የደረሰ ሰብል መሰብሰብ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች የህልውና ዘማች አርሶ አደሮችን ሰብል ሰበሰቡ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች በይልማና ዴንሳ ወረዳ በህልውና ዘመቻው ግንባር ላይ እየተፋለሙ ያሉ አርሶ አደሮች የደረሰ ሰብል በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ፡፡  

የአጨዳ ስራው በይልማና ዴንሳ ወረዳ በተመረጡ 4 ቀበሌዎች ይከናወናል፡፡ አጨዳው የተጀመረው በስፋት ጤፍ የተዘራበት "አብካ" ቀበሌ ላይ ሲሆን በአካባቢው አርሶ አደሮች አስተባባሪነት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬውን ጨምሮ በርካታ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በአጨዳ ስራው ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ማጨድ የማይችሉ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ብር በማዋጣት የቀን ሰራተኞችን በመቅጠር አብሮነታቸውን አሳይተዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የአጨዳ ዘመቻውን ዓላማ በተመለከተ እንደገለጹት ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ የሚባክነውን ሰብል ከመቀነስ ባሻገር አብሮነትን ለመግለፅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና በመሰል ተግዳሮቶች ምክንያት 30 በመቶ የሚሆን ሰብል እንደሚባክን ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተቀዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ተሰማ አይናለም የአጨዳ ዘመቻው ለሁለት ሳምንት እንደሚቀጥል ገልፀው ዩኒቨርሲቲው በርካታ መምህራንና ሰራተኞች ስላሉት በተለያዩ ቀናት ግቢዎችን በመከፋፈል ተራ ወጥቶላቸው የአጨዳ ዘመቻው በተለያዩ የተመረጡ ቦታዎች እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ጤፍ የታጨደላቸውና በአጨዳው ሲሳተፉ ያገኘናቸው የአካባቢው አርሶ አደሮችና የቀበሌው አስተዳዳሪዎች በስራው ደስተኛ እንደሆኑና ዩኒቨርሲቲው ይህን የስራ ስምሪት ስላዘጋጀ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡