ፅዳት በመስቀል አደባባይ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ጋር በጋራ በመሆን አኩሪ ተግባር ፈፀሙ፡፡
*****************************************************************************
በሸጋዉ መስፍን
“ምክንያታዊና ንፁህ ትዉልድ (ም.ን.ት)” የተሰኘዉና በምስረታ ላይ ያለዉ የበጎ ተግባር አራማጅ ተማሪዎች ማህበር በከተማዋ ከሚገኘዉ “ድንበር የለሽ የበጎ አድራጎት ማህበር” ጋር በመተባበር ጥር 13/2012 ዓ.ም ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ በጥምቀት በዓል ምክንያት መንገድ ላይ የወዳደቁ ቆሻሻዎችን ጨምሮ የባህር ዳር ከተማ መስቀል አደባባይን አፅድተዋል፡፡

የፅዳት ፕሮግራሙን ሲያስተባብር ያገኘነዉ ተማሪ ቀለሙ እሱባለዉ እንደገለፀዉ አሁን አሁን በእምነት ምክንያት ቁርሾ ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት እንዳሉ ጠቅሶ ማህበራቸዉ እነዚህን አካላት በተግባር ይታገላል ብሏል፡፡
በፅዳት ዘመቻዉ ስትሳተፍ ያገኘናት ተማሪ በእምነት አማን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ መሆኗን ገልፃ ማህበሩ የተለያዩ ብሄርና ሀይማኖቶች ስብጥር ያለበት በመሆኑ አገራዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል ትልቅ ፋይዳ አለዉ ስትል እምነቷን አንፀባርቃለች፡፡ተማሪ በእምነት አክላም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በአእምሮው የጎለመሰ ነዉ በማለት ኢትዮጱያዊነት የሚመሰረተዉ ከዚሁ ነዉ ስትል ጨምራ ገልፃለች፡፡

የ3ኛ አመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ የሆነዉ የሱፍ አህመድ በበኩሉ ይህ የፅዳት ዘመቻ የአንድነት እሴታችንን ለማዳበር ትልቅ ፋይዳ አለዉ፤ ከክርስቲያን ወንድሞቼ ጋርም በፅዳቱ በመሳተፌ በጣም ደስተኛ ነኝ ብሏል፡፡ተማሪ የሱፍ አክሎም ዘር፣ ቋንቋ፣ ብሄር ሳይል አንድነታችን የተመሰረተዉ ከፖለቲካዉ በፊት ነዉ፤ ስለሆነም ሊለያዩን ቢሞክሩም አይሳካላቸዉም ሲል ተናግሯል፡፡

ከባህር ዳር ከተማ “ድንበር የለሽ የበጎ አድራጎት ማህበር” ያነጋገርነዉ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ደራሲና ተዋናይ ከፊያለዉ እሸቴ ማህበራቸዉ በጎ እናስብ (think positive) በሚል መሪ ቃል የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሶ ማህበራቸዉ ሰባት አላማዎችን ለመፈፀም እንደሚሰራ ተናግሯል፡፡በዚህም የፅዳት ዘመቻን ጨምሮ ሱስን መከላከል፣ መተሳሰብን ማጎልበት፣ ንቁ ዜጎችን ማፍራት ከማህበሩ አላማዎች ዋነኞቹ ናቸዉ ብሏል፡፡ ማህበራቸዉም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልፆልናል፡፡
ሌላዋ በፅዳት ዘመቻዉ ስትሳተፍ ያገኘናት የ1ኛ አመት የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ እና የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነችዉ ተማሪ ከሚላ በላቸዉ በዚህ ተግባር በመሳተፏ በጣም እንደተደሰተች ገልፃ ቆሻሻዉ በአጋጣሚ በጥምቀት በአል የተፈጠረ ቢሆንም የከተማዋ ፅዱ መሆን ለሁሉም ነዋሪ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ሰዉ በዚህ ተግባር መሳተፍ አለበት ብላለች፡፡ከሚላ በተጨማሪም ‘ሀምሳ ሎሚ ለሀምሳ ሰዉ ጌጡ ለአንድ ሰዉ ሸክሙ’ እንዲሉ በከተማ የመንገድ ፅዳት ስራ ለተሰማሩ እናቶች ከፍተኛ ድካምን ይቀንሳል ብላለች፡፡

በቦታዉ ተገኝተዉ ለወጣቶች ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዘዉዱ እምሩ በሌሊት ብርድ ሳይበግራቸዉ የዘንባባ ቅጠሎችን በመያዝ ከተማዋን ለሚያፀዱ ወጣቶች የተሰማቸዉን ልዩ የሆነ ደስታ እና ያሳደረባቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡ይህ ተግባር በታሪክ ተመዝግቦ ይኖራል፤ መሰል ስራዎች ቢጠናከሩ ክፋት ከአካባቢያችን ይርቃል ሲሉ ወጣቶችን አበረታተዋል፡፡

የፅዳት ዘመቻዉ መስቀል አደባባይን ጨምሮ ከአዘዋ ሆቴል እስከ ሙሉአለም የባህል ማዕከል ያለዉን መንገድ ያካለለ ሲሆን በዚህ ድንቅ ተግባርም ከወጣቶች በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲዉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ መምህራንና ሰራተኞች ተሳትፈዉበታል፡፡