የኪነ ጥበብ ምሽት

“ንፁህ ትዉልድ እንፍጠር“ ፣ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት ተካሄደ

በሸጋዉ መስፍን

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ ግቢ አዳራሽ የዩኒቨርሲቲዉ ተማሪዎች፣ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ጥር 9/2012 ዓ.ም ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት ተካሂዷል፡፡

የኪነ ጥበብ ምሽቱን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲዉ የዉስጥ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ አክሎግ በተማሪዎች አነሳሽነት እና በባህል ማዕከሉ ተባባሪነት ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን አመስግነዉ፤ መሰል ዝግጅቶች በሚኖሩበት ጊዜ የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንደማይለያቸዉ ጠቁመዋል፡፡አክለዉም የዉጭ ሀገራት ተሞክሮዎችን በመጥቀስ መሰል የኪነ ጥበብ ፕሮግራሞች በተማሪዎች ህይወት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩ መዘዉተር አለባቸዉ ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዉ ለታዳሚዎች አነቃቂ ንግግር ያደረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዉ የሳይኮሎጅ መምህር አቶ ታምሩ ደለለኝ እንደተናገሩት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች  ሁለት ዋነኛ ችግሮችን ሊያስቡባቸው ይገባል ብለዋል፡፡ አንደኛው ስብዕናና ክህሎት በማይገነቡ ጊዜያዊ እርካታ ላይ በሚያተኩሩ ክዋኔዎች ለምሳሌ ቲሸርቶችን እያሳተሙ የከለር ደይ፣ ቤቢ፣ ውሃ ደይ ወይም ሌሎች የመሳሰሉት ላይ ማተኮር ሲሆን፤ ሌላው እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣው ደግሞ ሰክኖ ከመወያየት ይልቅ አለመግባባትና ግጭት በስፋት መከሰት ናቸው፡፡ ከአለመግባባት እና ግጭት ጋር በተያያዘም ተማሪዎች በዙሪያቸው ያሉ ሌሎች ተማሪዎችን እንደ ተማሪ  እንዲመለከቷቸውና እርስበእርስ እንዲተሳሰቡ መክረዋል፡፡ አቶ ታምሩ በመቀጠልም ተማሪዎች ትዕግስትና ማስተዋልን አጥብቀዉ በመያዝ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለህይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ ስንቅ የሚያገኙበት እንዲሆን እንዲያደርጉት አሳስበዋል፡፡  

በኪነ ጥበብ ምሽቱ “የንፁህ ትዉልድ እንፍጠር” በጎ ሀሳብ አፍላቂ ተማሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን በቀጣይም መሰል ፕሮግራሞች በየ 3 ሳምንቱ እንደሚካሄዱ የዩኒቨርሲቲዉ የተማሪዎች ባህል ማዕከል ኃላፊ ተማሪ ተመስገን ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡ በኪነ ጥበብ ምሽቱ በርካታ ታዳሚያን የተገኙ ሲሆን በፕሮግራሙ መደሰታቸዉን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በኪነ ጥበብ ምሽቱ በርካታ የግጥም ስራዎችን ጨምሮ ‘በቃን’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ አዝናኝና አስተማሪ ጭዉዉት አንዲሁም ‘ከኛ ጓዳ’ የተሰኘ ተከታታይ የኮሜድ ስራ ቀርቧል፡፡