5ኛው ሀገር አቀፍ የአማርኛ ቋንቋ እና የባሕል ዘርፎች ዓውደ ጥናት ተካሄደ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም (አቋማተ) 5ኛውን ሀገር አቀፍ የአማርኛ ቋንቋ እና የባሕል ዘርፎች ዓውደ ጥናት አካሄደ፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መለሰ ገላነህ ተቋሙ የአማርኛ ቋንቋን በማልማት ላይ እንደሚገኝና የቋንቋ ልማት በአለማችን ላይ ከሚገኙ ጥንታዊ ቋንዎች በታሪክ ተጠቃሽ ማለትም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከበለፀጉ ሀገራት ጋር በቀጥታ የተቆራኘ እንደሆነ እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደሆነ ጠቁመው የቋንቋውን የመግለጽ ደረጃ በማሳደግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የምርምርና ጥናት ቋንቋ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህ ዓውደ ጥናት በየዓመቱ የሚያካሄዱት ለተማሪዎችና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም ለተመራማሪዎች ደግሞ በዚህ ላይ ለመስራት ምን እንደሆነና• ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ግንዛቤ ስለሚሰጥ በምን ላይ መመራመር እንዳለባቸው ትልቅ ግብዓት እንደሚሰጥም ገልፀዋል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግንባር ቀደምነትን በመውሰድ የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም ለመመስረት በርካታ አሳማኝ ምክንያቶች እንዳሉት ከነዚህም ውስጥ መጀመሪያውና ዋናው ምክንያት አማርኛ ቋንቋ ማበልፀግና ማሳደግ ለሀገር ልማት ያለው ፋይዳ በመረዳት እንደሆነና አንድ ሀገር የሚያደርገውና የሚበለጽገው በራሱ ቋንቋ ሲመራ፣ ሲጽፍ፣ ሲጠቀም፣ ቋንቋው የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ ለታሪኩ መገለጫ መሳሪያ መጠቀሚያ ሲሆን እንደሆነና ቋንቋው የመግባቢያ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን የማንነት መገለጫም ጭምር እንደሆነ የተናገሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ ናቸው፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቆም ብሎ በማሰብ የሀገር የጥበብ መነሻ መርምሮ፣ ወደፊትም ረጅም ርቀት ተመልክቶና አልሞ አሁን የሚደረገው የአገራችን ህዳሴ በማህበረሰቡ ባህል፣ ፍልስፍና፣ ጥበብ ላይ ተመስርቶ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቀጣይነት ያለው ልማት፣ እድገት፣ ጥበብ እንዲኖር ለማድረግ በግዕዝ ቋንቋ የተፃፉ ፅሁፎችን ወደ አማርኛ በመተርጐም እና የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋምን በማቋቋም ቋንቋውን በማበልፀግ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በመማሪያና የምርምር ቋንቋ በማድረግ ሌሎች አገሮች ከደረሱበት የእድገት ጐዳና እንድንደርስ የወሰደው አገራዊ ሀላፊነት ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ካሰመረባቸው ውጤታማ ተግባራቱ በተጨማሪ ታሪክ በመስራት ላይ እንደሆነ አመላካች ተግባር እንደሆነ እና በዓለም ላይ የበለፀጉም ሆኑ በእድገት ዝቅተኛ የሆኑ አገሮች እድገታቸውም ሆነ ውድቀታቸው የአስተሳሰባቸው ውጤት እንደሆነ እና ለእድገታችንም ሆነ ለውድቀታችን የመጀመሪያው መሳሪያ አስተሳሰባችን መሆኑን የተናገሩት የእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የአማራ ክሄራዊ ክልላዊ መንግስት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሂሩት ካሳው ናቸው፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ታላቅ ነበረች የምትባልባቸው አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ፋሲልን፣ ፊደላችንና ስርዓተ ጽህፈታችን፣ ታላላቅ መጽሐፍቶቻችንና የመሳሰሉት ጥበቦች የአስተሳሰባችን ውጤቶች መሆናቸው እንደሆነ እና ወደራሳችን ተመልሰን ስለራሳችን ለማሰብና አስፈላጊ ሲሆን የሌሎችንም ለመውሰድ ከራሳችን መነሳት እንደሚኖርና ይህን ለማድረግ መረዳት፣ መገንዘብ፣ ከዛም በተረዳነው መጠን ማሰብና ማፍለቅ የምንችለው የራሳችንን እውነት በምንገልጽበት፣ በምንቀበልበት ቋንቋ ስንጠቀም ቀድሞ አገራዊ ኃላፊነትን በመውሰድ በአማርኛ ላይ የሚመክር አመታዊ ጉባኤ በማዘጋጀትና ተቋም በመመስረት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ በመሆኑ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲው ብሎም ከአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም ጋር በጋራ ለመስራት በተደረገው ስምምነት መሰረት የአማርኛን የፊደል አመታዊ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት፣ የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ የአማርኛ ቋንቋና ባሕል ቴክኖሎጂ ማዕከል በየትምህርት ቤቱ በማቋቋም፣ እንዲሁም አማርኛን የመማሪያና የማስተማሪያ ቋንቋ ለማድረግ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም እየተሰራ ያለውን ሥራ በማጠናከር የአብክመ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከሚመለከተው ከትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን መስራትና ማሟላት የሚገባውን ሁሉ በመስራት በአማራ ክልል እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርቱ እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ የቢሮ ኃላፊዋ ገለፀዋል፡፡ በዓውደ ጥናቱ ላይ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጐባቸዋል፡፡