የአይሲቲ አውደ ጥናት

አይሲቲ ለልማት የምርምር ማዕከል 2ኛውን አለም አቀፍ አውደ ጥናት አካሄደ።

በትዕግስት ዳዊት

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አይሲቲ ለልማት የምርምር ማእከል ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር አይሲቲ ለአፍሪካ ልማት በሚል መሪ ቃል ለ3 ቀናት የሚቆይ አለም አቀፍ አውደ ጥናት  በባህር ዳር አካሂዷል።

የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋ ተገኘ እንዳሉት የአውደ ጥናቱን ተነሳሽነት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ወስዶ እንዳሰባሰበው ገልፀዋል፡፡ የጉባኤው አላማም በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በቋንቋ ጥናት፣ በጤና፣ ትምህርትና የግብርና ስራን በቴክኖሎጂ መደገፍ ላይ፣ ገመድ አልባ የሞባይል አገልግሎት እንዲሁም የውሀ ጥራት ላይ ስፖንሰሮችን በመጠቀም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማውጣት ነው ብለዋል።

በአይሲቲ የማህበረሰቡን ችግር እንዴት እንፈታለን የሚል አላማ ላይ ትኩረት ያደረገው አውደ ጥናቱ ከተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ የአይሲቲ ምሁራን የተሳተፉበት ሲሆን 31 የሚሆኑ የምርምር ወረቀቶች ቀርበዋል፡፡ ይህም ካለፈው አመት ሲታይ ቀጥሩ የላቀ ሲሆን ይህም አበረታች ነው ተብሏል፡፡

ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጡት የመርሀ ግብሩ ተሳታፊ አቶ ቢንያም  ጉባኤዎች በየክልሉ የሚሰሩ የምርምር ስራዎችን ለመጋራትና አንዱ ያለውን ጥሩ ተሞክሮ ለሌሎች ለማካፈል ይረዳሉ ብለዋል፡፡ በእለቱ እንደተናገሩትም አይሲቲን በመጠቀም የጤናና የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል፡፡ አቶ ቢንያም  በዕለቱ በጤናው ዘርፍ ላይ ያላቸውን እውቀትና ተሞክሮ ለተሳታፊዎች አካፍለዋል።

ኢትዮጵያ ወስጥ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እንዴት ይሰራሉ የሚል ርእሰ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይም በምርምር ዘርፍ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ለመስራት ዋጋቸው ውድ ያልሆኑና ማህበረሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመለየት መስራት እንደሚገባ የተጠቆመ ሲሆን ተመራማሪዎችም ያላቸውን ልምድና እውቀት አካፍለዋል። ተጋባዥ ምሁራኑም ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጥምረት ለመስራት ተወያይተዋል፡፡