ስለኮሮና ቫይረስ በቴሌቪዥን ስልጠና

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከአማራ ሐኪሞች ማኅበር ጋር በመተባበር ስለኮሮና ቫይረስ በቴሌቪዥን የሚተላለፍ ስልጠና ጀመረ

------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በሙሉጌታ ዘለቀ

በመላው የዓለም ብሎም በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ  /ኮቪድ-19/ በሽታ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህብረተሰቡ ከዚህ አደገኛ ዓለምአቀፋዊ ወረርሽኝ እራሱን እንዲጠብቅ  የተለያዩ  የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን እና የቁሳቁስ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ አሁንም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከአማራ ሐኪሞች ማኅበር እና በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም  ከአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋር በመተባበር ከ60 ሺ በላይ ለሚሆኑ በክልሉ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ ሕክምና አሰጣጥ እና በሽታው ከተከሰተ በኋላ የሚታዩትን  ምልክቶች እንዲሁም የበሽታውን ሥርጭት እንዴት መቆጣጠር እንደሚገባና በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ መወሰድ ስለሚገባቸው  ቅድመ ጥንቃቄዎች  እና የበሽታው ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የስጋት ወቅት ተግባቦት ላይ ያተኮሩና ለሕክምና ባለሙያዎች ግንዛቤ የሚፈጥር የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅቶ በማሰራጨት ላይ መሆኑን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሀኪምና መምህር የሆኑት ዶ/ር ወንድማገኝ እመቢአለ ተናግረዋል፡፡

የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ለጤና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ማህበረሰብ ስለ ኮሮና ቫይረስ  ኮቪድ-19 በሽታ ይበልጥ ግንዛቤን የሚጨምርና ጥንቃቄዎችን እንዲያደርጉ የሚረዳ ስለሆነ የጤና ባለሙያዎችም ሆነ ህብረተሰቡ ፕሮግራሙን በአማራ ቴሌቪዥን እና በyou tube መከታተል አንደሚችሉ ዶ/ር ወንድማገኝ ተናግረዋል፡፡