ስፖርት ለህግ ታራሚዎች

ስፖርት ለህግ ታራሚዎች
---------------------------
በሙሉጎጃም አንዱአለም
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከባሕር ዳር ከተማ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የህግ ታራሚዎች የሚሳተፉበት ለሁለት ወራት የሚቆይ ስፖርታዊ ውድድር በማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተጀምሯል::
ለመርሃ ግብሩ ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የማረሚያ ቤቱ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ውብሸት መኮነን በማረሚያ ቤቱ ከሚገኙት ታራሚዎች ከ75% በላይ የሚሆኑት ወጣቶች በመሆናቸውና ስፖርት ለአካላዊም ሆነ ለአእምሮአዊ ብልፅግና ጉልህ ፋይዳ ስላለው ሁሉም ታራሚ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የቅጣት ጊዜውን ጨርሶ ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀል ብቁ ዜጋ እንዲሆን በማሰብ ዩኒቨርሲቲው መርሐ ግብሩን በማዘጋጀቱ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት አካዳሚ ዲን ዶ/ር ዳኛቸው ንግሩ በበኩላቸው ጥሪውን አክብረው ለመጡ ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁና የምስጋና መልዕክታቸውን አስተላልፈው ስፖርታዊ ውድድሩ ለሁለት ተከታታይ ወራት የሚቆይ መሆኑንና ታራሚዎች የቅጣት ጊዜአቸውን ጨርሰው ሲወጡ በአካልም ሆነ በአእምሮ በቅተው እንዲገኙ እንዲሁም ከውድድሩ መልስ ብቁ ዜጋ ይሆኑ ዘንድ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ጨዋታው በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ስፖርት ጤናን፣ፍቅርን ፣ሰላምን፣አንድነትን ስለሚያጎለብት ታራሚዎች የቅጣት ጊዜአቸውን ጨርሰው እስከሚወጡ መነቃቃትን ለመፍጠር አካዳሚው ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ለወደፊት ከስፖርቱ በተጨማሪ ታራሚዎች በሌሎች ሙያዎች እራሳቸውን አብቅተው እንዲወጡ የሚያደርጉ ተግባራትን እንደሚያከናውን ቃል ገብተው የስፖርት ውድድሩ የማንቂያ ደወል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመክፈቻው ዞን 1 ከዞን 3 ጋር ባደረጉት የገመድ ጉተታ ጨዋታ የዞን-1 ታራሚዎች 2 ለ 0 አሸንፈዋል፤በተጨማሪም የዞን 4 ታራሚዎችና የፖሊስ አባላት ባደረጉት የመረብ ኳስ ጨዋታ ታራሚዎች የፖሊስ አባላትን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል፡፡
በመጨረሻም ከአዲስ አምባና ከቤንማስ ሆቴል ለህግ ታራሚዎች የተሰጠ የስፖርት ትጥቅ ርክክብ ተፈፅሟል፡፡