አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ

የብር አዳማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ

ትዕግስት ዳዊት 

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢን/ስት/ኮም ም/ፕረዚደንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መንግሥት ባወጣው የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650 ለዩኒቨርስቲዎች ከተሰጣቸው ሦስት ተልዕኮዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን በፍላጎት ላይ የተመሰረተ የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት በተለያየ ደረጃ እየተገበረ ይገኛል፡፡ ይህ በእለቱ የተከናወነው የትምህርት ቤት ስራ ምረቃም የዙህ ጥረት አንድ አካል እንደሆነ ዶ/ር ዘውዱ ገልፀው ይህን መሰል ስራዎችም ሞዴል መደረግ በሚችሉበት ደረጃ እንደሚሰሩም ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ዘውዱ አክለውም ለትምህርት ቤቱ ግንባታ እውን እንዲሆን ከተለያዩ ባለሙያዎች እና የመንግስት ኃላፊዎች ትብብር ባሻገር ኤፍጂሲኤፍ (FGCF) የተሰኘው የግብረ ሰናይ ድርጅት ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡ ይህም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም. ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ጋር በትምህርት ዘርፍ በትብብር ለመስራት ላደረጉት ስምምነት ተግባራዊ ማሳያ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የኤፍጂሲኤፍ (FGCF) አማራ ክልል አስተባባሪ አቶ አቢወት አሸናፊ የተገነቡትን 16 መማሪያ ክፍሎች፣ አንድ አስተዳደር ሕንፃ ፣ አንድ ቤተ-ሙከራ እና አንድ ቤተ-መጻሕፍት በምረቃ መርሃግብሩ ለተገኙት አካላት ያስጎበኙ ሲሆን የህንጻውን ክፍሎች እንዲሁም ውስጣቸው ስላሉት ቁሳቁሶች እና ስለሚሰጡት አገልግሎቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አቶ አቢወት በቀጣይ ደግሞ በዋነኛነት የትምህርት ቤቱን ምድረ-ግቢ ማሳመር፣ ለመምህራን የተለያዩ አቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት እንዲሁም ለተማሪዎች የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ለመስጠት እንደታቀደ ገልፀዋል፡፡ የግንባታውን ወጪ ሶስት አካላት የሸፈኑት ሲሆን ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ 30%፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ወረዳው 40%፣ እንዲሁም ኤፍጂሲኤፍ (FGCF) 30%ቱን አዋጥተዋል፡፡ በትምህር ቤቱ ምርቃት ላይ የተገኙት የቋሪት ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ የፀዳው አጥናፍ እንደተናገሩት ወረዳው በትምህርት ጥራት በኩል ሰፊ ችግር ያለበት በመሆኑ ይህ ግንባታ ሲገነባ ሰፊውን ችግር ለማቃለል የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ተማሪዎች ከፈራረሰ ትምህርት ቤት ወጥተው ደረጃውን በጠበቀ ህንጻ እንዲማሩ በመደረጋቸው የትምህርት ጥራት እንደሚሻሻል ጠቁመው የተገነባውን ህንጻ ማህበረሰቡ እንደራሱ እንዲንከባከበው አሳስበው ለዚህ ህንጻ መገንባት አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት የአክብሮት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በመርሃግብሩ የተገኙት የተማሪ ወላጆች በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ በ1972 ዓ.ም የተገነባ እንደነበረ ጠቁመው አሁን ላይ አገልግሎት ለመስጠት የማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ እያለ አዲሱ ህንጻ መገንባቱ ከሃሳብ እና ጭንቀት እንደታደገቸው ገልጸዋል፡፡ አክለውም አሁንም ያልተሟሉላቸው እነደ ውሀ እና መብራት ያሉ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉላቸው ጥያቄአቸውን አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ወላጆች ልጆቻቸውን በርትተው እንደሚያስተምሩ ተናግረው ት/ቤቱን ወደ ሁለተኛ ደረጃ እንደሚያሳድጉትም ቃል ገብተዋል፡፡