የስርዓተ ትምህርት ግምገማ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተቋም የስርዓተ ትምህርት ግምገማ አካሄደ
---------------------------------------------------------------------------------------------
በሙሉጌታ ዘለቀ
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም የአደጋ መከላከልና ዘላቂ ልማት ትምህርት ክፍል አዲስ ለሚከፍተው የ3ኛ ድግሪ የአደጋ ስጋት መከላከል ሳይንስ ጥናት ዘርፍ የስርዓተ ትምህርት ግምገማ በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ተካሂዷል፡፡
 
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር አዳነ ተስፋዬ በአሁኑ ጊዜ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውንና በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተናግረው ይህንን አደጋ የሚቀንሱና የሚተነትኑ እንዲሁም አመራር የሚሰጡ ባለሙያዎችን ለማፍራት የዚህ ፕሮግራም መከፈት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ወደ እለቱ ዋና ውይይት እንደ መንደርደሪያ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተቋም ተመራማሪና መምህር የሆኑት ዶ/ር ምንተስኖት አዘነ አዲስ ስለሚከፍተው የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪ የስርዓተ ትምህርት ረቂቅ እና ስለተደረገው የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር በላይ ስማነ እና ፕሮፌሰር ወልደ አምላክ በእውቀት በረቂቅ ስርዓተ ትምህርቱ ላይ ጥልቅ የሆነ ግምገማ ቀርቧል፡፡ እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት በመጡ እንግዶችና ታዳሚዎች ሀሳቦችና አስተያየቶች ቀርበው በስርዓተ ትምህርት አርቃቂ ኮሚቴውና በፕሮግራሙ ተሳታፊ በሆኑ መምህራን ግብረ-መልስ እና ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
 
በመጨረሻም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር አዳነ ተስፋዬ በውይይቱ ላይ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር የፕሮግራሙ መከፈት ለሀገራችን ብሎም በአፍሪካ ደረጃ ተቋሙ ተወዳዳሪ እንዲሆንና የሰለጠኑና ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎች ለማፍራት ተቋሙን በሰው ሀይል፣በቤተ ሙከራና በትምህርት ቁሳቁስ የተሟላ በማድረግ ረገድ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በኩል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር አዳነ አክለውም ከሚቀጥለው መስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሁለት ወይም አራት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን ተቋሙ ማስልጠን እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡ በእለቱ የተገመገመውን የስርዓተ ትምህርት ረቂቅ አስመልክቶ ዳይሬክተሩ ሲናገሩ ተቋሙ የተሰጡትን ግብዓቶች በማካተት እንደገና በባለሙያ እንደሚያስተች እና አስፈላጊውን በማሟላት ወደ ተግበራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡