ስምምነት ከቡና ባንክ ጋር

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲና ቡና ባንክ በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ
***************************************
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ የብድር አገልግሎት ስምምነት በ26/02/2014 ዓ.ም. ከቡና ባንክ ጋር ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱን በተመለከተ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ እንደተናገሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሀገራችን ኢትዮጵያን ከገጠማት ችግር ለማውጣትና አጥፊውን የሕወሀት ሽብር ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ ገልጸው ከዚህ ጎን ለጎን የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተሻለ የባለቤትነት ስሜት የተቋሙን ተልዕኮዎች በማሳካት ለበለጠ ውጤት እንዲነሳሳ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ስምምነት ከቡና ባንክ ጋር ተፈርሟል ያሉ ሲሆን በዚህ ስምምነት የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ለቤት መስሪያ፣ ለመኪናና የቤት እቃዎች መግዣ የሚሆን የብድር አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሰራተኞቹን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር በዩኒቨርሲቲው ጥበበ ጊዮን ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነጻ ህክምና አገልግሎት የጀመረ መሆኑንም አውስተዋል።
የቡና ባንክ ሰሜን ምዕራብ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ልጅአለም ሙጨ በበኩላቸው ቡና ባንክ የተለያዩ አማራጮችን ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በማቅረብ ተጠቃሚ ለማድረግ በትጋት በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስራ አስኪያጁ አክለውም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከባንኩ ጋር ውል በመግባት ሰራተኞቹን ተጠቃሚ ለማድረግ እያሳየ ያለው ተነሳሽነት ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
ባንኩ በየትኛውም ሰዓት ለዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚያገለግልና በተመጣጣኝ ወለድ የብድር አገልግሎት እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን ስምምነቱ ከ10ሺህ በላይ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲውን ሰራተኞች የብድር ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡