ለተመራቂ ተማሪዎች ሥራ ለማፈላለግ የሚረዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

ኢትዮ ጆፕስ (Ethiojobs) አዲስ በፈጠረው ደረጃ ዶት ኮም (Dereja.com) በተሰኘው ድረ-ገፅ አማካኝነት ሁሉም ተመራቂ ተማሪ በቀላሉ ሥራ ማፈላለግ የሚያስችለውን ግንዛቤ ለመፍጠር ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ስልጠና ሰጠ፡፡

የዌብሳይቱ ፕሮጀክት ማናጀር ወ/ሪት ሲሀም አየለ የስልጠናው ዋና ዓላማ ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ የማፈላለጉ ልምድ ስለሌላቸው ያለውን ብዥታ ለማስወገድና ቀጣሪ ካምፓኒዎችን ከተቀጣሪዎች ጋር በዌብ ሳይቱ አማካኝነት ተገናኝተው በሚፈልጉት ሙያ እንዲሰሩና በራስ የመተማመን ወኔ እንዴኖራቸው እንዲሁም በግልፅ ያለባቸውን ደካማና ጠንካራና ጐን ለሌላው አሳውቀው መቀጠር እንዲችሉ ታልሞ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማናጀሯ አያይዘውም ዌብሳይቱ ከተመሰረተ ሁለት ዓመት ቢያልፈውም ሰፊ መስራት የተቻለው በያዝነው ዓመት ስለሆነ ከ6ቱ ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲት፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲና አዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

የዌብ ሳይቱ መቀመጫው አዲስ አበባ ይሁን እንጂ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተደራሽነቱን ለማስፋት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚካሄድ ደማቅ የሥራ አውደ ርዕይ በመጭው ሰኔ ወር ስለሚካሄድ ስልጠናው ለሁሉም ተመራቂ ተማሪ የሚፈልገውን መረጃ በቀላሉ የሚያገኝበት የማንቂያ ደወል መሆኑን ማናጀሯን ጨምሮ ሁሉም አሰልጣኞች ገልፀዋል፡፡

በስልጠናው የተሳተፉ ተማሪዎች ዌብ ሳይቱ ሁሉንም ተማሪ የሚያሳትፍና በቀላል ቋንቋ በፍጥነት መረዳት በሚቻልበት መንገድ እንደተዘጋጀ ግንዛቤ ማግኘታቸውንና ለወደፊት በተግባር ላይ ሲውል አመርቂ ውጤት እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡