ባህር ዳርን እንደቤቴ

የዩኒቨርሲቲው  ተማሪዎች የትንሳኤ በዓልን ከባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ጋር አከበሩ

በዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል አስተባባሪነት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የትንሳኤ በዓልን ከባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ጋር አከበሩ ፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ዶ/ር ቃለወንጌል ምናለ የዩኒቨርሲቲው  ተማሪዎች ከከተማው ማህበረሰብ ጋር የፋሲካ በዓልን ማክበራቸው  ትርጉም ያለው ውህደት ከማድረጋቸው ባሻገር  ከባህር ዳር ከተማ ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲመሰርቱ ብሎም ባህር ዳርን እንደቤታቸው እንዲቆጥሩ በማድረግ የዩኒቨርሲቲውንም ሆነ የማህበረሰቡን ገጽታ በመገንባት ስብዕናና ትሩፋት ይጋራሉ ብለዋል፡፡ ይህም ዋና የሆነውን የተማሪዎችን የእውቀት ግብይት ተግባር እና ውጤታማነትን በጉልህ እንደሚያሳድገው ይታመናል፡፡

ዶ/ር ቃለወንጌል አክለውም ባለፈው የገና በዓል በርካታ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ጋር በዓል ማክበራቸውን አስታውሰው ከተለያዩ  የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው የአካባቢውን ታሪክ ፣ባህል እና ቋንቋ  ማወቅ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በቆይታቸውም ባህር ዳርን እንደ ቤታቸው ቆጥረው በትምህርት ገበታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም በአገራችን ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡ መክረው ወደፊት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አምባሳደር እንደሚሆኑ እምነታቸውን ተናግረዋል ፡፡

በመጨረሻም የፋሲካ በዓልን ከበርካታ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር ያሳለፉትን የጣና ፣ የበላይ ዘለቀ፣ የአፄ ቴወድሮስ እና የአፄ ምኒሊክ ክፍለ ከተሞች የወጣቶች ማህበራት አባላትን ፣ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎችን ፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና የእኛ ለእኛ የበጎ ፈቃደኞች ማህበርን ፤ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳሉ እንዲሰማቸው በማድረግ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፆ ባህር ዳርን እንደቤቴ በተሰኘው ፕሮጀክት ስም ዶ/ር ቃለወንጌል ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል ፡፡