የኢድ አልፈጥር በዓል ተከበረ

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከከተማው የሙስሊም ማህበረሰብ ጋር የኢድ አልፈጥር በዓልን አከበሩ፡፡
============================================
ባሕር ዳር እንደቤቴ በተሰኘው ፕሮጀክት ስም የእስልምና እምነት ተከታይ ተማሪዎች የኢድ አልፈጥር በዓልን ከባህር ዳር ከተማ ሙስሊም ማህበረሰብ ጋር አክብረዋል፡፡
 
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደተቋሙ በሚመጡ ተማሪዎችና በባሕር ዳር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች መካከል ቤተሰባዊ ግንኙነት እንዲኖር ’’ባሕር ዳር እንደቤቴ‘’ የተሰኘ ፕሮጀክት በተግባር ላይ መዋሉ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚሁ ፕሮጀክትም ከዚህ ቀደም የክርስትና እምነት ተከታይ ተማሪዎች የገና እና ፋሲካ በዓላትን ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ማሳለፋቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከከተማው የሙስሊም ማህበረሰብ ጋር የኢድ አልፈጥር በዓልን አክብረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው የአካባቢውን ታሪክ ፣ባህል እና ቋንቋ ማወቅ እንዲችሉ የሚያግዝ እና ባህር ዳርን እንደ ቤታቸው ቆጥረው በትምህርት ገበታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም በአገራችን ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚረዳ እንደሆነ ይታመናል፡፡
 
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከከተማው ማህበረሰብ ጋር የኢድ አልፈጥር በዓልን በማክበራቸው ትርጉም ያለው ውህደት ከማድረጋቸው ባሻገር ከባህር ዳር ከተማ ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲመሰርቱ ብሎም ባህር ዳርን እንደቤታቸው እንዲቆጥሩ በማድረግ የዩኒቨርሲቲውንም ሆነ የማህበረሰቡን ገጽታ በመገንባት ስብዕናና ትሩፋት ይጋራሉ ፡፡ ይህም ዋና የሆነውን የተማሪዎችን የእውቀት ግብይት ተግባር እና ውጤታማነትን በጉልህ እንደሚያሳድገው ይታመናል፡፡
 
በእለቱ የተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የኢድ አልፈጥር በዓልን ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር ያሳለፉትን የባሕር ዳር ከተማ የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችና የወጣቶች ማህበራት አባላትን ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳሉ እንዲሰማቸው በማድረግ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፆ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ክፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡