ፋኩልቲው 6ኛ አመታዊ ትምህርታዊ ጉባኤውን አካሄደ

የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ 6ኛውን አገር አቀፍ ጉባኤ አካሄደ

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ 6ኛ አመታዊ ትምህርታዊ ጉባኤውን  በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለሁለት ተከታታይ ቀናት አካሄደ::

የፋኩልቲው ዲን ዶ/ር ቃለወንጌል ምናለ ጥሪውን አክብረው ለመጡት ታዳሚዎች በሙሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን  አስተላልፈው ፋኩልቲው በ8 የቅድመ ምረቃ፣ በ11 የድህረ ምረቃ እና በ3 የሶስተኛ ዲግሪ (PhD) ፕሮግራም ከ5000 (አምስት ሺህ) ተማሪዎች በላይ ተቀብሎ  በተለያዩ ሙያዎች እያሰለጠነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዲኑ አክለውም ፋኩልቲው ከሌሎች ኮሌጆችና ፋኩልቲዎች ቀድሞ የተቋቋመ ቢሆንም እስካሁን የሚጠበቅበትን ያህል መስራት እንዳልቻለ ጠቁመው የሰውን ልጅ በአግባቡ ለማነፅ ብሎም የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የማህበራዊ ሳይንስ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፤ በመሆኑም ፋኩልቲው በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ በጉባኤው ከተለያዩ ተቋማትና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተውጣጡ ምሁራን የሚቀርቡት ጥናታዊ ፅሁፎችና ውይይት የማንቂያ ደወል ሆኖ እንደሚያገለግል እምነታቸው መሆኑን ተናግረው በአሁኑ ስአት ፋኩልቲው የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችል በዕቅድና በተደራጀ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

መርሃ-ግብሩ በይፋ መከፈቱን ያበሰሩት የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ዩኒቨርሲቲው በስምንት ግቢዎች በሶስቱም የስራ አምዶች ማለትም በመማር ማስተማሩ፣በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በመግለፅ ዩኒቨርሲቲውን በሰፊው እያስተዋወቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ እንደማሳያም  ባህር ዳር ከተማን የትምህርት ከተማ ለማድረግ  በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት በኩል ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸው ተግባራት አመላካች እንደሆኑ ተናግረው የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲም ታሪክ ሳይዛባ ለትውልድ እንዲተላለፍ፣ፖለቲካም በሳይንሳዊ ዘዴ ለማህበረሰቡ ማስተላለፍ ያለበትን መልዕክት እንዲያስተላልፍ እንዲሁም በጂኦግራፊውም ዘርፍ ብቁ ባለሙያ በማፍራት ረገድ ከፍተኛ የሆነ አገራዊ ድርሻ እንዳለበት ተገንዝቦ በየአመቱ ጉባኤውን ማክበር ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ በመለየት ክፍተቶችን የሚሞላ ስራ ማከናወን እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

የጉባኤውን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጋብዘው የመጡት ፕሮፌሰር ወልደአምላክ በውቀቱና የዩኒቨርሲቲያችን አንጋፋ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ ሲሆኑ ፕሮፌሰር ወልደአምላክ እንዳሉት የምርምር ስራዎች ተግባራዊነት አንዱ መለኪያ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆን ጥናት ማድረግ እንደሆነ ገልፀው ይህን እውን እስከምናደርግ ለውጥ የሚያመጣ ስራ እንዳልሰራን በማሰብ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል ሲሉ ክፍተቱን ጠቁመዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በተለያዩ ሙህራን በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡