Latest News

                         ለተማሪዎች ስልጠና ተሠጠ

በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እና በትምህርትና ስነ ባህሪ ኮሌጅ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የምርምር ስራቸውን ለማከናወን ያስችላቸው ዘንድ ስልጠና ተሰጣቸው፡፡

በኮሌጆቹ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በመመረቂያ ፅሁፍ ዝግጅት ጊዜ ለሚያከናውኑት  መረጃን የመተንተን፣ የማደራጀት እና የማጠናከር ተግባር በብቃት ይወጡት  ዘንድ ከሚያስለፍጓቸው ክህሎት እና እውቀት ውስጥ የ statistical package for social sciences software (SPSS) ስልጠና ከሚያዚያ 07 ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናውም ከስታቲስቲክስ ትምህርት ክፍል በመጡ ሁለት መምህራን የተካሄደ ሲሆን በስልጠናው ማብቂያም በዩኒቨርስቲው የስልጠና ዳይሬክቶሬት አቶ ወርቁ አበበ እና የአጠቃላይ ጥራት አስተዳደር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደሳለኝ እጅጉ እጅ ስልጠናውን ላጠናቀቁ ተማሪዎች  የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ (ፔዳ) ትናንት ምሽት በፖሊ-ፔዳ ኢንተርፕራይዝ ላይ ቃጠሎ ተከስቶ በተደረገ ከፍተኛ ርብርብ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

 

ቃጠሎውን ለማጥፋት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶች፣ የጸጥታ ሃይልና ልዩ ኃይል አባላት እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብና የእሳት አደጋ መከላከያ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ቃጠሎው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር የቻሉ ሲሆን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለእነዚህ በባለቤትነት ስሜት ከፊት ተሰልፈው ቃጠሎውን ለመቆጣጠር ለተረባረቡት አካላት እጅግ ከፍተኛ ምስጋና አቅርቧል፡፡

 

የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

የገጠር ልማት ት/ክፍል በድህረ ምረቃና በሶስተኛ ዲግሪ አዳዲስ ፕሮግራሞችን ለመክፈት የስርዓተ ትምህርት ክለሳ አካሄደ
በሙሉጎጃም አንዱዓለም

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው የገጠር ልማት ት/ክፍል PhD in Rural Development (የሶስተኛ ዲግሪ በገጠር ልማት) እና MSc in Agricultural Extension and Innovation (የሁለተኛ ዲግሪ በግብርና ኤክስቴንሽን ኢኖቬሺን) አዳዲስ ፕሮግራሞች ለመክፈት በኮሌጁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የስርዓተ ትምህርት ክለሳ አካሂዷል፡፡

የኮሌጁ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ግርማቸው ስራው በግብርና ኤክስቴንሽን ኢኖቬሺን የሁለተኛ ዲግሪ የስርዓተ ትምህርት ረቂቁን አቅርበው እንዲገመገም ተደርጓል፡፡ ዶ/ር ግርማቸው የትምህርት ፕሮግራሙን መከፈት አስፈላጊነት ሲያስረዱ እንደተናገሩት ት/ክፍሉ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ በግብርና ኤክስቴንሽን ኢኖቬሺን ተማሪዎችን እያሰለጠነ ቢሆንም በሀገሪቱ በሙያው ተሰማርተው ያሉት ሙያተኞች ቁጥራቸው አናሳ ከመሆኑም በላይ የክህሎት ውስንነት ስለሚስተዋልና በሌሎች ሙያተኞች ስራው እየተሰራ በመሆኑ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ፕሮግራሙ የመጀመሪያ መሆኑ መከፈቱ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የሁለቱም ካሪኩለም ረቂቅ ቀርቦ በገምጋሚ እንግዶችና ታዳሚዎች አስተያየቶች ቀርበው ከአቅራቢዎችና በፕሮግራሙ ተሳታፊ በሚሆኑ መምህራን ግብረ-መልስ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

                     ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ተበረከተ       
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር ለሚገኘው የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ህክምና የሚውሉ መሳሪያን ጨምሮ ለዩኒቨርሲቲው ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አገልግሎት የሚሰጡ ልዩ ልዩ የህክምና ዕቃዎች ህንድ አገር ከሚገኘው ኦፕሬሽን አይ ሳይት ከተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት በርዳታ ተበርክቷል፡፡ከዚህ በተጨማሪ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ለመማር ማስተማር የሚውሉ ልዩ ልዩ መሳሪያዎች ለግሷል፡፡  

ዩኒቨርሲቲውም በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አማካኝነት የዩኒቨርሲቲውን የሚወክሉ ልዩ ልዩ የስጦታ እቃዎች ለበጎ አድራጎት ድርጅት ተወካዮች በምስጋና ስም አበርክተዋል፡፡  

ኮሌጁ ለዝሆኔ በሽታ ተጠቂዎች የአልባሳት ስጦታ አበረከተ

በሙሉጎጃም አንዱአለም

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለደቡብ አቸፈር ወረዳ የዝሆኔ በሽታ ተጠቂዎች የጫማ ስጦታ በማበርከት የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ አከናውኗል::

የኮሌጁ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ተጠሪ ዶ/ር ወንድማገኝ እምቢአለ ማህበሩ እንደ ኢትዮጲያ አቆጣጠር በ2004 ዓ.ም የተመሰረተና ከ400 በላይ አባላት እዳሉት ገልፀው ከአሁን በፊት በርካታ የበሽታው ተጠቂዎች ተከታታይ የህክምና አገልግሎት ስለተሰጣቸው ዘላቂ ፈውስ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በርክክቡ ስነ-ስርዓትም የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ዳኛው ዋሴ፣በሂሳብ ሹምነት እያገለግሉት የሚገኙት አቶ ስሜነህ ደርሶ እና የኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ደረበ ነጋ በወረዳው ጤና ጣቢያ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከዶ/ር ወንድማገኝ እጅ  የጫማ ስጦታውን ተቀብለዋል፡፡

ስጦታውን የተረከቡት የኮሚቴ አባላት ከአሁን በፊት በዶ/ር ወንድማገኝ በኩል ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት አግኝተው ከበሽታቸው መፈወሳቸውንና በየጊዜው የጫማ ስጦታ እየተደረገላቸው በመሆኑ የማህበሩ አባላት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በአንክሮ ተናግረዋል፡፡

ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ እውነታውና አቅጣጫው

በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋክልቲ አዘጋጅነት ‹‹ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ እውነታውና አቅጣጫው››  በሚል ርዕስ ተጋባዥ ምሁራን በተገኙበት በዩንቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ የግማሽ ቀን ውይይት ተካሄደ ፡፡

የመወያያ ፅሁፉ በታዋቂው ምሁር ዶ/ር ታየ ብርሃኑ የቀረበ ሲሆን በዋነኛነትም አቅራቢው በኢትዮጵያ የፌደራልዝም አመሰራረትና አተገባበር፣ የፌደራሊዝም ምስረታ መነሻ ሀሳብ ምንነትና አደረጃጀት የሚሉ ሀሳቦች ላይ ተኩረት ያደረገ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ታየ በፅሁፋቸውም ስለ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሲናገሩ በጎሳ ላይ መሰራት ያደረገ መሆኑ በአለማችን ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን የሃገሪቷን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ ስለመሆኑ ጥየቄን እንደሚያጭር ገልፀዋል፡፡

ፅሁፍ አቅራቢው አክለውም ሶስቱን የመንግስት ቅርሶች አሃዳዊ፣ ፌደራላዊና ኮንፌዴሪሽን የሚሉትን በመተንተን በኢትዮጵያ እና በሌሎች አገሮች የፌደራሊዝም ባህሪያትና ገፅታ በንፅፅር አቅርበዋል፡፡ በዚህም ከታዳሚው የግልፅነት ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሠጥቶባቸዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግቢዎች የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ፡

በሃገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን የጽዳት ስራ ምክኒያት በማድረግ ሚያዝያ 06/2011 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ግቢዎች የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ስራተኞችና ተማሪዎች የተሳተፉበት ይህ ዘመቻ ከየግቢው ቀላል የማይባል ደረቅ ቆሻሻን ከማስወገድ ባለፈ አብሮ የመስራት ባሕልን በማሳደግ ሌሎች የጋራ ርብርብ የሚፈልጉ ጉዳዩችን ሁሉ በትብብርና በጋራ በመስራት የተሻለ አካባቢን መፍጠር እንደሚቻል የታየበት ነው፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ባለፈ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ የሚኖሩ ወጣቶችና ሴቶችም የተሳተፉ ሲሆን በተለይም በኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ተሳትፎ ላደረጉት የአካባቢው ወጣቶች በተቋሙ ሃላፊዎች ምስጋናና የማስታወሻ ቲሸርት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ወጣቶቹ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ወደፊትም በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች አብረው መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ግቢዎች ማለትም በግብርና እና አካባቢ ሳይንስ፣ በህግና መሬት አስተዳደር፣ በዋናው ግቢ በተፈጥሮ ሳይንስ እና በሌሎችም ክፍሎች የጽዳት ዘመቻ የተካሄደ ሲሆን በዋናው ግቢ በተለይም በሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና በጎልማሶች ትምህርት ክፍል (Adult Education) ተማሪዎችና ጥቂት መምህራን የተደረገው ግን ከሁሉም የጎላና በተምሳሌትነቱ የሚጠቀስ መሆኑን ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ይህም የጽዳት ዘመቻ በየወሩ እንደሚካሄድ ከአስተባባሪዎቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡   

የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ 6ኛውን አገር አቀፍ ጉባኤ አካሄደ

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ 6ኛ አመታዊ ትምህርታዊ ጉባኤውን  በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለሁለት ተከታታይ ቀናት አካሄደ::

የፋኩልቲው ዲን ዶ/ር ቃለወንጌል ምናለ ጥሪውን አክብረው ለመጡት ታዳሚዎች በሙሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን  አስተላልፈው ፋኩልቲው በ8 የቅድመ ምረቃ፣ በ11 የድህረ ምረቃ እና በ3 የሶስተኛ ዲግሪ (PhD) ፕሮግራም ከ5000 (አምስት ሺህ) ተማሪዎች በላይ ተቀብሎ  በተለያዩ ሙያዎች እያሰለጠነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዲኑ አክለውም ፋኩልቲው ከሌሎች ኮሌጆችና ፋኩልቲዎች ቀድሞ የተቋቋመ ቢሆንም እስካሁን የሚጠበቅበትን ያህል መስራት እንዳልቻለ ጠቁመው የሰውን ልጅ በአግባቡ ለማነፅ ብሎም የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የማህበራዊ ሳይንስ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፤ በመሆኑም ፋኩልቲው በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ በጉባኤው ከተለያዩ ተቋማትና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተውጣጡ ምሁራን የሚቀርቡት ጥናታዊ ፅሁፎችና ውይይት የማንቂያ ደወል ሆኖ እንደሚያገለግል እምነታቸው መሆኑን ተናግረው በአሁኑ ስአት ፋኩልቲው የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችል በዕቅድና በተደራጀ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

መርሃ-ግብሩ በይፋ መከፈቱን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ዩኒቨርሲቲው በስምንት ግቢዎች በሶስቱም የስራ አምዶች ማለትም በመማር ማስተማሩ፣በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በመግለፅ ዩኒቨርሲቲውን በሰፊው እያስተዋወቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ እንደማሳያም  ባህር ዳር ከተማን የትምህርት ከተማ ለማድረግ  በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት በኩል ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸው ተግባራት አመላካች እንደሆኑ ተናግረው የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲም ታሪክ ሳይዛባ ለትውልድ እንዲተላለፍ፣ፖለቲካም በሳይንሳዊ ዘዴ ለማህበረሰቡ ማስተላለፍ ያለበትን መልዕክት እንዲያስተላልፍ እንዲሁም በጂኦግራፊውም ዘርፍ ብቁ ባለሙያ በማፍራት ረገድ ከፍተኛ የሆነ አገራዊ ድርሻ እንዳለበት ተገንዝቦ በየአመቱ ጉባኤውን ማክበር ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ በመለየት ክፍተቶችን የሚሞላ ስራ ማከናወን እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

የጉባኤውን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጋብዘው የመጡት ፕሮፌሰር ወልደአምላክ በውቀቱና የዩኒቨርሲቲያችን አንጋፋ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ ሲሆኑ ፕሮፌሰር ወልደአምላክ እንዳሉት የምርምር ስራዎች ተግባራዊነት አንዱ መለኪያ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆን ጥናት ማድረግ እንደሆነ ገልፀው ይህን እውን እስከምናደርግ ለውጥ የሚያመጣ ስራ እንዳልሰራን በማሰብ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል ሲሉ ክፍተቱን ጠቁመዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በተለያዩ ሙህራን በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

5ኛው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቱሪዝም ሳምንት አመታዊ አውደ ጥናት ተካሄደ
*****************************************************
የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት ‹‹ የባለ ድርሻ አካላት ሚና በቅርሶቻችን እንክብካቤ ›› በሚል መሪ ቃል መጋቢት 27, 2011 ዓ.ም. የግማሽ ቀን አውደ ጥናት ተካሂዷል፡፡

በአውደ ጥናቱ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ኮሌጅ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አያሌው መለሰ በጥናታዊ ፅሁፋቸው እንዳቀረቡት ጣናን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ መጀመሪያ የሃይቁን ድንበር ማስከበር ይገባል ሲሉ፤ ለዚህም ምክንያቱ ጣና ከላይም ከታችም እሳት እየበላው በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ከላይ የጣና ዳር ተራራ እየታረሰ መሆኑ፤ ከታች ደግሞ ወደ አባይና ጣና ሀይቅ የሚለቀቅ ቆሻሻ መኖሩ ምሆኑን ገልፀው ከዚህም ባሻገር ጣና በደለል በመሞላቱ ምክንያት እስከ ውሃው ዳር እየታረስ በመሆኑ 120 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የሀይቁ አካል በድን ሆኗል ብለዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ከሚኒስተር መ/ቤቱ፣ ከባህር ዳር ከተማ ባህል ቱሪዝም እና ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎች የተጋበዙ መምህራንና ባለሙያዎች ተገኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡

ፕሬዚደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የዩኒቨርሲቲው መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች፣ ሴት መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎች በተገኙበት መድረክ  በሴቶች በተለይም በዩኒቨርሲቲው ሴት  ተማሪዎች ተግዳሮቶች ዙሪያ በዋናው ግቢ ኦዲቶሪየም አዳራሽ ውይይት አደረጉ፡፡

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንግዶች ወደ ውቧ ባህር ዳር እና ወደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንኳን በደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ያለባቸውን ታላቅ የሀገር ኃላፊነት ከተቀበሉ በአጭር ጊዜ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ለመጉብኘት በመምጣታቸው አመስግነው ዩኒቨርሲቲው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ያከናወናቸውን እና እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት በአጭሩ ገልፀዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ካላቸው የተጣበበ ጊዜ የሴት ተማሪዎችንና መምህራንና ሰራተኞች ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ለመካፈል እና ያላቸውውን የዳበረ የስራና የህይወት ተሞክሮ ደግሞ ለማካፈል በዩኒቨርሲቲው በመገኘታቸው በራሳቸው እና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስም ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ስርዓተ-ፆታ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሚል ርዕስ አጠር ያለ ንግግር አቅርበዋል፡፡ በንግግራቸውም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የዳሰሱ ሲሆን ተጨማሪ ስራም እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬው በንግግራቸው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተለያዩ የጥናት ምስኮች ላይ ያተኮሩ ተቋማት ግቢዎች  እንዳሉት አውስተው ከተማዋን የዩኒቨርሲቲ ከተማ እንዳደረጋትና በዚህም ምክንያት UNESCO የትምህርት ከተማ ብሎ እንደሰየማት አስታውሰዋል፡፡ በተያያዘም የዩኒቨርሲቲውን የወደፊት አደረጃጀት የሚያሳይ የፖሊ-ፔዳ ማስተር ፕላን አሳይተዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬው በመቀጠል የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ በቁጥር እና በመቶኛ አመልክተው ከርቀት ትምህርት ውጭ ተሳትፏቸው አናሳ መሆኑን ጠቁመው የፕሬዚደንቷ እገዛ ከታከለበት በዚህ ዙሪያ የተሸለ ስራ መስራት እንደሚቻል የአቅም ግንባታ ስራ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ካሉ ሴት ተኮር ድጋፎች አንፃር የህፃናት ማቆያ የሚጠቀስ ሲሆን በ2012 ዓ.ም. በሁሉም ግቢዎች ተመሳሳይ ማቆያዎች እንዲኖሩ እቅድ እንደተያዘ ፕሬዚደንቱ ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱ መርሃ ግብር የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት ሚንስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው ለፕሬዚደንቷ የተደረገው አቀባበል እና በአዳራሹ የተገኘው ታዳሚ ከዚህ በፊት በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ወቅት እንዳላዩት ተናግረው ፕሬዚደንቷን እንኳን ደህና መጡ ብለዋል፡፡ ዶ/ር ሂሩት አክለውም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሰራቸው ስራዎች ከቀረበውም በላይ እንደሆነ አውስተው የሴት መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ማህበር እንዲቋቋም በማድረግ ሴቶች ለመብታቸው እንዲታገሉ ያደረገ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ወደ መድረክ በመውጣት ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን በጣና ፎረም ምክንያት እንደሚያውቁት ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚደንቷ አክለውም የመጀመሪያ የስራ ህይወታቸው በትምህርት ሚንስትር እንደነበር አስታውሰው ከዚያም ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ በሚመስለው የዲፕሎማሲው ዘርፍ አገራቸውን ለረጅም ጊዜ እንዳገለገሉ ገልጸው ጉዟቸው የፆታም ሆነ ሌሎች ተግዳሮቶችን በመፋለም የተሞላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በንግግራቸውም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ከታች ጀምሮ ሊሰራ እንደሚገባ በአፅንኦት አሳስበው የተለያዩ መሰናክሎችን አልፋ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባችውን ሴት ልጅ ዲግሪዋን ይዛ መውጣት እንድትችል ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም  ከተሳታፊ ሴት መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ፕሬዚደንቷ የተነሱትን ችግሮች ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ ለሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንደሚያሳውቁ ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በራሱ ሊፈቱ የሚችሉትን ችግሮች እንደሚቀርፍ እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ተቋማት አካታችና ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆናቸው መሰረታዊ መሆኑን ገልፀው በሴቶች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች የዜሮ ቶለራንስ ፖሊሲ መከተል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የሴቶች ጉዳይም የሁሉም ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ኃላፊነቱን በመውሰድ ተጨበጭ ለውጥ እንዲመጣ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁም ከወሬ ያለፈ ሃሳብ በማፍለቅ የሴቶችን ጉዳይ ወደ ማሃል በማምጣት ችግሮችን ለመቅረፍ መሰራት እንዳለበት ተናግረው ቀጣይ አቅጣጫዎችንም እንደሚከተለው ጠቁመዋል፡፡

1. የሴቶችን አስተዋፅኦ ብዛትና ጥራት ለማሳደግ ከሌሎች የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጉድኝት መሰራት፤

2. የማማከር ስራ/Mentoring- በስፋት መሰራት እንዳለበት ጠቁመው ወጣት ሴቶችን ለማበረታታት እና በራስ መተማመናቸውን ለማጎልበት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

3. በዩኒቨርሲቲው ለሴቶች የሚሰጠው የአጋዥ ስልጠና/ Tutorial/ አገልግሎት በውጤት ያልተደገፈ በመሆኑ ሂደቱን በመፈተሸ እና በማሻሻል ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

4. ሴቶች የነፃ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ስራዎች እንደሚሰሩና ጅምሮችም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

Pages