የእንቦጭ አረምን ለመከላከል ደንገል ችግኝ መትከል

የእንቦጭ አረምን ለመከላከል የደንገል ችግኝ መትከል ዘላቂ መፍትሄ መሆኑ ተገለፀ

****************************************************************************

[ሰኔ11/2014ዓ/ም፤ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ] የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ሻጎመንጌ ቀበሌ የእንቦጭ አረምን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል የደንገል ችግኝ ተከላ አካሄደ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከአሁን በፊት በፔዳ ግቢ፤ በአባይ ወንዝ ዳር፣ በባሕር ዳር ከተማ ድብ አንበሳ ሆቴል ፊት ለፊት እና ሚካኤል አባገሪማ ቤተክርስቲያን አካባቢዎች የደንገል ችግኞችን በመትከል የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ከመጠበቅ ባሻገር የእንቦጭ አረምን በዘላቂነት መከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የደንገል ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ንብረት አስራደ እንደገለጹት በሻጎመንጌ ቀበሌ የተጀመረው እንቦጭን በመከላከል ወደ ጣና የሚገባውን ደለል በማስቀረት እንቦጩ ከውሃው አልፎ ወደ እርሻ ማሳው እንዳይስፋፋ ለማድረግ የደንገል ተክሉ ሚናው የጎላ ነው፡፡  ይህ ማለት ደግሞ ውሃው አካባቢ የሚኖሩ የአሳ ዝርያዎችን ጨምሮ እንስሳትም ሆነ ተክሎች ስለማይጠፉ የደንገል ችግኝ ተከላው ብዝሀ-ህይወትን ለመጠበቅ ተመራጭ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ንብረት አያይዘውም በአንድ ወቅት የሰሙት የጓደኛቸውን አባባል ተውሰው‹‹ ጣና ያለ ደንገል ሰው ያለ ኩላሊት አይኖርም›› በማለት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በየአመቱ 98 ሺህ ብር እንቦጭን ለመከላከል ቢመድብልንም ከቦታው እርቀት አንጻር ለክትትል እና የደንገል ችግኝ ለማጓጓዝ የትራንስፖርት ችግርን እንደተግዳሮት አንስተዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ነፃነት በየሮ በበኩላቸው ከዚህ በፊት እንቦጭን ለመከላከል በሰው ሃይል እና በማሽን የተሞከረ ቢሆንም አሁን ላይ የደንገል ተክል እንደ ዘላቂ አማራጭና መፍትሄ ተወስዷል፡፡ በዚህም ያጋጠመን ችግር በሚተከልባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ህብረተሰብ ግንዛቤ አናሳ መሆን እና የስራ መሳሪያዎች እጥረት መኖሩን ገልፀዋል፡፡

በሻጎመንጌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር አማረ ማንዴ ከአመታት በፊት እኔን ጨምሮ የአካባቢው ህብረተሰብ ከሐይቁ አሳ በማስገር ተጠቃሚ ነበረ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን እንቦጭ እንዲስፋፋ ያደረገው አንዱ ደለል ወደ ሀይቁ መግባት ስለሆነ በደንገል ተክል ደለሉን በመያዝ አካባቢው ያጣውን የአሳ እርባታ ለመመለስ የሚደረገው ሙከራ መልካም ነው ብለዋል፡፡