ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የፕሮፌሰር መኮነን አሰፋ 3ኛ ዓመት መታሰቢያ ስፖርታዊ ውድድር

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የፕሮፌሰር መኮነን አሰፋ 3ኛ ዓመት መታሰቢያ ስፖርታዊ ውድድር ተሳተፈ

በፕሮፊሰር መኮነን አሰፋ (ከ1936-2011 ዓ.ም) መታሰቢያ ስፖርታዊ ውድድር ወደ ደብረ ታቦር ያቀናው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ልኡካን ቡድን በቦታው በመገኘት ልምዱን ያካፈለ ሲሆን የስፖርት ሳይንስን በሚመለከት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና ስፖርቱን በምርምር ለመደገፍ ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

በወዳጅነት ስፖርታዊ ውድድሩ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ የቀለም ዕውቀትን በመተግባር ቀልብን የሚስቡ ማራኪ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ በማሳየትና ልምዱን በማካፈል ተጋጣሚውን የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚን 4ለ2 አሸንፎ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው የተጀመረውን የመልካም ግንኙነት መንፈስ ለማጠናከር እንደማስታወሻ ይሆን ዘንድ የአፄ ቴወድሮስን ምስል ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ልዑካን ቡድን መሪ ለዶ/ር ዳኛቸው ንግሩ አበርክተዋል፡፡

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው በመልዕክታቸው በዝግጅቱ የታደሙትን ሁሉንም አመስግነው የፕሮፊሰር መኮነን አሰፋ 3ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲከበር ፕሮፊሰሩ አገራቸውንና አካባቢያቸውን በቅንነት ማገልገላቸው ይታወሳል ብለዋል፡፡ በተለይም ለደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በርካታ ፕሮጀክቶችን ከውጪ ሀገር በማምጣት ከፍተኛ ገንዘብ ያስገኙ፣ የደብረ ታቦር እና ሁመራ ሆስፒታልን ያስገነቡ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የጤና ረዳት ት/ቤት ደብረ ታቦር በማስከፈት የጤና ተጠሪ ስልጠና ያስጀመሩ፣ በርካታ ጤና ጣቢያዎችን ያሰሩና እና በጤና መኮነንነትና ኃላፊነት ያገለገሉ መምህርና ተመራማሪ የበጎ ሰው አርያችን ነበሩ ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡

ደ/ር አነጋግረኝ በመጨረሻም  ‹‹ ትምህርት የሰውን ልጅ ህይወት እስካልቀየረ ድረስ ምንም ነው›› የሚለውን የፕሮፊሰር መኮነን አሰፋን እምነት የሚያንፀባርቀውን ንግግራቸውን አስታውዋል፡፡

አርቆ አሳቢዎችና የሀገር ባለውለታዎች በስራዎቻቸው ሲታዎሱ ይኖራሉ!