የስነ ምድር መረጃ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል አመታዊ አውደ ጥናት አካሄደ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስነ ምድር እና መረጃ ጥናት ተቋም አራተኛውን ብሄራዊ የስነ ምድር ጥናት “የስነ ምድር መረጃ እና ቴክኖሎጅ ለዘላቂ ልማት” በሚል ርዕሰ ለሁለት ቀናት አካሄደ፡፡ 
በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ኘ/ጽ/ቤት የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዋሴ አንተነህ በአውደ ጥናቱ ተገኝተው እንደገለፁት በአለም ዙሪያ ያሉ ሁሉም ተቋማት እቅድና ውሳኔዎችን የሚወሰኑት ከስነ ምድር መረጃና ቴክኖሎጅን ተጠቅመው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተለይም እንደ ሀገር መከላከያ፣ ግብርና፣ የካርታ ሥራ፣ የውሃ ሀብት አስተዳደር፣ የመሬት አስተዳደር ፣የአየር ንብረት ለውጥ፣ በከርሰ ምድር ማዕድናት፣ ቱሪዝም፣ እና ጉዞ የስነ ምድር መረጃና ቴክኖሎጅን መሰረት አድርገው እንደሚከናወኑ ገልፀው በዘርፉ የዳበረ ልምድ ያላቸው ሀገራት ዘላቂ ልማታቸውን እያረጋገጡ ነው ብለዋል ዶ/ር ዋሴ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ የስነ ምድር መረጃና ቴክኖሎጅን መጠቀም ላይ ውስንነት እንዳለ ጠቁመው የአውደ ጥናቱ ተሣታፊዎች አዳዲስ ሀሣቦችን በማመንጨትና በማዳበር ዘላቂ ልማት ለረጋገጥ የሚያስችለንን አቅጣጫ ልንቀይስ ይገባል ብለዋል፡፡ 
ዶ/ር አስናቀ መኩሪያው የስነ ምድር መረጃና ቴክኖሎጅ ምርምር ዳይሬክተር በበኩላቸው የአዉደ ጥናቱን አላማ ሲገልፁ የስነ ምድር መረጃና ቴክኖሎጂ ምርምር ተቋም ተጨባጭ የሆነ ወቅታዊ መረጃ በማሰባሰብና በመተንተን ለውሳኔ ሰጭዎች በማቅረብ ለዘላቂ ልማት ጥቅም ላይ እንዲያውሉት ለማድረግ የሚሰራ ሲሆን በዚሀ ሂደት ተቋም ያለው አስተዋፅኦ ምን ይመስላል የሚለውን ለመወያየት ነው፡፡ በመሆኑም ወቅቱ ያፈራቸውን መሣሪያዎችን በመጠቀም ተጨባጭ መረጃ መሰረት ያደረገ ምርምር እያካሄደ ይገኛል፡፡ ተቋሙ በአሁኑ ሰዓት በጣና ዙሪያ የአፈር ካርታ (soil maps)፣ በክልሉ የድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን የመለየት፣ የደን ሽፋን ምን ያህል የካርቦን መጠን የመያዝ አቅም እንዳለው እና በክልሉ ለወባ በሽታ ተጋላጭ የሆነ አካባቢዎችን የመለየት ስራ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም የተንቀሣቃሽ ስልክን በመጠቀም በባህር ዳር ከተማ ቱሪስቶች በቀላሉ አንድን አቅጣጫ የሚያገኙበት የቱሪስት መረጃ ካርታ ተሰርቶ በጥቅም ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል፡፡ 

በሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ አንጋፋ መምህር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ነቃ የአውደ ጥናቱን መጠናቀቅ አስመልክተው እነደተናገሩት በአውደ ጥናቱ የስነምድር መረጃ እና ቴክኖሎጅ እውቀትና የካበተ የልምድ ልውውጥ የተደረገበት ነበር ማለት ይችላል ብለዋል፡፡ እንዲሁም ይህ አውደ ጥናት በየአመቱ የሚካሄድ መሆኑን ገልፀው ለቀጣይነቱ ደግሞ የተሳታፊዎች እገዛ አስፈላጊ መሆኑን አሰታውሰው ለተግባራዊነቱ በንቃት እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል፡፡ በሁለቱ ቀኑ አውደ ጥናት የስነ ምድር መረጃ እና ቴክኖሎጅን እውቀት የተመለከተ 11 የምርምር ስራዎች የቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎችም በርካታ ሀሣቦች ተነስተው ውይይት ተደርጐባቸው የወደፊት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡