የተማሪዎች እንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብር

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብር አካሄደ

በወንዳለ ድረስ

 

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል በ COVID 19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው የቆዩ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲው መመለስ ምክንያት በማድረግ አዝናኝ የኪነጥበብ ስራዎችንና፣አስተማሪ መልዕክቶችን በማቅረብ፣‹‹የእንኳን ደህና መጣችሁ›› ዝግጅት አካሄዷል፡፡

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ ዝግጅቱን የከፈቱት ሲሆን በመክፈቻ ንግግራቸውም ‹‹የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሀገራዊ ተቆርቋሪነትና የሀላፊነት ስሜት የሚሰማቸው ሊሆኑ ይገባል›› ሲሉ በአፅንኦት ጠቁመዋል፡፡

 

ባህል ማዕከሉ በዕለቱ ታዋቂውን የሀገራችን የፍልስፍና ምሁር ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን እንግዳ አድርጎ የጋበዘ ሲሆን ዶ/ር ዳኛቸው ‹‹ዩኒቨርሲቲ ምንድን ናት? የዩኒቨርሲቲ ተማሪስ ምን ስነምግባር ሊኖረው ይገባል?›› በሚል ርዕስ ቁልፍ ንግግር አቅርበዋል፡፡ በንግግራቸው ‹‹ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል ናት፣ዩኒቨርሲቲ የራሷ ዓላማና ግብ አላት፤ ይህንን ለማንም አሳልፋ መስጠት የለባትም፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ሲወጣ ‹ዲስፕሊንድ› (ስነምግባር የታነፀ) አእምሮ ይዞ ሊወጣ ይገባዋል›› ብለዋል፡፡

 

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የአስዳደር ጉዳዩች ም/ፕሬዚዳንት ተወካይና ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ገደፋው ሽፈራው ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች መመለስ የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ ከገለፁ በኋላ ኮቪድን የመከላከል ስራን ታሳቢ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን መማሪያ፣ መመገቢያ ክፍሎችን፣ ቤተመፅሀፍትና ቤተ ሙከራዎች በሚገባ አዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ኮቪድን በመከላከልም ሆነ ሰላምን በመጠበቅ ሂደት ተማሪዎች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

 

የስነባህሪ ኮሌጅ መምህር የሆኑት አቶ ታምሩ ደለለኝ በዝግጅቱ  ላይ  ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀውን የጥበብና የሰላም ፍኖተ ካርታ ያቀረቡ ሲሆን ‹‹ትምህርት ማለት የአእምሮ፣ የስነልቦናና የአካል ቅንጅታዊ ዑደት ነውና ሁላችንም ከዚህ እሳቤ አንፃር ራሳችንን ካስተማርን ሰላማችን መጠበቅ እንችላለን›› ብለዋል፡፡

 

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር አስቴር ሙሉ  ‹‹ሰው ያለ ባህል›› እንስሳ ነው ብለው በመቀጠልም  ሀገራችን ኢትዮጵያ  በርካታ ስብዕናዎችን ማጎልበት እና ማጎናፀፍ የሚያስችሉ ባህሎች ባለቤት ናት ብለዋል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከልም ስብዕናው የጎለበተና የሀገሩን ባህል ጠንቅቆ ያወቀ ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድ የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡ ይህንን በማድረግ ሂደትም ወጣቶች ዋና ባለድርሻ አካላት ናችሁና ባህል ማዕከሉ ተልዕኮውን ለማሳካት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ አጋዥ ሁኑ ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡