የማስክ/ጭንብል አዘገጃጀት ስልጠና

 

የማስክ/ጭንብል/ የቤት ውስጥ አዘገጃጀት እና አጠቃቀም የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሠጠ ነው

ትዕግስት ዳዊት

 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ መምህራን እና FGCF ከተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት በመጡ አሰልጣኞች የተዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና ባሕር ዳር ዙሪያ ከሚገኙ 63 ት/ቤቶች ለተወጣጡ ፍላጎቱ ያላቸው 126 መምህራን እየተሰጠ ሲሆን ከጥቅምት 25 ጀምሮ እስከ 28 እንደሚቀጥል ተነግሯል፡፡

ከዚህ ስልጠና በኋላ ኋሰልጣኞች በሚያስተምሩባቸው ት/ቤቶች ለሚገኙ ስልጠናውን ላልወሰዱ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ለተማሪ ወላጆች እንደሚሰጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

FGCF ከተባለው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ስልጠናውን ለመስጠት የመጡት ሲ/ር ማርናት አዱኛ እንዳሉት በኮሮና ምክንያት ተዘግተው የነበሩት ትምህርት ቤቶች በቅርቡ የሚከፈቱ በመሆናቸው የኮሮናን አደጋ ለመቀነስ እንዲቻል መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ሲ/ር ማርናት  አክለውም ተማሪዎችና መምህራን ወጭ ሳያወጡ ቤት ውስጥ በሚገኙ ባገለገሉ ልብሶች ጭንብል ማዘጋጀት እንዲችሉ የሚያስችል ውጤታማ ስልጠና እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ከማስክ/ጭንብል/ አሰራር በተጨማሪ ሲ/ር ማርናት ስለኮሮና ቫይረስ (COVID _19) መተላለፊያ እና መከላከያ መንገዶች ለሰልጣኞች አስረድተዋል፡፡

ሜጫ ወረዳ በወተት አባይ ት/ቤት መምህር የሆኑት መምህር ሽባባው አስማረ የስልጠናውን ጠቃሚነት አብራርተው ወጭ ቆጣቢና ማንም ሰው አገልግሎት ከሰጡ ጨርቆች ማዘጋጀት የሚችለው መሆኑን እና ያገኙትን እውቀትም ለሌሎች እንደሚያጋሩት አያይዘው ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ ከፍርን የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ት/ቤት የመጡት መምህርት ማለፊያ ልየው ከስልጠናው ስለኮሮና ቫይረስ (COVID _19) ምንነት፣ መተላለፊያ መንገዶች፣ በቁሶች ላይ ለምን ያክል ጊዜ እንደሚቆይ እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል/ማስክ/ በቤት ውስጥ እንዴት እንደሚዘጋጅና አጠቃቀሙን በተመለከተ ሰፊ እውቀት ማግኘታቸውን አጋርተውናል፡፡