የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማዕከል ተከፈተ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማዕከል በይፋ ተከፈተ፡፡

(በሙሉጉጃም አንዱዓለም)

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሳንባ ቆልፍ (ኮሮና ቫይረስ) ለመመርመር የሚያስችል ማዕከል ተከፈተ፡፡

በመክፈቻ መርሐ-ግብሩም ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የሺጌታ ገላው ጥሪውን አክብረው ለመጡ እንግዶች ምስጋናና የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው የመመርመሪያ ማዕከሉ በአማራ ክልል 6ኛው በባህር ዳር ከተማ ደግሞ 2ኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ አክለውም በክልሉ ያሉት አምስት መመርመሪያዎች ከህዝቡ ቁጥር አንፃር ሲታዩ አነስተኛ እንደሆኑና የማዕከሉ መከፈት ፋይዳው የጎላ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ማሽኑ አውቶማቲክ ሳይሆን በማኑዋል የሚሰራና በአንድ ግዜ 96 ናሙናዎችን የሚቀበል እንደሆነ እንዲሁም ከሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ጀምሮ ለ24 ናሙናዎች (ሁሉም ውጤታቸው ከቫይረሱ ነጻ የሆነ) ምርመራ እንዳካሄደ አስገንዝበው ወደፊት ማሽኑን ወደ አውቶማቲክ ከፍ ለማድረግ የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ዩኒቨርሲቲው ወረርሽኙን ለመከላከል በርካታ አኩሪ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ገልፀው የዚህ ማዕከል መከፈትም አንዱ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዘዳንቱ አክለውም ኮሌጁ ወረርሽኙን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሰራ ላለው ስራና ለጤና ባለሙያዎች ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ፕሬዘዳንቱ በማስከተል በቴክኖሎጂ ዘርፉም ዩኒቨርሲቲው ያፈራቸው ምሁራን በርካታ ቁጥር ያላቸው የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን አምርተው በማቅረብ ግንባር ቀደም መሆናቸው ዩኒቨርሲቲውን እንደሚያኮራ ጠቅሰዋል፡፡

የመርሃ-ግብሩ የክብር እንግዳና የአ/ብ/ክ/መ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የክልሉ ኮሮናን የመከላከልና መቆጣጠር ግብረ-ኃይል ሰብሳቢ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በርካታ ስራዎችን እንዳከናወኑ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉነሽ እንደገለጹት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ እየሰራቸው ካሉ ተግባራት ጎን ለጎን በእንቦጭም ሆነ በሌሎች ተግዳሮቶች ዙሪያ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ስለሆነ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው የማዕከሉ መከፈት እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነና ለወደፊትም ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሌች ተቋማት ጋር ተቀናጅተው በመስራት ወረርሽኑን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው ማዕከሉ በይፋ ተከፍቶ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን አብስረዋል፡፡

የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ ሙላቱ መለሰ በበኩላቸው ወረርሽኙ ሀገራችንን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የፈተነ በመሆኑና በዚህ ወቅት ደግሞ በቅንጅት በመስራት ወረርሽኙን ከመዋጋት አንፃር ዩኒቨርሲቲዎች የአንበሳውን ድርሻ ወስደው በመረባረብ በርካታ የሚያስመሰግን ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በርካታ ምሁራንን የያዘ በመሆኑ መጠነ-ሰፊ ስራዎችን በማከናወን ግንባር ቀደም ተደራሽ ስለሆነና ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ማዕከሉ እንዲከፈት ስላደረገ በጤና ቢሮው ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አቶ ሙላቱ በማስከተል ለወደፊቱ ማሽኑን ወደ አውቶማቶክ የመቀየርና ተቀናጅቶ የመስራት አቅምን ከፍ የማድረጉ ጉዳይ ሊሰመርበት የሚገባ ስለሆነ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ርብርቡን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡ በመረሐ-ግብሩ ላይ የመመርመሪያ ላቦራቶሪው ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን ናሙና የሚወስዱ 20 የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዳሉና እነሱ ጎን ለጎን ሌሎችንም እያሰለጠኑ እንደሚገኙ መረዳት ተችሏል፡፡