ወላጆቻቸውን ላጡ እና አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ድጋፍ

 

 

የባሕር ዳር ዪኒቨርሲቲ ኤች.አይ .ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ዳይሬክቶሬት በኤች.አይ ቪ/ኤድስ ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡ እና አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ድጋፍ አደረገ፡፡

***************************************************************************************************

የባሕር ዳር ዪኒቨርሲቲ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ዳይሬክቶሬት ከእድገት በስራ ማህበር ጋር በመተባበር በባሕር ዳር ከተማ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡና አቅም ለሌላቸው ተማሪዎ ሕዳር 9/2014 ዓ.ም በጥበብ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የምግብ ድጋፍ አደረገ፡፡

የባሕር ዳር ዪኒቨርሲቲ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ሲስተር ምህረት ጌታቸው በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ፕሮግራሙን ከፍተው ማህበሩ በቫይረሱ ምክናያት ወላጆቻቸውን ያጡ እና ረዳት የሌላቸውን ተማሪዎች ከጎናችሁ ሰው አለ ብሎ ለማበረታታት የተቋቋመ ነው ብለዋል፤እንዲሁም ተማሪዎችን ነገ ሌላ ቀን እንደሆነ አስባችሁ እንድትበረታቱ፤ ችግራችሁን እያሰባችሁ ወደኋላ እንዳትቀሩ በማለት ወደ ፊትም እገዛው እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት የሴቶች ወጣቶች ህጻናት እና ኤች.አይ ቪ ዳይሬክተር ሲስተር ማርታ አስማረ በበኩላቸው ማህበሩ የተቋቋመበትን አላማ ከገለፁ በኋላ ተማሪዎቹን በትምህርታቸው ጠንካራ እንዲሆኑና ሌሎቹን እንዲያግዙ እና እንዲንከባከቡ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም ከአምስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመጡ 25 ተማሪዎች ለምግብ አገልግሎት የሚውል ለእያንዳንዳቸው 10 ኪሎ ግራም ማካሮኒ ድጋፍ ከተደረገ በኋላ የእድገት በስራ ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አበባው ንጋቴ ወደፊት በትምህርታቸው ጎበዝ ተማሪዎችንም ማዕቀፍ አድርገው እንደሚሰሩና አሁን በማህበሩ የታቀፉ ተማሪዎች በሚመጡበት ጊዜ ውጤታቸውን በማየት ጥሩ ነጥብ ለሚያስመዘግቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡