በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደረገ
በሶሻል ሳይንስ እና አለምአቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት " የፓለቲካ ታህድሶ ተግዳሮቶችና እድሎች" በሚል ርእሰ ጉዳይ በቀድሞዉ ሰኔት አዳራሽ ዉይይት ተደርጓል።
*********************************************************************
በመድረኩ የዩኒቨርስቲው ፕሬዘዳንት-ዶ/ር ፍሬዉ ተገኘ፣ የአስተዳድር ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት የሆኑት አቶ ብርሃኑ ገድፍ እና ሌሎችም አመራሮች ታድመዋል። አቶ ብርሃኑ ዉይይቱን በንግግር እንዲጀመር ያደረጉ ሲሆን ፣ ዶ/ር ታዬ ደምሴ ፕሮግራሙን መርቶታል። በተጨማሪም በመድረኩ አምስት ያህል ጭብጦች በተወያዮች ቀርበዋል።
እነዚህም ውስጥ አንዱ ጭብጥ ለውጡን እንደገና በአንክሮ ማጤን በሚል ርዕሰ በመምህርት መስከረም አበራ ቀርቧል። መምህርት መስከረም ለውጡ ሲጀምር የነበረው ተስፋን እና አሁን መሬት ላይ ያለዉ ነባራዊ ሃቅ የተራራቀ መሆኑን ሁነቶችን በመጥቀስ አስረድተዋል። እንደ መምህርቷ ይልቁንም ከጅምሩ የለውጥ መሪ ተብለው እውቅና በተሰጣቸው ልሂቃን መካከል ሳይቀር ልዩነች መፈጠሩንም ተናግረዋል። ከዚህም በላይ አምባገነንነት፣ አፈና እና የተረኝነት አዝማሚያ መኖሩንም ጠቁመዋል።
ሌሎች ሁለት ጭብጦች የአማራ ብሄርተኝነትን ማአከል ያደረጉ ነበሩ። በዚህ ዙሪያ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ ት/ቤት ዲን የሆኑት አቶ ተገኝ ዘርጋዉ የአማራ ህዝብ ጥያቄና ምላሹ በሚል ከ ህገ መንግስቱ በመነሳት ተንትነዉ አቅርበዋል። በዚህም የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ፈርጀ ብዙ መሆናቸውን አምነው ዋናው ግን ህገ-መንግስታዊ መሆኑን አብራርተዋል። አቶ ተገኝ የአማራ ህዝብ ችግር ህገ መንግስቱ የፈጠረዉ በመሆኑ ምላሹም ህገመንግስታዊ ማሻሻያ የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ዶ/ር ዉህብእግዜር ፈረደ የአማራ ህዝብ ትግል በሚል ጭብጥ ሃሳባቸውን አጋርተዋል። በዚህም የአማራ ህዝብ እና የሃገረ መንግስት ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ የገባ መሆኑን በመጠቆም የችግሩን መውጫ መንገዶች አመላክተዋል።
በአራተኛ ደረጃ የመወያያ ጭብጥ የነበረው ሃገሪቱ የምትገኝበትን ጅኦፓለቲካዊ ሁኔታ የሚዳስስ ነበር። አቅራቢዉ ረዳት ፕሮፌሰር ባንታየሁ ሽፈራዉ ናቸዉ። አቶ ባንታዬሁ ሃገሪቱ የጀመረችዉ የለውጥ ጉዞ በተቃራኒ ራዕይ ያላቸው የፓለቲካ ሃይሎች ፍትጊያ ምክንያት የተጠበቀውን ያክል ተቋማዊና ህገ-መንግስታዊ ለውጥ ያላመጣ መሆኑን ጠቁመው ችግሩ በዚህ ከቀጠለ ከሃገሪቱ ጅኦፓለቲካዊ ውጥረት እንፃር ወደከፋ ችግር ሊገባ እንደሚችል አመላክተዋል።
በመጨረሻ ላይ የመወያያ ጭብጥ ያቀረቡት አቶ አንተነህ ብርሃኑ ሲሆኑ የጭብጣቸዉ ማጠንጠኛ ርዕስ ጉዳይ የፓለቲካ ተግባቦት ና የፓለቲካ ሽግግር የሚል ሲሆን በዚህ ጉዳይ ለሽግግር ተግዳሮቶችና እድሎች ያሉ መሆኑን አብራርተዋል። የማህበራዊ ሚዲያ እና የነቃ ወጣት መኖሩ የፓለቲካ ሽግግር ሂደትን ሊያሳልጥ እንደሚችል ጠቁመዋል። ይሁንና ማህበራዊ ሚዲያ ና ወጣቶች ተነሳሽነት ጉዳዮች በአግባቡ ካልተከወኑ ጉዳታቸዉ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ዶ/ር ታደስ አክሎግ እና ረዳት ፕሮፌሰር እምቢአለ በየነ በአወያይነት መድረኮችን የመሩ ሲሆን በመድረኩ በሳል እና ገንቢ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበዉ በተወያዮች በኩል ምላሽ ተስጥቶባቸዋል።