ዩኒቨርሲቲው በግልገል አባይ ወንዝ መዳረሻ አካባቢ የሚሰራውን ፕሮጀክት ጎበኘ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በግልገል አባይ ወንዝ መግቢያ ያሉ ውሃ አዘል መሬቶች ማገገምና ዘላቂ ልማት ኘሮጀክት (Rehabilitation and Sustainable Utilization of little Abay River Mouth Wetlands Project) በወንዙ ተፋሰስ ዙሪያ ያከናወናቸውን ስራዎች አስመልክቶ የአንድ ቀን ጉብኝት አካሄዷል፡፡
ኘሮጀክቱ ከተጀመረ  ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን የአካባቢውን ውሃ አዘል መሬት መሪ እቅድ ማውጣት፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ፤ በተለይ ለተማዎች እና ለተመራማሪዎች እንዲሁም ለአርሶ አደሮች፣ የደንገልን ተከላና እንክብዛቤ ማስፈን፣ የብዝሀ ህይወት ሀብት የሆነውን ጣና ሀይቅን መጠበቅ ዋና ዋና ዓላማዎች እንደሆኑ የኘሮጀክቱን በዋናነት የያዙት ሶስት የዩኒቨርሲቲው ሙህራን/ ዶ/ር ምንውየለት መንግስት፣ ዶ/ር ዋሴ አንተነህ እና ዶ/ር አማረ ሰውነት/ ገልፀዋል፡፡ ከእነዚህ አላማዎች መካከል ከ85-90 % የሚደርሱት የተከናወኑ እንደሆኑና ከዛም በዘለለ የአካባቢውን ስራ አጥ ወጣት በማደራጀት በአሳ ማስገር ሥራ ተሰማርተው እራሳቸውን እንዲችሉ ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በአባይ ተፋሰስ አካባቢ ከ4500 ሕዝብ በላይ የሚኖርባቸው ሁለቱ ቀበሌዎችን ማለትም ከሰሜን አቸፈር ወረዳ እስቱሚት ቀበሌ እና ከባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ልጆሚ ቀበሌ በተሻለ ዘዴ ኑሮአቸውን እንዲመሩ ለማስቻል ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የፕሮጀክቱ ባለቤቶች ገልፀዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ኘሬዚዳንት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ የተገኙ ሲሆን ከጉብኘቱ በርካታ ያልጠበቋቸው ነገሮች ተሰርተው እንዳገኙ እንዲሁም ለወደፊቱ በደለል በመሞላት ምክንያት ተጎጅ የሆነ ያለውን የጣና ሀይቅ ለመታደግ ሁሉም እርብርብ ማድረግ እንዳለበት ገልፀው በኘሮጀክቱ አማካኝነት የተገኙትን ሁለት የሞተር ጀልባዎች ለስቱሚቱ እና ለልጆሚ ቀበሌ አስተዳደሮች አስረክበዋል፡፡ “የ CEPF(Eastern Afromontane Regional implementation Team” ) አማካሪ  የሆኑትን አቶ አብዱራሀማን ኩብሳን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች ፣ ሙህራንና የአካባቢው ማህበረሰብ በጉብኝቱ ተሳትፈዋል፡፡