"የአለመግባባት መንስኤዎችና መፍትሔዎች" - መጽሐፍ ምረቃ

"የአለመግባባት መንስኤዎችና መፍትሔዎች" የተሰኘ መጽሐፍ ምረቃ ተካሄደ
==============================================
በሙሉጎጃም አንዱዓለም
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ውስጥ በጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ በሆኑት በአቶ ሙሉጌታ ነቅዓ “የአለመግባባት መንስኤዎችና መፍትሄዎች” በሚል ርእስ በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰርቶ የተፃፈው ባለ አምስት ምዕራፍ መጽሐፍ ሚያዚያ 01/2013 ዓ.ም በነባሩ የሴኔት አዳራሽ ተመረቀ፡፡
መጽሐፉን የገመገሙት የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን አቶ አበበ አሰፋና ዶ/ር ታየ ደምሴ ሲሆኑ መድረኩን በመምራት ያወያዩት ደግሞ ዶ/ር ፋንታሁን አየለ ናቸው፡፡
አቶ አበበ ለደራሲው ታላቅ ምስጋና አቅርበው መጽሐፉ አምስት ምዕራፎች እንዳሉትና እያንዳንዱ ምዕራፍ የተነሱትን የሀሳብ ፍሰት ቅደም ተከተል በመጠበቅ ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል በሆነ መልኩ መፃፉን ገልፀዋል፡፡
አቶ አበበ በማስከተል መጽሐፉ ሁሉንም የአለመግባባት ዓይነት የዳሰሰ፣ ማለትም ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ አልፎም እስከ ሃገር ያሉትን የአለመግባባት አይነቶችና መንስኤዎች ከነመፍትሄዎቻቸው ለአንባቢያን ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም መጽሐፉ ስለ አለመግባባት ምንነትና መፍትሄው ክህሎትን የሚያዳብር መሆኑና ለጆግራፊ እና ለስነ-ዜጋ መምህርም ሆነ ተማሪ እንደ ዋቢ መጽሐፍት ሆኖ እንዲያገለገል ታልሞ የተፃፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ታየ ደምሴም በበኩላቸው የመጽሐፉን ይዘትና ከይዘት ባሻገር ብለው ያቀረቡት ሰፊ ትንተና ከመጽሐፉ ጠንካራ ጎን ጀምረው በአማርኛ ቋንቋ ተጽፎ ለሁሉም ማህበረሰብ በቀላሉ ተደራሽ መሆኑ በመግቢያው ላይ አንባቢያን መጽሐፉን ሲያነቡ በውስጡ የሚያገኟቸውን አጠቃላይ ሃሳብ ጨምቆ መያዙ ፣በጥናትና ምርምር የተደገፈ መሆኑ፣አግባብነት ባላቸው ምዕራፎችና ንዑሳን ክፍሉች የተከፈለና የአረፍተ ነገሮች በቀላል ቋንቋ መፃፋቸው፣እንዲሁም የቀረቡት ንድፈ ሃሳቦች ሁሉም ማህበረሰብ በሚረዳው መልኩ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ታየ አክለውም ከይዘት ባሻገር የማተሚያ ቤቱ ጥራት ውስንነት መኖሩንና አንዳንድ መስተካካል ያለባቸው ሃሳቦች እንዲሁም የቃላት ግድፈቶችን በቀጣዩ እትም መስተካከል እንደሚገባቸው ጠቁመው ደራሲው ይህን የመሰለ መጽሐፍ ስላበረከቱ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የመፅሃፉ ደራሲ አቶ ሙሉጌታ ነቅአ በመፅሃፉ ዝግጀት ዙሪያ እና መፅሐፉን ለመፃፍ ምን እንዳነሳሳቸው አብራርተዋል፡፡ ደራሲውም የሀገራችን ኢትዮጲያ በውጥረት ውስጥ መሆን፣ የዕርስ በርስ ግጭቶች መስፋፋታት፣ እንዲሁም የማህበረሰብ አንቂዎች ተጨባጭ ባልሆነ መረጃ ተነስተው መነሻና መድረሻው ባልታወቀ ሀሳብ ሲባዝኑ መታዘባቸው መጽሐፉን ለመፃፍ እንዳነሳሳቸው ገልፀው የ6 ዓመታት የጥናት ውጤቶችን መሰረት በማድረግ መፃፋቸውን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም በመፅሀፍ ምረቃው ላይ የተገኙት ታዳሚያን ደራሲውን አመስግነው መጽሐፉ ወቅቱን ያማከለ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ገልፀው ለወደፊት የሚፅፉት ምሁራን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚበረታቱበት መንገድ ቢመቻች የሚል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም መፅሐፍ ማሳተም የአንድ ምሁር የመጨረሻው ትልቅ አበርክቶ እንደሆነ በመጥቀስ ይህን መሰል መፅሐፍት ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ የማስተዋወቅ ስራው ላይ ዩኒቨርሲቲው፣ ሚዲያዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን ማድረግ እንዳለባቸው በአፅንኦት ተጠቁሟል፡፡
በእለቱ የመፅሐፉ ደራሲ፣ ዶ/ር ፋንታሁን አየለ (በአወያይነት)፣ አንጋፋ ምሁራንና የደራሲው የስራ አጋሮች፣ ገምጋሚዎች፣ ሌሎች ከተለያየ የጥናት መስክ የመጡ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡