Latest News

ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ገለፃ ተደረገላቸው

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በትምህርት ሚኒስተር የተመደቡለትን የመጀመሪያ አመት ተማሪዎች በሰላም ግቢ ፋሽን አዳራሽ ስለቤተ መጻሕፍት አጠቃቀም በዳይሬክተሩ አቶ አሰማኸኝ አያሌው፣ ተማሪዎች ስለ ሚያጋጥማቸው የስነ ልቦና እና ማህበራዊ ጫና  በተማሪዎች  አማካሪ ማዕከል  አስተባባሪ  ዶ/ር አብዮት የኔዓለም፤ ለተማሪዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር ዋና ኢንስፔክተር ሙላት ስሜ ገለፃ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም ተማሪዎች የሬጅስትራርን የጊዜ ሰሌዳ ተጠቅመው የወጣውን ሕግና ደንብ እንዲያከብሩ በዩኒቨርሲቲው  ማዕከላዊ ሬጅስትራር  ቡድን  መሪ በአቶ መላኩ ቢያዝን  ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡

በሰላም ግቢ ስለተመደቡ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች አቀባበል የጠየቅናቸው የጀማሪ ተማሪዎች መርሃ ግብር የሰላም ግቢ ምክትል ዲን አቶ  ደምሰው መንግስቴ  በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ1300 በላይ የማህበራዊ እና  የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መካከል ከ700 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን በአካል መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ አንድ ተማሪ በአንድ ወሰነ ትምህርት ከ85% በላይ የሆነውን ክፍለ ጊዜ በክፍል ወስጥ ተገኝቶ  መከታተል ይኖርበታል በዚህም ከአላስፈላጊ ውጣ ውረዶች ይድናል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  አስተዳደር  ጉዳዮች ተቀዳሚ ዳይሬክተር አቶ ገደፋው ሽፈራው አንጋፋውና የመጀመሪያው  የምርምር  ዩኒቨርሲቲን መርጣችሁ በመምጣታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ኃላፊው አታርፍድ በሚል ለተማሪዎች ባቀረቡት ፅሁፍ የህይወት  ትልቁ ስህተት  ማርፈድ ነው፤ ሁሉም ነገር የሚያምረው እና የሚበጀው በጊዜው ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ማድረግ ያለብህን ነገር  ሳታመነታ ተሎ አድርገው፣ መጀመር ያለብህን ጉዳይ ሳትዘገይ ጀምረው፣ መተው ያለብህ ነገር ሳታቅማማ በጊዜ ተወው፣ መወሰን ያለብህ ጉዳይ ካለም ዛሬውኑ ወስን፣ ማቋረጥ ያለብህ ግንኙነት ካለ ሳይወሳሰብ ቋጨው፤ ህይወት ማለት እንደ አልፎ ሂያጅ ወንዝ ናት ወደፊት እንጂ ወደኋላ አትራመድም፣ እረፍዶ እንዳይፀፅትህ ጊዜህንና እድሜህን ባግባቡ ተጠቀምበት አስተውል ፀፀት መጨረሻ  እንጂ መጀመሪያ  መጥቶ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ነገን እንዳይቆጭህ ዛሬ አታርፍድ በሚል ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

 

የህግ ትምህርት ቤት ሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ነፃ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከል “የተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ መብቶች ምንነትና አተገባበራቸዉ”  በሚል ርዕስ በባሕር ዳርና አካባቢዉ ለሚገኙ የሃይማኖት አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች አደረጃጀቶች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ ሌሎች ተቋማት ለተውጣጡ ግለሰቦች በእንጅባራ ከተማ ከ28/08/2014 ዓም ጀምሮ የሁለት ቀን ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናዉም ስለሰብአዊ መብቶች በጠቅላላዉ ፣ ስለ ህፃናት ሰብአዊ መብቶች፣ ስለሴቶች ሰብአዊ መብቶች ፣ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች፣  ስለአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡

ስልጠናዉን በአካል በመገኘት በንግግር የከፈቱት የሕግ ትምህርት ቤቱ ዲን አቶ ተገኘ ዘርጋዉ በማሕበረሰቡ ዘንድ የሚከሰቱ የተለያዩ አለመግባባቶችን ከችግሩ ምንጭ በመፍታትና ዘላቂነት ያለዉ መፍትሔ በመስጠት ረገድ የሐገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የማይተካ ሚና ያላቸዉ ሲሆን ይህ ሚናቸዉን ለማጎልበት የአቅም ግንባታ ጉዳዮች መሰጠቱ አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አያይዘዉም እነዚህ ተቋማት አለመግባባትን በሚፈቱበት ጊዜ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መብት ከግንዛቤ ዉስጥ ቢያስገቡ ይበልጥ ተቀባይነት እንዲኖራቸዉና የተአማኒነት መጠናቸዉን እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል፡፡

ስልጠናዉ በሕግ ትምህርት ቤቱ የካበተ ልምድ ባላቸዉ አቶ ደሳለኝ ጥጋቡ እና አቶ ሙሃመድ ዳዉደ የተሰጠ ሲሆን ተስማሚ የሆነ  የስልጠና ስነዘዴ በመጠቀም በተጠቀሱት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንዛቤን ለማስጨበጥ ጥረት አድርገዋል፡፡

ሰልጣኞች በበኩላቸዉ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ስልጠና መሰጠቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳስገኘላቸዉ በመግለጽ በስልጠናዉ የጨበጡትን እዉቅት ወደ ተግባር ለመቀየር ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስልጠናዉ ቀጣይነት ባለዉ መንገድ እንዲሰጣቸዉ ጠይቀዋል፡፡

ስልጠናዉ የተዘጋጀዉ በነፃ የህግ ድጋፍ መስጫ ማዕከል አማካኝነት ነው

ትምህርት እና የምርምር ተወዳዳሪነት ኢኮኖሚያዊ ክህሎትን ከማሳደግ አኳያ በሚል ርእሰ ጉዳይ ህዝበ ገለጻ ተካሄደ

**********************************************************************

[ሚያዚያ 28/2014ዓ/ም፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ] 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል  ለአካዳሚክ እና ለምርምር ተወዳዳሪነት ኢኮኖሚያዊ ክህሎትን ማሳደግ ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ህዝበ ገለጻ በኮሌጁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አለባቸው አስፋው በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው  የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር  ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና  ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንደገለጹት ከዚህ በፊት በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ላይ የጥናትና ምርምር ማዕከል ለማቋቋም ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በዛሬው እለት ህዝበ ገለጻ የሚያደረጉት ዶ/ር ግርማ ተስፋሁን ከዚህ በፊትም ስልጠና ሰጥተውልን ያውቃሉ ዛሬም ስለመጡ አመሰግናለሁ ብለዋል ዶ/ር ተስፋዬ፡፡

የአገራችን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በእውቀትና ጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ በየዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ እየተሰራ አይደለም ስለሆነም በትኩረት መሰራት ይገባል፡፡ እንደሀገር የኢኮኖሚ ፍኖተ-ካርታችን ዝብርቅርቅ ያለ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው ስለሆነም የኢኮኖሚ አቅም የት አካባቢ ነው ያለው ብሎ ያሉንን ጸጋዎች በመለየት ጥናትና ምርምር ማድረግ አለብን፡፡ ውሃ እና አፈር በእጃችን ይዘን ተመጽዋች የሆንበት ሁኔታን መቀየር አለብን፤ ለኢንዱስትሪ ግብአቶች የሚሆኑ ምርቶች በስፋት እንዲመረቱ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ መሰራት ይገባል ሲሉ ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም በዚህ ክልል ያልተጠቀምንባቸው የኢኮኖሚ አቅሞች በየቦታው አሉ እነሱን አውጥተን ጥቅም ላይ ለማዋል የዩኒቨርሲቲው አመራርና ትምህርት ክፍሉ ለምን የኢኮኖሚክስ ምርምር ማዕከል አቋቁመን በትኩረት አንሰራም የሚል ቁጭት ሊያድርብን ይገባል፡፡

የኢኮኖሚክስ ምርምር ማዕከል እንዲቋቋም ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ያሉ ሰዎች ግፊት ሲያደርጉ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ዛሬም የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ጠንክሮ ለመስራት የነደፋቸው ፕሮግራሞች አበረታች ናቸው የተዘጋጁት መርሀ-ግብሮችም ለሌሎች ትምህርት ክፍሎች ጭምር ልምድና ተሞክሮ የሚሰጥ ነው ይህም መጠናከር አለበት ሲሉ ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የኢኮኖሚ ምርምር ማእከሉን እንድታጠናክሩት ከአደራ ጭምር ማሳሰብ እፈልጋለሁ ብለዋል ዶ/ር ተስፋዬ፡፡

ህዝበ ገለጻውን ያደረጉት ዶ/ር ግርማ ተስፋሁን  ለአካዳሚክ እና  ለምርምር  ተወዳዳሪነት  ኢኮኖሚያዊ ክህሎትን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን በዝርዝር ገልጸዋል፡፡

የመርሀ ግብሩ ዋና አስተባባሪ እና የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሀላፊ አቶ ነጋ እጅጉ በበኩላቸው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ከዚህ በፊት ባልነበረ ሁኔታ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ እስከ ሚቀጥለው ሳምንት ድረስ የኢኮኖሚክስ ሳምንት በሚል የተለያዩ ስልጠናዎችን፤ ህዝባዊ ገለጻዎችን፤ የPhD ተማሪዎችን ተቋቁሞ የመሳሰሉ ስራዎችን እየሰራ ሲሆን በተለይም የPhD ተማሪዎች በህዝበ ገለጻው ያገኙትን እውቀት ከስልጠናው ጋር አስተሳስረው ይጠቀሙበታል ብለዋል፡፡

ህዝበ ገለጻው ትኩረት የሚያደርገው በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ትምህርት የተለመደና ለምርምር ግብአት የሚሆን የኢኮኖሜትሪክስ ሞዴልን ጠቀሜታ ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ይህን ሞዴል በምን አይነት መንገድ መጠቀም ውጤታማ እንደሚያደርግ እንዲሁም ኢኮኖሜትሪክስ ያለውን ጠቀሜታ በትክክል ተረድቶና እሱን ተጠቅሞ ጥናትና ምርምር ሰርቶ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆን ጥናት እንዲያደርጉ ያግዛል ብለዋል አቶ ነጋ እጅጉ፡፡

ሌሎች ትምህርት ክፍሎችም ተመሳሳይ ስራዎችን መስራት ቢችሉ ሲሉ አቶ ነጋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፤ የ PhD ተማሪዎች፤ የኮሌጁ መምህራን፤ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ PhD ተማሪዎች፤ከአማራ ክልል የተለያዩ ቢሮዎች የመጡ ተሳታፊዎች በመድረኩ ተገኝተዋል፡፡

 

81ኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአርበኞች ቀን በዓል ተከበረ

[ሚያዚያ 27/2014ዓ/ም፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ]

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዐባይ የቋንቋና ባህል ጥናት ተቋም ከታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል እንዲሁም የውስጥ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከባህል ማዕከል ጋር በመተባበር 81ኛውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አርበኞች ቀን በዓል የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በጥበበ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተከበረ፡፡ 

በዓሉን በተመለከተ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንደገለጹት ብሔራዊ በዓሎቻችን ስንዘክር የትናንት ማንነታችን፤ ለዛሬ የደረስንበት  እና ለነገ ደግሞ መድረስ የሚጠበቅብንን መነሻ አድርገን ልንማማርባቸው የሚገባ ስለሆነ ዩኒቨርስቲዎችም የአካዳሚክ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ምን እንማራለን፣ ዩኒቨርስቲዎችስ ታሪክን ከመሰነድ እና ለቀጣይ ትውልድ ከማስተላለፍ አንፃር ምን ድርሻ አለባቸው የሚለውን ምሁራዊ ውይይት በማድረግ አስተዋጽዖ ለማበርከት ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም በታሪክ እንደሚታወሰው በዛሬዋ ቀን ጀግኖች የኢትዮጵያ አርበኞች የድል ችቦዎቻቸውን ያበሩበት ቀን ሲሆን የጣሊያንን ሰንደቅ ዓላማ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በብሔራዊ ቤተመንግስት የሰቀሉበት ቀን በመሆኑ ሁላችንም ጀግኖች አርበኞቻችን የምናወድስበት፣ የምናመሰግንበት እና ከነሱ ልምድ ተምረን እያንዳንዳችን በየመክሊታችን አስተዋፆ የምናደርግበት ነው ብለዋል፡፡   

በስነ-ስርዓቱ ሁለተኛው የኢትዮ-ጣልያን ጦርነት በአዶልፍ ፓርላሳክ እይታ በሚል ርእሰ ጉዳይ በዶ/ር ዋጋው ቦጋለ ከታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል እንዲሁም አርበኛ ደራሲያንና ተጋድሏቸው በሚል ርእስ ሀኪም ወርቅነህ እሸቴን በማሳያነት በመግለፅ ዶ/ር ሞገስ ሚካዔል ከአባይ የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን በፅሁፍ አቅራቢዎች እና መድረኩን በመሩት በዶ/ር ፈንታሁን ከታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም ከአቶ አሰፋ አሊ ‹‹አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ- መፅሐፈ ሰዋሰው ወግስ መዝገበ ቃላት ሐዲስ (1962)›› እንዲሁም ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ- የዓለም ጅኦግራፊ (1920)›› የሚሉ መፅሀፍትን ለዓባይ የቋንቋና የባህል ጥናት ተቋም ተበርክቷል፡፡  

 

 

[ሚያዝያ 21/2014 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ]

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እና ምርምር ተቋም የምክክር አውደ ጥናት አካሄደ

-------------------------------------------------------------------------------------------

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እና ምርምር ተቋም የተለያዩ ምሁራን የተሳተፉበት የምክክር አውደ ጥናት በዋናው ግቢ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡

 

የምክክር አውደ ጥናቱን  በንግግር  የከፈቱት  የባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ  የምርምርና  ማህበረሰብ  አገልግሎት  ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰአት በ5 ፕሮግራሞች ማለትም በመምህራን ትምህርትና አመራር ጥናት፤ በቴክስታይል ምህንድስና፤ በመሬት አስተዳደር፤ በአደጋ ስጋት አስተዳደርና ምግብ ዋስትና፤ በማሪታይም ምህንድስና የልህቀት ማዕከል መሆን የቻለ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

የልህቀት ማዕከላት የተከፈቱበት ምክንያት ከዛሬ 11 አመታት በፊት የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የአሰራር ስርአት ክለሳ ሲያደርግ በምርምር የልህቀት ማዕከል ለመሆን በአገራችን ያለውን ምቹ ሁኔታ እና ዩኒቨርሲቲው ያለውን አቅም መነሻ በማድረግ በአምስት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የምርምር ልህቀት ማዕከል መሆን አለብን በሚል መነሻ የተጀመረ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ዛሬ ምክክር የተደረገበት የትምህርት ጥናት አንዱ መሆኑን ዶ/ር ተስፋዬ  ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም ፕሮግራሞችን በየጊዜው በጥናትና ምርምር የተደገፈ ፍተሻ በማድረግ የማያስፈልጉት ፕሮግራሞች እንዲዘጉ፤ አስፈላጊ የሆኑት ደግሞ ተሻሽለው እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንዲሁም አዳዲስ ፕሮግራሞች እንዲከፈቱ ማድረግ የሚያስችል ስልት መንደፍ እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልምድና ተሞክሯቸውን ለማካፈል ለመጡት እና ጥናት ላቀረቡት ዶ/ር ግርማ ለማ እና ዶ/ር ብርሃኑ አበራ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር ግርማ ለማ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት ኢንስቲትዩት የሰራቸውን ስራዎች፤ በምርምር ያሳተማቸውን የህትመት ውጤቶችና የምሁራን ተሳትፎን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር ብርሃኑ አበራ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት ኢንስቲትዩትን አደረጃጀትና አሰራር እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እና ምርምር ተቋም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የሰራቸውን ስራዎችና ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶች በተመለከተ የተቋሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ያየኽ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን በጥናት አቅራቢዎች እና የምክክር መድረኩን በመሩት የምርምር እና ህትመት ተቀዳሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ይኸነው ገብረ ስላሴ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አስናቀው ታገለ የምክክር መድረኮችን በየጊዜው በማካሄድ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎች፤ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የተለያዩ የምርምር ማዕከላት ዳይሬክተሮች፤ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ኮሚሽን አባላት፤ የፋኩልቲ ተወካዮችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በነባሩና አዲሱ የሥራ አመራር ቦርድ መካከል የሥራ ርክክብ ተደረገ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሁን ለደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሲያበረክት የቆየውና በክቡር አምባሳደር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ሰብሳቢነት ይመራ የነበረው የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ በቅርቡ ለተሰየመውና በክቡር አቶ አደም ፋራህ ለሚመራው አዲሱ ሥራ አመራር ቦርድ ዛሬ በይፋ ሥራ አስረክቧል።

በዚህ ልዩ የሥራ ርክክብና የምስጋና ሥነ-ስርዓት ላይ ነባሩን ሥራ አመራር ቦርድ ላለፉት ሶስት ዓመታት በከፍተኛ ሃላፊነት የመሩትና ለዩኒቨርሲቲው እድገት ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው የቦርዱ ሰብሳቢ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና የቦርድ አባል ለነበሩት አቶ ሃብታሙ ክብረት
በቦርድ ሰብሳቢው ክቡር አቶ አደም ፋራህና በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።  

በሥነ- ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና አመራሩ ለተቋሙ እድገት ከሥራ አመራር ቦርዱ ጋር የነበረውን ቅንጂት አድንቀው ለዩኒቨርሲቲው ይበልጥ ውጤታማነት የጋራ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አዲሱ የሥራ አመራር ቦርድም ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ሥራ እንዲሰራ አደራ ብለዋል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ከፍተኛ አመራር አካላት ተገኝተዋል።

Bahir Dar University holds consultative discussion with Smart Innovation Norway, a research center based in Norway, to work collaboratively.
[April 19/2022 Bahir Dar University, BDU]
Dr Tesfaye SHiferaw, vice president for Research and Community Services, BDU briefed the guests about Bahir Dar and the University. The v/president also highlighted the University’s focus in areas of technology innovation.
Mrs Heidi Tuiskula deputy general manager and head of the Energy sector of Smart Innovation Norway said she was pleased with the presentation on Bahir Dar University. She added that her organization is interested to work in collaboration with Bahir Dar University.
The guests paid a working visit to the University. Led by Dr. Tesfa Tegegne, Director of Bahir Dar Science and Incubation Center (STEM center), the guests visited the laboratories of the center and innovations by ICT department and the students.
Similarly, Bezawork Tilahun, BIT maker space coordinator at Dar University Institute of Technology (BiT), explained to the visiting guests on the innovative works being made by students at the Institute of Technology.
Bezawork added that BIT maker space project is focused on working in areas of medical technology, agricultural technology, cosmetics products, food processing and recycling.
Visitors from Norway expressed their appreciation on the innovations and the hands on teaching learning they have witnessed. They expressed that they have seen enough to decide on areas in which Smart Innovation Norway could work collaboratively.
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከ ‹‹Smart Innovation Norway›› ጋር ለመስራት የሚያስችል ምክክር አካሄደ
 
[ሚያዝያ 11/2014 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ] የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኖርዌይ ሀገር ከሚገኘው ‹‹Smart Innovation Norway›› ከተባለ የምርምር ተቋም ጋር በትብብር መስራት የሚያስችል ምክክር አካሄደ፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ባሕር ዳር ከተማን እና ዩኒቨርሲቲውን በማስመልከት ለእንግዶች ገለጻ አድርገዋል፡፡ ም/ፕሬዚደንቱ አክለውም በቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ዩኒቨርሲቲው ስለሚሰራባቸው የትኩረት ነጥቦችም አንስተዋል፡፡
የ‹‹Smart Innovation Norway›› ምክትል ስራ አስኪያጅና የኢነርጅ ዘርፍ ኃላፊ Mrs. Heidi Tuiskula በበኩላቸው ስለ ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ስራዎች በቀረበላቸው ገለጻ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ድርጅታቸውም በቀጣይ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
እንግዶቹ በዩኒቨርሲቲው የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የባሕር ዳር ሳይንስ ኢንኩቤሽን ማዕከል (STEM Center) ቤተ ሙከራዎች፤ ICT ክፍል እና በተማሪዎች የተሰሩትን የፈጠራ ስራዎች በማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋ ተገኘ አማካኝነት ተጎብኝቷል፡፡
በተመሳሳይ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (BiT) ሜከር ስፔስ አስተባባሪ (BIT maker space coordinator) ወ/ሪት ቤዛወርቅ ጥላሁን በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች እየተሰሩ ያሉትን የፈጠራ ስራዎች በተመለከተ ገለጻ በማድረግ አስጎብኝተዋል፡፡
ወ/ሪት ቤዛወርቅ አክለውም የፕሮጀክቱ የትኩረት መስኮች የህክምና ቴክኖሎጂ፤ የግብርና ቴክኖሎጂ፤ የመዋቢያ ምርቶች፤ የምግብ ማቀነባበርና ተረፈ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ዙሪያ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከኖርዎይ የመጡት የጉብኝቱ ተሳታፊዎችን ባዩት የፈጠራ ስራዎችና በተግባር የታገዘ ትምህርት አግራሞታቸውን ገልጠው የመጡበት ተቋም ‹‹Smart Innovation Norway›› በዘርፉ በትብብር ሊሰራባቸው የሚችላቸውን ስራዎች ለመወሰን የሚያስችል ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የሥርዓተ-ፆታ እና ልማት ጥናቶች ትምህርት ክፍል  እያካሄደ የነበረው አገር አቀፍ ጉባኤ ተጠናቀቀ

 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ስር የሚገኘው የሥርዓተ-ፆታ እና ልማት ጥናቶች ትምህርት ክፍል ከ "Friedrich Ebert Stiftung"  ጋር በመተባበር  "National conference on Contemporary Gender Issue" በሚል መሪ ቃል ሁለተኛውን አገር አቀፍ 

ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ ከሚያዚያ 05-06/2014 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ተካሄዶ  ተጠናቀቀ፡፡

የፋኩልቲው ዲን ዶ/ር ታዬ ደምሴ ለፕሮግራሙ መሳካት ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱት አካላት ምስጋናና ለታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ጉባኤው አገር አቀፍ መሆኑ ለትምህርት ክፍሉ መጠናከር ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑንና ትምህርት ክፍሉም ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

 

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ በኢትዮጵያ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዘዳንት ሆነው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ያገለገሉት  ክብርት  አምባሳደር  ዶ/ር  የሽመብራት  መርሻን  ጨምሮ  ለመላው  ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዶ/ር እሰይ አክለውም የጉባኤው መካሄድ ትምህርት ክፍሉን አንድ እርምጃ ከፍ እንደሚያደርገውና ለወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከሚቀርቡት ጥናቶች በመነሳት የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ እንደሚለይ ተናግረዋል፡፡

የክብር እንግዳዋ ክብርት  አምባሳደር ዶ/ር  የሽመብራት መርሻ  ይህን ጉባኤ  ለመታደም  ከሩቅም ከቅርብም ለመጡ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤታቸውም ቤተሰባቸውም መሆኑን አውስተዋል፡፡ በማስከተል ከአሁን  በፊት ዩኒቨርሲቲውን በማገልገል ላይ እያሉ ት/ት ክፍሉን ለማቋቋም በርካታ ውጣ ውረዶችን  እንዳሳለፉና በተለይ በአውሮፓ አገራት ያለውን የስርዓተ ፆታ የተራራቀ ልዩነት ተገንዝበው በአገራችንም የሴቶች ተሳትፎ ጎልቶ እንዲወጣ የዘወትር ህልማቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አምባሳደሯ በማስከተል  በአገራችን "ስርዓተ-ፆታ"  ሲባል የሴቶች  ጉዳይ ብቻ አድርጉ  የማየት  የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዳለና ዛሬ ላይ ያ አስተሳሰብ ተሰብሮ የሁሉም አጀንዳ መሆኑን የሚያመላክተው  ይህ ደማቅ ጉባኤው መካሄዱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡  ጉባኤውም ት/ት ክፍሉ ከመዳህ ዘሎ  በእግሩ መቆሙን ማሳያና የሴቶችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ  የማንቂያ ደወል እንደሆነ ዶ/ር የሽመብራት በደስታ ገልፀዋል፡፡

የእለቱን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ም/ኃላፊ ወ/ሮ ሰላም አለማየሁ በአገራችን ብሎም በክልላችን ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካው መስክ ያላቸው ተሳትፎና ውክልና አናሳ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ወ/ሮ ሰላም አክለውም ይህ የተሳትፎ ውስንነት ሴቶች የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዳያበረክቱና ከድህነት አረንቋ እንዳይወጡ ቢያደርጋቸውም   ጭቆናውን ተቋቁመው  በሁሉም መስኮች ሴቶች እያስመዘገቡት ያሉት ቱርፋቶች በቀላሉ የማይታዩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ በማስከተል የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ አበረታች ተግባራት ቢኖሩም የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የተለያዩ መሰናክሎች እንዳሉና ከእንቅፋቶችም መካከል በሴቶች ላይ ያለው የተዛባ አመለካከት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ጾታዊ ጥቃት፣የሴቶች የስራ ጫና፣ ተቋማዊ ተግዳሮቶች፣ወቅታዊ፣ሃገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች በዋነኛነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 

በተጨማሪም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ  ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመተባበር በርካታ አኩሪ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀው በአሁኑ ወቅት በክልላችን ብቸኛ የሆነውን የለውጥ መሪነት ለስርዓተ- ጾታ  ዕኩልነት  የስልጠና ማዕከል (Transformative Leadership For Gender Equality Training Center) በፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል መዘጋጀቱን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ፀድቆ የስልጠና ካሪኩለም ተዘጋጀቶለት በቅርቡ ስራ የሚጀምር መሆኑንና ዩኒቨርሲቲው ለሴቶች ተሳትፎ  ፈር ቀዳጅነት በመሆን በተለያዩ  ፕሮግራሞች  የትምህርት አድል  መፍጠሩን  ም/ቢሮ ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡

ወ/ሮ ሰላም በመልዕክታቸው ማጠቃለያም የስርዓተ-ጾታ ጉዳይ የአንድ ጾታ ጉዳይ ብቻ አለመሆኑንና በአንድ ክንፍ መብረር አለመቻሉን ሁሉም ሊረዳው እንደሚገባ በአንክሮ ገልፀው እኩልነቱን ለማስረፅ ከቤተሰብ ጀምሮ ት/ት ቤቶችና የሐይማኖት ተቋማት፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ምሁራን  ሰፊ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ 

 

የጽሁፍ አቅራቢዎች አገር በቀል ምሁራን በመሆናቸው ሴቶቸን የማብቃት  ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ወደ አመራሩም ሲመጡ ወንበሩን ብቻ መስጠት ሳይሆን  የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

 

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

      ባዳዩ-BDU

💦💦💦💧💦💦💧💦💦💦

ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ

Wisdom at the source of Blue Nile

🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎

Thank you for Inviting, liking, sharing & visiting BDU pages!

ለተጨማሪ መረጃዎች፡-

Telegram ፡- t.me/BDU_ISC_Official

Main Website :- www.bdu.edu.et

Facebook: - https://www.facebook.com/bduethiopia

YouTube ፡- www.youtube.com/c/BduEduEt

LinkedIn ፡- www.linkedin.com/school/bahir-dar-university

Twitter: - https://twitter.com/bdueduet

 

በመጪው ብሔራዊ ውይይት ተስፋዎች እና ፈተናዎች ላይ ውይይት ተደረገ

የባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ከFRIEDRICH EBERT STIFTUNG ጋር በመተባበር ‹‹መጪው  ብሔራዊ ውይይት  ተስፋዎች እና ፈተናዎች››  በሚል ጭብጥ  የግማሽ ቀን አውደ-ጥናት በዋናው ግቢ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡  

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ በመክፈቻ ንግግራቸው ባለፉት አስርት ዓመታት እንደ ህዝብ በብዙ ችግሮች ያለፍን እንደሆነ በመገንዘብ ለነዚህ ችግሮች ምንጭ የሆኑትን በመለየት ምሁራኑ ችግሮችን እንድናልፋቸው ዘንድ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ብዝሃነታችን አዙሮ በመጠቀም በመካከላችን መከፋፈል፣ መጠላላት፣ መገዳደል እንዲኖር የሚሰሩ ኃይላት እንደመሮራቸው ችግሮች እንዳይከሰቱ በትጋት መስራት ይገባል ብለዋል ዶ/ር እሰይ ከበደ፡፡

 

በሴሚናሩ Ethiopians Identity Crisis: Way Forward For the National Dialogue በፕሮፌሰር  ባህሩ ዘውዴ ፣ The Politics and Practices of Adjudicative and Deliberative Institution in Ethiopia: Lessons from Recent History በዶ/ር ተካልኝ ወልደማሪያም፣ Do No Harm: Managing Expectation in National Dialogue በፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ፣ The Conflict in Northern Ethiopia and Its Ramifications በዶ/ር ቴዎድሮስ ሃይለማሪያም የተሰኙ ጥናታዊ  ፅሁፎች  ቀርበው  ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ዶ/ር ታዬ ደምሴ በበኩላቸው የዚህ አይነት ውይይት ቀጣይነት ያለው መሆኑን ጠቁመው የጥናታዊ  ፅሁፎች  አቅራቢዎችን እና ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋፆ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ክብርት አምባሳደር ዶ/ር የሽመብራት መርሻን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው  ከፍተኛ አመራሮች፤ የትምህርት ክፍሉ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ  የተደረገላቸው ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ምሁራን እና ጥናት አቅራቢዎች ተሳትፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ወንዳለ ድረስ

የሰባታሚት ማረሚያ ቤት ስፖርታዊ ውድድሮችን ማካሄድ ጀመረ

*******************************************************

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከባሕርዳር ከተማ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጋር በመተባበር በማረሚያ ቤት ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች ሰባታሚት በሚገኘው የማረሚያ ቤቱ ስፖርት ሜዳ ከሚያዚያ 7/2014 ዓ.ም ጀምሮ ስፖርታዊ ውድድር ማካሄድ ጀምሯል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ የስፖርት ሳይንስ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዘመኑ ተሾመ ፕሮግራሙን ሲከፍቱ እንደገለጹት ውድድር ማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያት ታራሚዎች በቆይታቸው ከብቸኝነትና ተስፋ ከመቁረጥ ስሜት እንዲወጡ ለማድረግና አካላዊ እና አዕምሯዊ ጤናቸው ተጠብቆ የፍረድ ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ መልካም እና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ በማሰብ ነው ብለዋል፡፡

የአብክመ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የህግ ታራሚዎች ማረምና ማነጽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያዜ መኮነን በበኩላቸው ውድድሩ ለስነ ልቦና፣ ለአካል እና ለጤና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረጉ በተጨማሪ በታራሚዎች እና በማረሚያ ቤቱ አባላት መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር ያግዛል ብለዋል፡፡ ውድድሩ ለአንድ ወር ከ15 ቀን እንደሚቆይም ገልፀዋል፡፡

ስፖርታዊ ውድድሩ የተካሄደው በታራሚዎችና በጥበቃ ሰራተኞች (ወታደሮች) መካከል ሲሆን በውድድሩ ላይ የተካሄዱት የስፖርት አይነቶችም መረብ ኳስ፣ ገመድ ጉተታ እና እግር ኳስ ናቸው፡፡

በመጨረሻም የዚህ ፕሮግራም አዘጋጅ ከሆኑት መካከል የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ ዳንኤል ጌትነት የፕሮግራሙን መጀመር ታራሚዎች በጉጉት ሲጠብቁት እንደነበር በመግለፅ ቀጣይነት እንዲኖረውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ሆነ ሌላው የማህበረሰብ ክፍል ለስፖርታዊ ውድድሩ አስፈላጊ የሆኑ የቁሳቁስ ድጋፎችን ቢያደርግልን የሚል መልክት አስተላልፈዋል፡፡ 

ዘጋቢ፡- ባንቹ ታረቀኝ

 

Pages