የሰብል ዝርፊያና ውድመትን ማካካስ

በክልሉ የደረሰውን ከፍተኛ የሰብል ዝርፊያና ውድመትን ለማካካስ የመስኖ ልማት ንቅናቄ ተጀመረ

*****************************************************************************

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በክልሉ በትግራይ ወራሪ ኃይል ምክንያት የደረሰውን ከፍተኛ የሰብል ዝርፊያ እና ውድመትን ለማካካስ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ አዲስ ልደት ቀበሌ የመስኖ ስንዴ ልማት ንቅናቄ የማስጀመሪያ መርኃ ግብር ሕዳር 14/2014 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው "ሁላችንም ማድረግ የሚገባን እና ማድረግ የምንችለውን በማድረግ ለወገኖቻችን ልንደርስ ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቆጋ መስኖን በመጠቀም 56 ሄክታር ላይ የሚሰራቸውን የምርምር ሳይቶችን መነሻ በማድረግ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ አዲስ ልደት ቀበሌ የመስኖ ስንዴ ልማት ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር  አርሷደሩ ዘንድ  ያልተለመዱ የአሰራር ሂደቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ  በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል የወደመውን ምርት ለማካካስ እና ለችግር የተዳረጉ ወገኖችን ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ኃይለማሪያም ከፍያለው ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በከፈተው ጦርነት በአማራ ክልል ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፋ ረሀብ  መጋለጣቸውን   ጠቁመው፤  ህብረተሰቡ የቁጠባ ባህልን በማዳበር ካሁን በፊት በዘልማድ የሚደረጉ ድግሶችን በመቀነስ የተሰበሰበውን ምርት በቁጠባ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረው  እንደተለመደው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ማምረት ሳይሆን ሦስት ጊዜ በማምረት ሕዝባችንን ከረሀብ መታደግ እንደሚገባ ዶ/ር ኃይለማሪያም በአፅኖት ተናግረዋል፡፡

 

በዛሬው እለት ስራ የጀመረው ኩታ ገጠም የመስኖ ስንዴ ልማት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለአርሷሮች የምርጥ ዘር ፣ የማዳበሪያ ፣ የሙያ ድጋፍና የማማከር አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን የትራክተርና የኮምባይነር ግዥ ለመፈፀም  በሂደት ላይ  መሆኑ ተገልጿል፡፡ በኩታ ገጠም የሚለማው 502 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን ከ894 በላይ  አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ በመርሃ ግብሩ  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘን ጨምሮ ም/ፕሬዚዳንቶችና የቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ እና  ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡