በባሕር ዳር ከተማ ዋና የገበያ ማዕከል የሚገኘውን ክፍት ቦታ ማስዋብ ተጀመረ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባሕር ዳር ከተማ  ዋና የገበያ ማዕከል የሚገኘውን ክፍት ቦታ ማስዋብ  ጀመረ

****************************************************************************

(ሰኔ 14/2014 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ባዳዩ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን በዋናው የገበያ ማዕከል የሚገኘውን ክፍት ቦታ በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ስራ መጀመሩን ገለፀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የከተማውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የአረንጓዴ ልማት ስራ በከተማው ውስጥ የሚገኘውን የዋናውን የገበያ ማዕከል የማስዋብና ከዚህ ጋር ተያይዞ  በቀጣይ የሚሰሩ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ፣ ለሕዝብ መገልገያ የሚሆኑ መፀዳጃ ቤቶችን እና የውሃ ተፋሰሶችን ለመገንባት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የምድረ ግቢ ውበት ዳይሬክተር  ዶ/ር  ደሴ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሚሰራው ስራ ላይ የዲዛይን ስራ፣ የማማከር፣ የማቴሪያል እና የሰው ሃይል እገዛዎችን እያደረገ ሲሆን በዛሬው እለት የተጀመረው ቦታውን በአረንጓዴ የማልማት  ስራውን እሰከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም ድረስ በማጠናቀቅ ለከተማ አስተዳደሩ እንደሚያስረክብ ዳይሬክተሩ የተናገሩ ሲሆን በቦታው ላይ የሚሰሩ ቀሪ የግንባታ ስራዎች ከከተማ  አስተዳደሩ ጋር በመሆን የሚተገበር መሆኑም ተገልጿል፡፡