ምክንያታዊ ንፁህ ትውልድ- ፅዳት

'ምክንያታዊ ንፁህ ትውልድ' የተማሪዎች ማህበር አባላት የከተማ ፅዳት አደረጉ

በሙሉጌታ ዘለቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 'ምክንያታዊ ንፁህ ትውልድ'  የተማሪዎች ማሕበር ‹‹ኢትዮጵያዊያን የወደቁትን ያነሳሉ እንጅ የቆሙትን አይጥሉም!›› በሚል መሪ ቃል  በባሕር ዳር ከተማ የጥምቀት በዓልን አስመልከቶ የቆሸሹ መንገዶችን ከመስቀል አደባባይ፣  አዝዋ ፣ ፓፒረስ  እንዲሁም  የድሮው ከብት ገበያ ድረስ ያሉ ዋና መንገዶችን  ጥር 13/2013 ዓ.ም  ከጥዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ  አፅድተዋል፡፡

ተማሪ ተመስገን ሙሉቀን ምክንያታዊ ንፁህ ትውልድ የተማሪዎች ማህበር ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እንዳለው ማህበሩ የተቋቋመበት ዋና  አላማ  ቅንነትና በጎነትን የተላበሰና ከመጥፎ  አስተሳሰብና  ከሱስ ራሱን ያራቀ ንፁህ ትውልድን እንፍጠር የሚል ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ  አላማ መገለጫ ደግሞ በጎ ስራን በተግባር እየሰሩ ለከተማው ህብረተሰብ  አርዓያ በመሆን  የከተማው ነዋሪዎች ሁልጊዜ እንደዚህ ላሉ በጎ ተግባራት እራሳቸውን እንዲያተጉ ያነሳሳል  ሲል ተማሪ ተመስገን ተናግሯል፡፡ አክሎም ከሳምንት በፊት የአንደኛ ዓመት  ተማሪዎች  ሲገቡ ማህበሩ ግቢውንና  ከተማዋን አፅድተው መቀበላቸውን ጠቅሶ ዛሬ ደግሞ ከጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ መንገዶች በመቆሸሻቸው የማፅዳት ስራ መስራታቸውን ተናግሯል፡፡

በፅዳት ዘመቻው ላይ በርካታ የማህበሩ አባላት የተሳተፉ ሲሆን ዘመቻው  እንዲሳካ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እንዲሁም ተሸከርካሪዎችን በማቅረብ ለተባበረው  ለባሕር ደር ዩኒቨርሲቲ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የማህበሩ አባላት ተመራቂ በመሆናቸው ከሁለት ሳምንት በኋላ ግቢውን ለቀው እንደሚወጡ  የተናገረው ተማሪ ተመስገን  በቀጣይ ማህበሩን የሚያስቀጥሉ የአንደኛ አመት ተማሪዎችም በማህበሩ እንዲቀላቀሉ በማድረግ  ምክንያታዊ ንፁህ ትውልድ የመፍጠር አላማው ቀጣይነት እንዲኖረው  ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተገልጿል፡፡