አዲሱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ የስራ ጉብኝትና መደበኛ ስብሰባ

አዲሱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ የስራ ጉብኝትና መደበኛ ስብሰባ በማድረግ ስራውን ጀመረ

*************************************************************************************

(ሰኔ 11/2014 ዓ/ም፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ) አዲሱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ የስራ ጉብኝትና መደበኛ ስብሰባውን በማድረግ ሰኔ  11/2014 ዓ.ም ስራ ጀመረ፡፡

ስራ አመራር ቦርዱ ስራ በጀመረበት በዚሁ ቀን ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር ፣  በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት  እስካሁን የሄደባቸው ርቀቶች  እና ያስመዘገባቸውን  ውጤቶች  አስመልክቶ የስራ ጉብኝቱን የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ተቋም የቢዝነስ ኢንኩቤሽንና ቴክኖሎጂ ኢንተርፕረነርሺፕ ማዕከልን ተጠቅመው በሀገር ዓቀፍ ደረጃ  ተወዳድረው ተሸላሚ የሆኑ እና በተማሪዎች የተሰሩ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችን ፣ የስቴም ማዕከልን፣ እና የጃን ሞስኮቭ ቤተ መጽሀፍትን ፣ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ተቋም  የስራ እንቅስቃሴን ፣ በፔዳ ግቢ የተገነባውን ስፖርት አካዳሚ፣ የማሪታይም አካዳሚ ወርክሾፕ እና በጥበበ ግዮን ሪፈራል ሆስፒታል የተገነባውን ግዙፍ የሪሰርች ማዕክል እና የኦክስጅን ማምረቻ  እና ኮሌጁ የሰራቸውን  ሌሎችንም  አመርቂ ስራዎችን  እና በ (ICT) ዳይሬክቶሬት ክፍል የበለፀጉ እና  ኢ-ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ የተሰሩ እንደተማሪዎች የመረጃ አስተዳደር ስርዓት (SIMS)፣  የንብረት ግዥ አስተዳደር ስርዓት (PMS)፣  የተቋሙ የኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ክፍል እያከናወናቸው ያሉ  በኦንላይን ለመማር የሚያስችሉ አሰራሮችን (e-learning) ን በመተግበር  የተከናወኑ ስራዎችን  ቦርዱ ምልከታ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም አዲሱ የስራ አመራር ቦርድ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲን የውሃ እጥረትን ለማቃለል ከከተማው ወጣ ብሎ በሰባታሚት ከተማ የተቆፈረውን የውሃ ጉድጓድ ጎብኝተው ለስራው መሳካት ከፍተኛ አስተዋፆ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ አቅራቢነት ከቦርዱ ሰብሳቢ ከአቶ አዳም ፋራህ እጅ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡  

ይህንን ተከትሎ  ቦርዱ ከሰዓት በኋላ ባደረገው ውይይት ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የዩኒቨሪሲቲውን  የስራ  ክንውን አስመልክቶ  ለአዲሱ የሥራ አመራር ቦርድ ማብራሪና ገለፃ አድርገዋል፡፡  የአዲሱ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አደም ፋራህ  ዩኒቨርሲቲው በምርምር በቴክኖሎጂ ስራ  ፈጠራ እና በጤናው መስክ እየሰራው ባለው ስራ መደሰታቸውን ገልፀው ዩኒቨርሲቲው  የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ ወደፊት  ለሚሰሩ ስራዎች የጋራ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡  በጉብኝቱ ወቅት የተመለከቷቸውን የዩኒቨርሲቲውን ጠቅላላ የስራ እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ ከቦርዱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ም/ፕሬዚዳንቶች  ማብራሪያ እና ገለፃ አድርገዋል፡፡ ቦርዱ የዩኒቨርሲቲውን የ2014 ዓ.ም የሁለተኛውን ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት  ገምግሟል፡፡ የስራ አመራር ቦርዱ በክቡር አቶ አደም ፋራህ የሚመራ ሲሆን ሌሎች የቦርድ አባላትም ተገኝተዋል።