሉ አርሶ አደሮች እንዳሉት የቀረበላቸው ዝርያ እስካሁን ከተመለከቱት የተሻለ መሆኑን ተናግረው ለመኖ የሚሰጠው ውጤት አናሳ በመሆኑ ቢሻሻል በማለት አሁንም የግብዓትና የማማከር ድጋፋቸውም ከዚህ በላቀ መልኩ እንዲቀጥል አሳስበዋል ፡፡ ከዚህ ባሻገር በመስክ ምልከታው በታዩ ጠንካራ ጎኖችና ጉድለቶች ላይ ከወረዳ እስከ ክልል ከሚገኙ የፕሮጀክቱ አጋር አካላት ጋር የአካባቢው አርሶ አደሮች በተገኙበት ምክክር ተደርጓል፡፡ በምክክሩም ላይ ከአርሶ አደሮች እና ከግብርና ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንዳሉት 2011-ለ2012 በጀት አመት በተሠሩ የግብርና የተግባር ስራዎች ላይ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በግልፅ ተመልክቶ ደካማውን ደካማ ጠንካራውን ጠንካራ ለማለት እና አዳዲስ አሰራር ፣ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ፤ ከቀበሌ ቀበሌ ፣ ከአርሶ አደር ወደ አርሶ አደር ለማስፋፋትና ለአካባቢው ተስማሚ የሚሆነውን ዝርያ ለመምረጥ የመስክ ምልከታው ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡

 

በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ከባሕር ዳር ከተማ ወጣት ማህበራት ጋር ምክክር ተደረገ !!

በሙሉጌታ ዘለቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ተማሪዎች አቀባበል በማድረግ ዙሪያ ከዘጠኝ በላይ ከሚሆኑ የባሕር ዳር ከተማ ወጣት ማህበራት ጋር በዩኒቨርሲቲው የጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ምክክር አደረጉ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮምንኬሽ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንዲሁም የባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ የባህር ዳር ወጣቶች በዩኒቨርሲቲው ፀጥታ ጉዳይና የተማሪዎችን ደንነት ከመጠበቅ አንፃር እያበረከቱት ያለውን አስተዋፆ አድንቀዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ አክለውም ዩኒቨርሲቲውም የስራ እድሎችን በመፍጠርና የወጣቶችን አቅም በመገንባት የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግ ጠቁመው ወጣቶችም የባሕር ዳር ከተማና  የዩኒቨርሲቲው ስም በበጎ እዲነሳ አሁንም ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት የነበረውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል፡፡

ከባሕር ዳር ከተማ የተወጣጡ የወጣት ማህበራት  ተወካዮች እንደገለጹት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሞባይልና የላፕቶፕ ዘረፋዎች የሚደርስባቸው ተብለው የተለዩ ዋና ዋና የሚባሉ መስመሮች የመንገድ መብራቶቻቸው የጠፉ እና አንዳንዶችም መስመር ሊዘረጋላቸው የሚገባ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ከመብራት ሀይል እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡  አክለውም ወጣቶቹ በባሕር ዳር ከተማም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ለተነሱት ጥያቄዎች በባሕር ዳር   ዩኒቨርሲቲ  ከፍተኛ አመራሮች መላሽ ተሰጥቷል፡፡    

Pages