ለመተከል ተፈናቃዮች ድጋፍ

ለመተከል ተፈናቃዮች የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ

በሙሉጌታዘለቀ

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ውስጥ በተፈጠረው ሰባዊ ቀውስ ለተፈናቀሉ ዜጎች የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና በባሕር ዳር ከተማ የዳግማዊ ሚኒሊክ ክፍለ ከተማ የአዲስ አምባ (የልደታ ሳይት) ነዋሪዎች በቅንጂት የምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ፡፡

 

በድጋፉም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ተቋም በተማሪዎች የተመረቱ ለህፃናትና ለአዋቂዎች የሚሆኑ አልባሳት ያበረከተ ሲሆን በተጨማሪም የድጋፍ ቁሳቁሶችን ከቦታው ድረስ ለማድረስ የመጓጓዣ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ በእለቱ በተደረገው ድጋፍም በአጠቃላይ ከ75 ኩንታል በላይ የተለያዩ የህፃናት እና የአዋቂ አልባሳት፣ከ5 ኩንታል በላይ የተለያዩ የህፃናት እና የአዋቂ ጫማዎች፣ከ40 ካርቶን በላይ ፓስታ፣ 5 ኩንታል መኮሮኒ፣ 5 ካርቶን ዘይት እና የተለያዩ ሳሙናዎችን እንዲሁም ጣፋጭ ብስኩቶችን ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የጉዳቱ ሰለባዎች ቦታው ድረስ በመሄድ ተከፋፍሏል፡፡

 

ከክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ድጋፍ የማሰባሰቡን ሂደት ያስተባበሩት አቶ ኢሳ አብዲ፣አቶ ቻላቸው ተስፋ እና አቶ አያሌው ውብነህ ሲሆኑ በርክክቡ ወቅት አቶ ኢሳ እንዳሉት  በቤኒሻንጉል ጉምዝ  ክልል የንፁኋን ወገኖቻችን ግድያና እና ማፈናቀል  እንደ ሀገር ሁላችንንም ያሽማቀቀና አንገታችን ያስደፋ እንዲሁም በታሪካችንም ላይ መጥፎ ጠባሳ ያሳረፈ የታሪካችን አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰው በተቃራኒው ደግሞ የአዲስ አምባ (የልደታ ሳይት) ነዋሪዎች ለተጎዱ ወገኖቻችን እርዳታ ለማድረግ በጠየቅናቸው በሁለት ቀን ውስጥ በከፍተኛ መነሳሳት ያሳዩት የድጋፍ ስሜት እጅግ አስደናቂና ኢትዮጵያዊነትን በግልፅ ያየንበት አጋጣሚ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

አቶ ቻላቸው ተስፋ በበኩላቸው እርዳታውን በሁለት ቀን ውስጥ ማሰባሰብ እንዲቻል የተባበሩትን የአዲስ አምባ (የልደታ ሳይት) ነዋሪዎች አመስግነው እርዳታውን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን እንዲደርስ ላደረጉት ለልደታ ቤተ ክርስቲያን የፅዋ ማህበራት እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን አመስግነዋል፡፡ አቶ ቻላቸው አክለውም ያለወላጅ ለቀሩ ሕፃናትና ጧሪ እና ቀባሪ ላጡ አረጋዊያን እንዲሁም ጉዳቱ የደረሰባቸውን ሁሉንም ወገኖቻችን ለመርዳት ሁሉም የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው በመደራጀት መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡