ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም ክልላዊ የምርጥ ቴክኖሎጂ ሽግግር አውደጥናት

ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም ክልላዊ የምርጥ ቴክኖሎጂ ሽግግር አውደጥናት አካሄደ

***********************************************************************************

በሙሉጌታ ዘለቀ

ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም ግብርናን መሰረት ያደረገ መተዳደሪያን ቀጣይነት በኢትዮጵያ እውን ማደረግ ፕሮግራም በኔዘርላድ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚሰራ ሲሆን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና የወልደያ ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም የሦስት ዓመት የስራ እንቅስቃሴዎችን እና በፕሮግራሙ ቀጣይነት ዙሪያ ክልላዊ የምርጥ ቴክኖሎጂ ሽግግር አውደ ጥናት ከየካቲት 6-7/2013 በጎንደር ከተማ አካሄዷል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም ባሳለፈው የሦስት ዓመታት የቆይታ ጊዜ ምርጥ ተሞክሮው በዘር፣ በአቅም ግንባታ እና በስርዓት ዝርጋታ ላይ የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ጋር በመቀናጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ አስር ወረዳዎች ላይ የአርሶ-አደሩን ሕይወት የቀየረ ውጤታማ ስራዎችን ማከናዎኑ ተገልጿል፡፡

አውደጥናቱን በንግግር የከፈቱት ቤነፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ዋና ማኔጀር የሆኑት ዶ/ር ቴወድሮስ ተፈራ እንዳሉት ፕሮግራሙ ባለፉት ሦስት ዓመታት የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ በሀገራችን ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ምርጥ ተሞክሮዎችን በማልማት፣ በማላመድ፣ በማረጋገጥ ረገድ አርሶ-አደሩ ላይ የተሰራው ስራ አርኪና ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ አክለውም ፕሮግራሙ በሰራው ጠንካራ ስራ በሀገራችን በተለዬ ሁኔታ በአማራ ክልል በርካታ በሴፍትኔት የታቀፉ አረሷደሮች ከተረጅነት በመውጣት ራሳቸውን በመቻል ለሌሎች ሞዴል የሚሆኑ እማውራና አባውራ አርሷደሮች ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቤነፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም የቆይታ ጊዜው እያበቃ በመሆኑ ፕሮግራሙ የጀመራቸውን የልማት ስራዎች አርሷሩን  በዘላቂነት ከተረጂነት የሚያላቅቅ በመሆኑ  በመስኩ ያሉ አጋር ተቋማትን አቅም በመገንባት  ውጤታማ ስራ እንደሚጠበቅ በአፅኖት ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት  ማናጀር የሆኑት ዶ/ር አልማዝ ጊዜው በአውደጥናቱ ላይ የፕሮግራሙ የስራ እንቅስቃሴን የሁለት አመት የስራ ክንዉን አቅርበዋል፡፡ ቤነፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ክላስተር በምዕራብ አማራ በተመረጡና የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ አስር ወረዳዎች ላይ በስፋት መስራቱን ተናግረዋል፡፡ ከወረዳዎቹ መካከል ሊቦ ከምከምና እና እነብሴ ሳር ምድር ወረዳዎች የምርምር ወረዳዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ቀሪዎቹ ስምንት ወረዳዎች እብናት፣ ላይ ጋይንት፣ ታች ጋይንት፣ ስማዳ፣ ሸበል በረንታ፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴ፣ ዳባትና ወገራ ወረዳዎች  በማራዶ የፓፓያ ዝርያ አመራረት፣ በምግብ ገብስ አመራረት፣ የተመረጡ የድንች ዘር በማቅረብ፣ የአንድ ጥማድ ፓኬጅ አተገባበር እና የተሳቦ ቀልዝ ብስባሽ አዘገጃጀትና ጥቅሙን በተመለከተ የማስፋፊያ ስራ የተሰራባቸው ወረዳዎች መሆናቸው በስራ ክንዉን ፁሁፉ ተጠቅሷል፡፡ ቤነፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ክላስተር በሴፍትኔት ፕሮግራም የታቀፉና የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ አርሷደሮችን በመመልመል የፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀው የፕሮግራሙን የስራ እንቅስቃሴ፣ ዋና ዋና ስኬቶችን፣ የነበሩ ምቹ ሁኔታዎች፣ የተገኙ ልምዶችን እና በሂደቱ ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ በስራ ክንዉን ፁሁፋቸው በዝርዝር ቀርቧል፡፡  

በአውደጥናቱ ላይ የቤነፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑ እና የምግብ ዋስትናቸውን ያረጋገጡ ሞዴል አርሶ አደሮች ተገኝተው ለአውደጥናቱ ተሳታፊዎች ገለፃ አድርገዋል፡፡  

በመጨረሻ በአውደ ጥላቱ ላይ የባሕር ዳር እና የወልደያ ዩኒቨርሲቲዎች ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም ባዘጋጁት የስራ ግምገማ ላይ በክልሉ የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች፣የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን እንዲሁም አጋር ፕሮጀክቶች የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተው ቤነፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም የቆይታ ጊዜው እያበቃ በመሆኑ ፕሮግራሙ የጀመራቸውን የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የአጋር ተቋማት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ውይይት ተደርጎበታል፡፡