የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጤና እግር ኳስ ቡድን አሸነፈ

የዓመቱ የጤና እግር ኳስ ውድድር በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፊደሬሽን ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ጋር በጋራ በመሆን ከጥር 09 እስከ ሚያዝያ 19/2013 ዓ.ም ሲያካሂድ የነበረው የመንግስትና የግል ተቋማት ሰራተኞች የእግር ኳስ የጤና ውድድር በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡
 
አመታዊ ውድድሩ የተጀመረው በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ ከተለያዩ የግልና የመንግስት ተቋማት በመጡ 32 የጤና ቡድኖች ሲሆን በአራት ምድብ ተከፋፍለው ማጣሪያው ተከናውኗል፡፡ በውድድሩ ለግማሽ ፍፃሜ ካለፉት ሶስቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቡድኖች ሲሆኑ ለፍፃሜ ጨዋታ የደረሱት የምድብ ሐ አንደኛ በመሆን ያጠናቀቀው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና የምድብ ለ አንደኛው የዘንዘልማ ካምፓስ ነበሩ፡፡ በፍፃሜ ጨዋታውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ ግቢ ዘንዘልማ ካምፓስን 2 ለ 0 በማሸነፍ ሻምፒዮን በመሆን የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በዚህም ዘንዘልማ ካምፓስ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆን BIT የጤና እግር ኳስ ቡድንም ኢትዮ ጫማን በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃ ሆኖ የነሀስ ሜዳሊያ በመውሰድ አጠናቋል፡፡
 
አቶ ዘላለም መንግስቱ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት በውድድሩ ጉልህ አስተዋጽኦ ለነበራቸው የዕውቅና የምስክር ወረቀት የሰጡ ሲሆን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፔዳ ግቢ እግር ኳስ ጤና ቡድን ኮከብ አሰልጣኝ ዳንኤል ሀብታሙ፣ ኮከብ ተጨዋች ሀይለየሱስ ሙሉአለም እንዲሁም ከBIT የጤና እግር ኳስ ቡድን ኮከብ ጎል አግቢ ታደሰ ሙሉቀን፣ ኮከብ በረኛ ፈንታሁን ክንዴ ሁነው ተመርጠዋል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ ግቢ ጤና ቡድንን ሲያስተባብሩ ያገኘናቸው መምህር እና ዋና አሰልጣኝ የሆኑት አቶ ጠቢቡ ሰለሞን ካሁን በፊት የመጡበትን ሂደት ማለትም ጥሎ ማለፉ በጣም ፈታኝ እንደ ነበር አስታውሰው፤ የዘንድሮ ተወዳዳሪዎች ጠንክረው የቀረቡበት ቢሆንም ቡድናቸው የነበረውን ጫና ተቋቁሞ ሻምፒዮና ሆኗል ብለዋል፡፡ አቶ ጠቢቡ አመቱን ሙሉ ጊዚያቸውን አጣበው ልምምድ በማድረግ ላሳዩት ተነሳሽነት ሁሉንም ተጫዋቾች አመስግነዋል፡፡
በዕለቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ ተገኝተው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለወጡ ቡድኖች የመዳሊያ ሽልማት ሰጥተዋል፡፡ እንዲሁም የ2013 ዓ.ም የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ የባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ የጤና ቡድን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ እጅ ተረክበዋል፡፡
 
በመጨረሻም የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አሰፋ ለውድድሩ አሸናፊ ለሆነው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጤና እግር ኳስ ቡድን የተዘጋጀውን የዋንጫ ሽልማት አበርክተዋል፡፡