የፀረ ሱሰኝነት ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ

ዩኒቨርሲቲዎችን መሰረት ያደረገ የፀረ ሱሰኝነት ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄን ለማጠናከር ውይይት ተካሄደ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኤች. አይ. ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ከጤና ሚኒስቴር ፣ ከኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን፣ መቋሚያ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት፣ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴርና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዩኒቨርሲቲዎችን መሰረት ያደረገ የአደንዛዥ እፆች ተጠቃሚነትን እና ሱሰኝነትን ለመከላከል የማህበረሰብ እንቅስቃሴ ለማጠናከር የአቅም ግንባታ አውደ ጥናት መጋቢት 24/2013 ዓ.ም ተካሄደ ፡፡

በዓውደ ጥናቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ግንኙነትና ተግባቦት ዳይሬከተር ዶ/ር ታደሰ አክሎግ እንደተናገሩት የአደንዛዥ ዕፆች ሱሰኝነት ችግር አለም አቀፋዊ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ጉዳይ መዘዙ ፈርጀ ብዙ የሆነ የጤና ችግር እንደሆነ አመልክተዋል አክለውም በአንዳንድ የዓለማችን አገራት የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት የግለሰብና እና የማህበረሰብ ችግር እየሆነ ይገኛል ብለዋል፡፡ ችግሩ በማንኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኝን ማህበረሰብ የሚጎዳ ቢሆንም በተጋላጭነት ደረጃ ወጣት የሚባለውን የህብረተሰብ ክፍል እንደሚያጠቃ ጥናቶች እንደሚያመላክት አመላክተዋል፡፡

ኃላፊው አያይዘውም መንግስት ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት የዘገየ ቢሆንም በቅርቡ የአንዛዥ ዕፅን ለመቆጣጠር የህግ ማዕቀፍ ያወጣ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ይህንንም ተንተርሶ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ከሚመለከታቸው የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና ማህበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም ለችግሩ ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎችን ያካተተ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡

በውይይቱም በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የክፍለ ከተማ ተወካዮች፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ባለሙያዎችና መምህራን ተካፍለውበታል፡፡ በውይይቱ ሁለት ጥናታዊ ፅሁፎች እና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎችን መሰረት ያደረገ የአደንዛዥ እፆች ቁጥጥር እና ክትትል ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ ቀርቧል፡፡ ከተሳታፊዎችም በርካታ መረጃዎች ገንቢ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ በዚህም ሁለንተናዊ እና ቅንጅታዊ ብሎም ተቋማዊ አሰራር እንዲዘረጋ የጋራ መግባባት ተደርሷል፡፡ በዚህ በኩል ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጀመረውን ጥረት በማጠናከር ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ማህበረሰባዊ ግዴታውን እንደሚወጣ  በተወካዮች ተገልጿል፡፡