ሰብል በመሰብሰብ ደጀንነት

የዘማች ሚሊሻ ቤተሰብ ሰብል በመሰብሰብ ደጀንነታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ሰራተኞች ተናገሩ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መሬት አስተዳደር ፤ቴክስታይል እና ማዕከላዊ ግቢ የሚገኙ የአስተዳደር ሰራተኞች በጎንጅ ቆለላ ወረዳ ኮሬ ጣንክራ ቀበሌ የዘማች ሚሊሻ ቤተሰብ ሰብል በመሰብሰብ ደጀንነታቸውን ያሳዩ ሲሆን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል ፡፡    

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች የአርሶ አደሩን በተለይም የዘማች ቤተሰቦችን ከጎን ሁኖ ለመደገፍ በወቅቱ ሰብል እንዲነሳ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋፆ እያደረጉ ይገኛል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንዲታጨድ የተለየው አካባቢ በስሩም የዘማች ቤተሰቦች ያሉበት ወደ 4 ሄክታር የሚሆን ሰብል ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ባሻገር በዚህ ወቅት ከዝናቡ መምጣት ጋር ተያይዞ ሰብሉ እንዳይበላሽ በመታደግ በኩል እያደረገ ያለውን  ርብርብ የጎንጅ ቆለላ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ ዘመኑ አደራው አመስግነዋል፡፡

የኮሬ ጣንክራ ቀበሌ ም/ሊቀመንበር አርሶ አደር ዋሌ ፍላቴ በበኩላቸው  ከግል  ሥራቸው  አስቀድመው ለሀገራቸው እና ለወገናቸው ክብር ሲሉ በግንባር እየተፋለሙ የሚገኙ ዘማቾችን ሰብል  ቅድሚያ በመስጠት በአካባቢው ህብረተሰብ እንደሚሰበሰብ ጠቁመዋል፡፡  በቀጣይም  የተሰበሰበውን  ሰብል ወደ ጎተራ ከማስገባት በተጨማሪ ሌሎች የግብርና ሥራዎችን በማከናወን ዘማቾች በድል እስኪመለሱ ቤተሰቡን የመጠየቅ እና የመደገፍ ተግባራቸውን የቀበሌው ማህበረሰብ በማስተባበር  አጠናክረው  እንደሚቀጥሉ ገልፀውልናል፡፡