ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎችን አስመረቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጤናው ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
**************************************************************************
[ህዳር 10/2015 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ] የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጤናው ዘርፍ በሰባት ትምህርት ክፍሎች ለ9ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 57 የስፔሻሊቲ ሐኪሞች 13 የማስትርስ ድግሪ እና 182 በመጀመሪያ ድግሪ በድምሩ 252 ተማሪዎችን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ በተገኙበት በጥበብ ህንፃ የመስብሰቢያ አዳራሽ በድምቀት አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ተመራቂ ተማሪዎች ባለፉት ዓመታት ሀገራችንና መላው ዓለም ያሳለፈውን ከባድ የፈተና ግዜ አልፋችሁ፣ የእናንተ እና የወላጆቻችሁ ከፍተኛ የትግስት ውጤት ለሆነው የምረቃ ቀናችሁ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የምርምር ዩኒቨርሲቲ የመሆን ራዕዩን በማስቀመጥ ለምርምር እና ማሕበረሰብ አገልግሎት ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ የመሆን ራዕዩ እንዲሳካ በትምህርት ጥራት ማሳደግ፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች ውስጥ በመሳተፍ የኩራት አምባሳደር እንድትሆኑ ሲሉ ለተመራቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በተማሪዎች ምረቃ ላይ የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ በንግግራቸው ለተመራቂዎች በዛሬው እለት የህክም ትምህርታችሁን የጨረሳችሁበት ሳይሆን ይልቁንም የህክምና ትምህርታችሁን መሰረታዊ ክህሎቶችን ይዛችሁ የህዝባችሁን ጤና ለመጠበቅ ታላቅ ሃላፊነትን በመቀበል የሂዎት ዘመን የህክምና ትምህርት ቤት የምትቀላቀሉበት እና ሌላውን የህይወት ምዕራፍ የምትጀምሩበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ የምትቀላቀሉት ሙያ የህይወት ዘመን ትምህርት እና ፍላጎትን የሚጠይቅ እንዲሁም የአውንታዊ ማህበረሰብ ግንኙነት የሚሻ በመሆኑ በቀጣዩ የአገልግሎት ጊዜያችሁ ከተለያዩ የሙያው አጋሮች ጋር በመሆን የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ እና ለማጎልበት ተግታችሁ እንድትሰሩ ሲሉ ለተመራቂ ተማሪዎች የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ አክለውም የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፍ በሰውሃይል ልማቱ ላይ እያበረከተ ያለውን ጉልህ አስተዋፆ እና በተለይም ለትምህርት ጥራት ለአካባቢ ልማት ምቹ አረንጓዴ ከባቢን የመፍጠር ጥረት አድንቀው በቀጣይ ዘመኑን የዋጄ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር በመጠቀም የመማር ማስተማር ስራውን በማዘመን ለትምህርት ጥራት የሰጣችሁትን ትኩረት አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂ ተማሪዎች የሜዳሊያ እና የእውቅና የምስክር ወረቀት መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡ በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የሙሉዓለም የባህል ቡድን ባህላዊ እና ዘመናዊ ሙዚቃዎችን በማቅረብ የፕሮግራሙ ታዳሚዎችን አዝናንቷል፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
-------------------------------------
``ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ``
``Wisdom at the source of Blue Nile``
Thank you for visiting, inviting and sharing our Pages!
Thank you for your likes and comments too!
ለተጨማሪ መረጃዎች፡-