የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት አደረጉ
Selam Campus
24 Apr, 2026
የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት አደረጉ።
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም: በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመገኘት የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ ሌሎች የልህቀት ማዕከላትን የተመለከቱ ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ እና ከሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር በሁለትዮሽ ትብብር ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ዘመናዊ የቤተ-ሙከራ መሰረተ ልማቶችን ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለሚደረጉ የጋራ ምርምሮች መጠቀም ፤ ወጣት የፈጠራ ባለተሰጥኦዎች በአሜሪካ ሀገር ከሚገኙ የትምህርትና የስልጠና ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር.፤ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ከአሜሪካ ኤምባሲና ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ያለውን አጋርነት ይበልጥ ማሳደግ በሚሎ ጉዳዮች ተወያይተዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ ለዩኒቨርሲቲው እየሰጠ ላለው ዕድልና እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ ዩኒቨርሲቲው የተጀመሩ የትብብር ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለወደፊትም በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

