news

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ላሸነፈው LINK በመባል የሚጠራ ፕሮጀክት ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሄደ

Campus Name

25 Dec, 2024

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ላሸነፈው LINK በመባል የሚጠራ ፕሮጀክት ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሄደ

 

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ላሸነፈው LINK በመባል የሚጠራ ፕሮጀክት ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሄደ

****************************************

ሰኔ 11/ 2016 ዓ.ም (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ)

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ላሸነፈው በምህጻረ ቃሉ LINK (Establishing Transformative Learning, Research and Community Outreach and Capacities in Agro-ecology በመባል የሚጠራ ፕሮጀክት ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሄደ፡፡

ፕሮጀክቱ የኦስትሪያ የልማት ትብብር (Austrian Development Cooperation -ADC) ፕሮግራም ሲሆን ዓላማው የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር በተጨባጭ ለልማት እንዲውሉ ለማድረግ ተቋማቱ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ማገዝ ነው፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኦስትሪያ ከሚገኘውና University College for Agrarian and Environmental Pedagogy (HAUP) ተብሎ ከሚጠራው ተቋም ጋር በመተባበር በቅርቡ ያሸነፈው ይሄው ፕሮጀክት 270 ሺህ ዩሮ ድጋፍ የተገኘበትና ትግበራው ለ3 ዓመታት የሚቆይ መሆኑን ዶ/ር ዘውዱ እምሩ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጅክ ኮሚዩኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንትና የፕሮጀክቱ አባል ስለ ፕሮጀክቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ መምህራንና ተመራማሪዎች፤ የአስተዳደር ሰራተኞችና በፕሮጀክቱ ትግበራ ተሳትፎ የሚኖራቸው የማህበረሰብ ተወካዮችና የኦስትሪያ አጋር ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የፕሮጀክቱ ረዳት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ለፕሮጀክቱ ትግበራ ውጤታማነት ለዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የተለያዩ ተሞክሮዎችን በማንሳት አስገንዝበዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ሁሉም በየደረጃው አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅበትና ለዚህ ደግሞ በተለይ ፕሮጀክቱ በሚሰራበት አካባቢ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በባለቤትነት ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህም እንዲያግዝ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ያሉ የክዋኔ ማሳያ መረጃዎችንም ሆነ ባለድርሻ አካላቱ ስለሚኖራቸው ድርሻ ጠቋሚ መረጃዎች በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች እንዲታሙ በማድረግ ተሞክሮዎችን የማዳረስ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አሳታፊነት ም/ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር እንየው አድጎ በቅድሚያ ፕሮጀክቱን ላሸነፉ አካላት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ይህ መሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ የማህበረሰብ ችግሮችን በምርምርና የልማት ፕሮጀክቶች የመፍታት አካሄድ እንደዩኒቨርሲቲ በተለያዩ አካዳሚክ ክፍሎች ተጠናክሮ ሊሰራበት የሚገባ አካሄድ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ለዚህም የአካዳሚክ ክፍሎችን የትግበራ ቤተ-ሙከራዎች በአግባቡ መጠቀምና አጋር አካላትን በመጠቀም ለተመራማሪዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ተቋማዊ ሁለንተናዊ አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን እነዚህን አቅሞች ተጠቅሞ ለምርምር የሚውሉ መሰል የገንዘብ ድጋፎችን ማግኘት ላይ በትኩረት መስራት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር እንየው አክለውም ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ የታቀደላቸውን ዓላማ አሳክተዋል ወይ የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚያስፈልግ በመሆኑ ይሄው ለሶስት ዓመታት የሚቆየው ፕሮጀክትም መጨረሻ ላይ ዓላማውን አሳክቷል ወይ የሚለው መመዘኛ ተዘጋጅቶለት በየደረጃው መገምገም ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በኦስትሪያ በኩል የሚገኘውና በፕሮጀክቱ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሚሰራው ተቋም (University College for Agrarian and Environmental Science -HAUP) ምክትል ቻንስለር ሮይታህ ውልፍ በበይነ-መረብ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሁለቱ ተቋማት በትብብር ይህንን ችግር ፈቺ ፕሮጀክት በማሸነፋቸው የተሰማቸውን ደስታ የገለጹ ሲሆን ከሁለቱም ወገን ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መነሳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በተቋሙ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ሚስተር ፊሊፕ በበኩላቸው ፕሮጀክቱን በሚመለከት ባለው አጋርነትና ስምምነት ዙሪያ አጠር ያለ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር ለፕሮጀክቱ መሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዘሪሁን ዮሐንስ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ባደረጉት ገለጻ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኦስትሪያ ከ University College for Agrarian and Environmental Science HAUP ጋር በመተባበር ባሸነፈው በዚህ ፕሮጀክት ትኩረት ተደርጎ የሚሰራባቸው ጉዳዮች የለውጥ ትምህርት (Transformative Learning-Green Pedagogy)/ አሳታፊ ተግባራዊ ምርምር፣ የስርዓተ ትምህርት ግምገማና አሳታፊ የሞጁል ቀረጻ፣ የማህበረሰባዊ ተሳትፎ ተግባራት፤ የአርሶ አደር ቤተሰብ መማሪያ ቡድኖች እንዲሁም የአግሮኢኮሎጂ ንድፈ ሀሳባዊ እና ተግባራዊ ሰርቶ ማሳያ ጣቢያዎች ግንባታ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ዘሪሁን አክለውም የፕሮጀክቱን ዓላማዎች፣ የሚከናወኑ ተግባራትንና የአሰራር ዘይቤዎችን፣ የታቀዱ ስራዎች የሚተገበሩባቸው ጣቢያዎችን የመምረጥ እንዲሁም የፕሮጀክቱን ዘላቂነት፣ የህብረተሰቡን ተሳትፎ፣ የስርአተ ጾታ እና የልዩ ፍላጎት አካታችነት የተመለከቱ ጉዳዮች በፕሮጀክቱ ቀረጻ ላይ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ጌታቸው አለማየሁ በበኩላቸው ፕሮጀክቱን ቀርጸው ለዚህ ላበቁ አካላት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን መሰል ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን ማምጣት እንዲቻልና በርከት ያሉ ምሁራን በእንደዚህ አይነት ውጤታማ ስራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማገዝ የምሁራንን የጥናትና ምርምር አጻጻፍ ብቃት የሚያሳድጉ አቅም ግንባታ ስራዎችና አውደ ጥናቶችን ማዘጋጀት እጅግ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት ባለ ድርሻ አካላትም ሰፊ ውይይት አካሂደው መርሀ ግብሩ ተጠናቋል፡፡