የመፅሀፍ እርዳታ ተደረገ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከቡክስ ፎር አፍሪካ በዕርዳታ የተረከባቸውን መፅሀፎች ለወረዳ ትምህርት ቤቶች አከፋፈለ፡፡

በሙሉጌታዘለቀ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር ካደረገው ቡክስ ፎር አፍሪካ ከተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር ባደረገው ግንኙነት በዕርዳታ ያስመጣቸውን የሳይንስ፣ የሂሳብ፣  የቋንቋ እና ስነ-ፅሁፍ መፅሀፎችን  በይልማናዴንሳ ወረዳ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች አከፋፍሏል፡፡

የዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ የሆኑት አዴት ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ብርአዳማ አካባቢ ደግሞ በሰከላል ጃንባራ መድሀኒያለም ቀበሌ የሚገኘው ገብረን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በስማርጋ ቀበሌ የሚገኘው ቼመን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በአይቫር ቀበሌ የሚገኘው መጣቅር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ እርዳታው ለሌሎችንም የመንግስት ት/ቤቶች ያካተተ እንደነበር ታውቋል፡፡ መፅሀፎቹ ለመምህራን እና ለተማሪዎች ማጣቀሻነት የሚሆኑ ከ1ኛ - 4ኛ ክፍል እና ከ5ኛ- 8ኛ ክፍል እንዲሁም ለጎልማሶች ትምህርት የሚያገለግሉ እንደሆኑ ማወቅ ተችሏል፡፡ በእለቱም ከ10 ካርቶን በላይ የሚሆኑ የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ፣ የስነ-ፁሁፍ እና የማህበራዊ ሳይንስ ይዘት ያለቸው መፅሀፎች ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ቦታው ድረስ በመሄድ ለርዕሳነ መምህራን  ርክክብ ተፈፅሟል፡፡

በርክክቡ ወቅት በሰከላል ጃንባራ መድሀኒያለም ቀበሌ የሚገኘው ገብረን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ አዱኛ አጥናፉ እንዳሉት የተደረገላቸው የመፅሀፍ እርዳታ በገንዘብ ሊተመን የማይችልና የተማሪዎችን ብሎም የመምህራንን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ ይህም የተማሪዎቻቸውን በሀገር ደረጃ የመወዳደር አቅም የሚያጎለብት በመሆኑ የመፅሀፍ እርዳታው ለትምህርት ቤቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም በትምህርት ቤታቸው ያሉባቸውን 1ኛ. ለሳይንስ ትምህርቶች የሚያገለግሉ ኬሚካሎች 2ኛ በፀሃይ  የሚሰራ የሃይል ማመንጫ ችግር ለመቅረፍ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን አስተዋፆ እንዲያደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ካደረገው የመፅሀፍ እርዳታ በተጨማሪ በይልማናዴንሳ ወረዳ ውስጥ ለሚገኙ ከስድስት በላይ የችግኝ ጣቢያዎች ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ በሰው የሚገፉ ጋሪዎች፣አካፋዎች፣የመጎንደያ መቀሶች፣ የአሸዋ መንፊያ ወንፊቶችና መጋዞችን ለጣቢያዎቹ አበርክቷል፡፡ የይልማናዴንሳ ወረዳ የስማርጋ ችግኝ ጣቢያ ሰራተኛና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ዳሳሽ ላቃቸው እንዳሉት ችግኝ ጣቢያው በአመት ከ80ሺ በላይ የተለያዩ አገር በቀል ችግኞችን በማፍላት ለአካባቢው ማህበረሰብ በነፃ እንደሚያቀርብ ገልፀው እስካሁን ባለው የስራ ሂደት ምንም አይነት የቁሳቁስም ሆነ የግብዓት ችግር እንዳላጋጠማቸው  ተናግረዋል፡፡

የመፅሃፍ ድጋፉ በጎንደር አካባቢ ለሚገኙ የወረዳ የመንግስት ትምህርት ቤቶችም የተደረገ ሲሆን መፅሃፎች ተመሳሳይ ይዘት ያለቸው  መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡