የተማሪዎች አቀባበል

በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ከባሕር ዳር ከተማ ወጣት ማህበራት ጋር ምክክር ተደረገ !!

በሙሉጌታ ዘለቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ተማሪዎች አቀባበል በማድረግ ዙሪያ ከዘጠኝ በላይ ከሚሆኑ የባሕር ዳር ከተማ ወጣት ማህበራት ጋር በዩኒቨርሲቲው የጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ምክክር አደረጉ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮምንኬሽ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንዲሁም የባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ የባህር ዳር ወጣቶች በዩኒቨርሲቲው ፀጥታ ጉዳይና የተማሪዎችን ደንነት ከመጠበቅ አንፃር እያበረከቱት ያለውን አስተዋፆ አድንቀዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ አክለውም ዩኒቨርሲቲውም የስራ እድሎችን በመፍጠርና የወጣቶችን አቅም በመገንባት የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግ ጠቁመው ወጣቶችም የባሕር ዳር ከተማና  የዩኒቨርሲቲው ስም በበጎ እዲነሳ አሁንም ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት የነበረውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል፡፡

ከባሕር ዳር ከተማ የተወጣጡ የወጣት ማህበራት  ተወካዮች እንደገለጹት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሞባይልና የላፕቶፕ ዘረፋዎች የሚደርስባቸው ተብለው የተለዩ ዋና ዋና የሚባሉ መስመሮች የመንገድ መብራቶቻቸው የጠፉ እና አንዳንዶችም መስመር ሊዘረጋላቸው የሚገባ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ከመብራት ሀይል እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡  አክለውም ወጣቶቹ በባሕር ዳር ከተማም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ለተነሱት ጥያቄዎች በባሕር ዳር   ዩኒቨርሲቲ  ከፍተኛ አመራሮች መላሽ ተሰጥቷል፡፡