የዓለም ዓሳ ስደት ቀን

 የዓለም ዓሳ ስደት ቀን ተከበረ

በወንዳለ ድረስ

ጥቅምት 14/2013 ዓ.ም

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከWorldFish እና IFAD ጋር በመተባበር ባሕር ዳር ዙሪያ ቆራጣ ቀበሌ ገልዳ ወንዝ በመገኘት ‹‹ግድቦች በዓሳዎች እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ እንከባከብ!’’ በሚል መሪ ቃል የዓለም ዓሳ ስደት ቀን (World Fish Migration Day) አክብረዋል ፡፡ 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዓሳ ሃብትና ውሃ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ  ዶ/ር ምንውየለት መንግስት እንደተናገሩት የበዓሉ ዓላማ ህብረተሰቡ ስለዓሳ ሀብት ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ እና ዓሳዎች በዎንዞች እንቅስቃሴ የሚደርስባቸውን ጫና መቀነስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዓሳ አስጋሪ የድግን መረብ ወንፊት ስፋት ከ8 ሴንቲሜትር በላይ እንዲሆን ማድረግ፣ ከሰኔ እስከ ጥቅምት በትልልቅ ወንዞችና ገባሮች ከሀይቁ ጋር በሚገናኙበት ቦታ የማስገር ስራ ማቆም፣ የወንዝ ጠለፋና ግድቦችን ተፅዕኖ ለመቀነስ የዓሳ መሰላልና ማሳለፊያ መስራት፣ የዓሳ ማስገር ስራን ስርዓት ማስያዝና ህጋዊ ፈቃድ በመስጠት እንዲከናወን ማድረግ፣ የክልሉን የዓሳ ሀብት አጠቃቀም አዋጅ በትክክል መተግበር የሚሉትን የመፍትሄ ሀሳቦች በውይይቱ ወቅት ዶ/ር ምንውየለት አንስተዋል፡፡

 በዓሉን በተመለከተ ንግግር ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አበበ ጌታሁን በዓሉ መከበር የጀመረው ከ2006 ጀምሮ መሆኑን ጠቁመው ሌሎች ሀገራት የሚያከብሩት ዓሳዎች ስለሚሰደዱ ብቻ ሲሆን እኛ ግን ዝርያቸው በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ አሳዎች ባለቤት መሆናችንም ጭምር በአሉን ማክበራችን የግድ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዋሴ አንተነህ  ክልሉ ከሀገሪቱ 50% የሚሆነውን የውሃ ሃብት የሚይዝ በመሆኑ ከፖለቲካ አመራሩ እስከ ፖሊሲ አውጪው ትኩረት ቢያደረግ በተለይም እንደ ገልዳ ወንዝ ግድብ ያሉ ለዓመታት ያለጥቅም የተቀመጡ ግድቦች ላይ ማስተካከያ በተጨማሪም መንግስት ያለው የተቋም አደረጃጀት ላይ ትኩረት መሰጠት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ 

በውይይቱ ከእንስሳት ኤጀንሲ፣ ከኢኮ ቱሪዝም፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተመራማሪዎች እንዲሁም ዓሳ አስጋሪዎች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አጋር አካላት ተሳትፈውበታል፡፡